ቅድመ ዳሰሳ | ድሬዳዋ ከተማ ከ ሀዲያ ሆሳዕና

በ3ኛ ሳምንት ከሚደረጉ ጨዋታዎች መካከል ድሬዳዋ ከተማ በሜዳው ሀዲያ ሆሳዕናን የሚያስተናግድበትን ጨዋታ ተከታዩ ዳሰሳችን ይመለከተዋል።

ላላፉት ሁለት ሳምንታት ከዐምና በተሻገረ ቅጣት የዋና አሰልጣኛቸውን ግልጋሎት ማገኘት ሳይችሉ የቀሩት ድሬዳዋ ከተማዎች በዚህ ሳምንት አሰልጣኝ ስምዖን ዓባይ ቡድናቸውን እየመሩ ወደ ሜዳ መግባታቸው መልካም ዜና ነው። በዚህ ጨዋታ በደጋፊያቸው ታግዘው በፕሪምየር ሊጉ ካደረጉት አስከፊ አጀማመር ለመውጣት ከፍተኛ ጥረት ያደርጋሉ ተብሎም ይጠበቃል።

ድሬዳዋ በሁለቱ የሜዳ ውጪ በአማካይ ክፍሉ የተጫዋቾች ቁጥር በማብዛት የኋላ መስመሩን ከአደጋ ለመጠበቅ ቢያልምም ስኬታማ አለመሆኑ ጨዋታውን በሜዳው ከማድረጉ ጋር ተደምሮ የማጥቃት አጨዋወትን ይዞ እንደሚገባ ይገመታል።

በብርቱካናማዎቹ በኩል ረመዳን ናስር፣ ያሬድ ሀሰን እና ያሬድ ታደሰ (አገግሟል) በጉዳት ግልጋሎት የማይሰጡ ሲሆን ከጉዳቱ እያገገመ የሚገኘው ሳምሶን አሰፋ የመሰለፉ ጉዳይም አጠራጣሪ ነው። በአንፃሩ ተከላካዩ ዘሪሁን አንሼቦ ከቅጣት መመለሱ ለተከላካይ መስመሩ እፎይታ የሚሰጥ ነው።

ከሁለት ጨዋታዎች አንድ ነጥብ በመያዝ እንደ ድሬዳዋ ሁሉ የመጀመርያ የውድድር ዓመት ድላቸውን ለማሳካት አልመው ወደ ሜዳ ይገባሉ። ቡድኑ ከሜዳው ውጪ ጨዋታውን የሚያከናውን እንደመሆኑ ለጥንቃቄ ቅድሚያ እንደሚሰጥ ይጠበቃል፤ ለዚህም በመጀመርያው ሳምንት ከመቐለ ጋር እንዳደረገው ጨዋታ ሁሉ በሦስት ተከላካዮች ጥምረት ወደ ሜዳ ሊገባ ይችላል።

ነብሮቹ የመልሶ ማጥቃት እና ረጃጅም ኳሶችን በመጠቀም የጎል እድል እንደሚፈጥሩ ሲገመት በአካላዊ ቁመናቸው ግዙፍ የሆኑት የሀዲያ ሆሳዕና የአጥቂ መስመር ተሰላፊዎች በሁለት ጨዋታ ሰባት ጎል ያስተናገደው የድሬዳዋ ከተማ የመከላከል አደረጃጀትን ይፈትናሉ ተብሎ ይጠበቃል።

በጨዋታው ሀዲያ ሆሳዕና በጉዳትም ሆነ በቅጣት የሚያጣው ተጫዋች የለም።

እርስ በርስ ግንኙነት

ቡድኖቹ በሊጉ ሁለት ጊዜ (2008) የተገናኙ ሲሆን ሁለቱንም ድሬዳዋ ከተማ በበላይነት አጠናቋል። (በሜዳው 3-2 ሲያሸንፍ ሆሳዕና ላይ ደግሞ 2-0 ረቷል።)

ግምታዊ አሰላለፍ

ድሬዳዋ ከተማ (4-2-3-1)

ፍሬው ጌታሁን

ፍሬዘር ካሣ – ዘሪሁን አንሼቦ – በረከት ሳሙኤል – አማረ በቀለ

ፍሬድ ሙሸንዲ – አማኑኤል ተሾመ

ዋለልኝ ገብሬ – ኤልያስ ማሞ – አዲሰገን ኦላንጄ

ሪችሞንድ ኦዶንጎ

ሀዲያ ሆሳዕና (3-5-2)

ታሪክ ጌትነት

በረከት ወልደዮሐንስ – ደስታ ጊቻሞ – አዩብ በቀታ

ሱራፌል ዳንኤል – አፈወርቅ ኃይሉ – ይሁን እንዳሻው – አብዱልሰመድ አሊ – ሄኖክ አርፍጮ

ቢስማርክ አፒያ – ቢስማርክ ኦፖንግ

ድሬዳዋ ከተማ (4-3-3)


© ሶከር ኢትዮጵያ