ሪፖርት | ወላይታ ድቻ እና ቅዱስ ጊዮርጊስ ያለ ጎል አቻ ተለያይተዋል

በኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ 3ኛ ሳምንት ሶዶ ላይ የተደረገው የወላይታ ድቻ እና ቅዱስ ጊዮርጊስ ጨዋታ 0-0 በሆነ ውጤተት ተጠናቋል፡፡

ባለሜዳው ወላይታ ድቻ በሁለተኛው ሳምንት በወልዋሎ ከሜዳው ውጪ ሽንፈት ከገጠመው ስብስቡ ቡድኑ ዳንኤል ዳዊት እና ዘላለም ኢያሱን በማሳረፍ ባዬ ገዛኸኝ እና እዮብ ዓለማየሁን ወደ መጀመሪያው አሰላለፍ ሲያካትት ሰበታ ከተማን አሸንፈው ወደ ሶዶ ያመሩት ፈረሰኞቹ በጉዳት ባጡት ሳላሀዲን ሰይድ ምትክ ዛቦ ቴጉይን ተሰላፊ በማድረግ ጨዋታው ተጀምሯል፡፡

በሁለቱም አጋማሾች አሰልቺ እና ለተመልካች የማይመጥን እንቅስቃሴን ባልተመለከትንበት ጨዋታ ቡድኖቹ ምርጫቸው አድርገው የገቡት ተደጋጋሚ ረጃጅም ኳሶች ፍሬ ማፍራት ያልቻሉበት ሆኖ አልፏል። ከጨዋታው እንቅስቃሴ ይልቅም ረጅም ኪሎ ሜትሮችን አቋርጠው የመጡት የፈረሰኞቹም ሆኑ የባለሜዳው ወላይታ ድቻ ደጋፊዎች ህብረ ዝማሬ ጎልቶ የወጣበት ነበር።

በባለሜዳው በኩል በ12ኛው ደቂቃ ላይ ባዬ ገዛኸኝ ከቅዱስ ጊዮርጊሱ ግብ ጠባቂ ባህሩ ነጋሽ ጋር አንድ ለአንድ ተገናኝቶ የግል ጥረቱን ተጠቅሞ ሞክሮ ኢላማዋን ሳጠብቅ የወጣችው፤ በቅዱስ ጊዮርጊሶች በኩል ደግሞ ከማዕዘን ምት ሀይደር ሸረፋ አሻምቶ አቤል ያለው መቶ ግብ ጠባቂው መክብብ ደገፉ ያዳነበት እንዲሁም ወላይታ ድቻዎች በመሀል ሜዳ ላይ ኳስን ሲቀባበሉ ሙሉዓለም መስፍን ከእድሪስ ሰይድ እግር ነጥቆ አክርሮ መትቶ መክብብ በቀላሉ ከያዛት ኳስ ውጪ ይህ ነው ብለን ልንጠቅሰው የምንችለው ተጨማሪ ሙከራን መመልከት አልቻልንም፡፡

በመጀመርያው አጋማሽ ወደ ኃይል አጨዋወት አመዝነው ሲጫወቱ የነበሩት የቅዱስ ጊዮርጊስ ተጫዋቾች ለሚፈፅሙት ጥፋት የእለቱ ዋና ዳኛ አዳነ ወርቁ ሲወስኗቸው በነበሩ ውሳኔዎች ላይ የወላይታ ድቻው አሰልጣኝ ገብረክርስቶስ ቢራራ ከአራተኛ ዳኛው ቴዎድሮስ ምትኩ ጋር ፈገግ የሚያሰኙ እና ሳቅ የተቀላቀለባቸው ንግግሮች ትኩረት ሳቢ ነበሩ።

ከእረፍት መልስ ሁለቱም ቡድኖች የአቀራረብ ለውጥ በማድረግ ተሻሽለው ይቀርባሉ ተብሎ ቢጠበቀም ይባሱኑ ደካማ እንቅስቃሴ የታየበት ሆኗል።
በቅዱስ ጊዮርጊስ በኩል ያደረገው ሦስት ኢላማቸውን ያልጠበቁ ሙከራዎች የተደረጉ ሲሆን አቤል ያለው በቀኝ በኩል ሁለት ጊዜ ፍጥነቱን በመጠቀም ገብቶ ሲሞክር መክብብ ያዳነበት እና እና በ82ኛው ደቂቃ መክብብ ደገፉ ኳስ ለማስጣል ሲወጣ አቤል ጥንካሬ አልባ ምት በመምታቱ አቅጣጫዋን ስታ የወጣችው ኳስ ተጠቃሽ ናቸው። 

በአንፃሩ ወላይታ ድቻ በኩል ኳስ መስርተው ወደ ተጋጣሚ የጎል ክልል ለመግባት ያደረጓቸው ሙከራዎች በጊዮርጊስ ጠንካራ የመከላከል አደረጃጀት ምክንያት ወደ ግብ እድልነት ሳይቀየሩ ቀርተዋል። ጨዋታው ያለምንም ግብ ተደምድሟል፡፡

*እጅግ በርካታ ደጋፊዎችን የሚያስተናግደው የወላይታ ሶዶ ስታዲየም በርካታ ተመልካቾች ሜዳው በመሙላቱ ምክንያት በዛፎች እና እንዲሁም ከሜዳው ውጪ ባሉ የሰዎች መኖሪያ ቤት ጣራዎች ላይ ሆነው ሲመለከቱ ማየት የሜዳው መለያ እየሆነ የመጣ ሲሆን ይህም ተጨማሪ የማስፋፊያ ስራዎች እንደሚጠብቁት ያመላክታል፡፡


© ሶከር ኢትዮጵያ