ሪፖርት | ወልቂጤ ከተማ በታሪኩ የመጀመርያ የፕሪምየር ሊግ ድሉን አስመዘገበ

በሦስተኛ ሳምንት የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ በተለዋጭ ሜዳ ለመጫወት የተገደደው ወልቂጤ ከተማ በሆሳዕናው አቢዮ ኤርሳሞ መታሰቢያ ስታዲየም ፋሲል ከነማን አስተናግዶ 1-0 በሆነ ውጤት በማሸነፍ የሊጉ የመጀመርያ ሦስት ነጥቡን አሳክቷል።

በሁለት የተለያየ የውጤት መንገድ የሚጓዙ ቡድኖች ባገናኘው ጨዋታ ጎል ማስቆጠር አልቀና ያልው ወልቂጤ ከተማ በአዳማ ከተማ 1-0 በሆነ ጠባብ ውጤት ከተሸነፈው ስብስቡ በጉዳት ቶማስ ስምረቱን በመሐመድ ሽፋ እንዲሁም አቤኔዘር ኦቴ ፣ አልሳሪ አልመሐዲን እና አህመድ ሁሴንን በማሳረፍ ኤፍሬም ዘካርያስ፣ በረከት ጥጋቡ እና ጫላ ተሺታን ተክተው ወደ ሜዳ ገብተዋል። በዐፄዎቹ በኩል ባለፈው ሳምንት ድሬደዋ ከተማን 5–0 በሆነው ውጤት ከረመረመው ቡድናቸው ጥንቃቄ ለማድረግ የፈለጉት አሰልጣኝ ሥዩም ከበደ በዛብህ መለዮን አሳርፈው ሐብታሙ ተከስተን ብቻ ተክተው ገብተዋል።

ሜዳው በዕድሳት ምክንያት ለጊዜው አገልግሎት የማይሰጠው የወልቂጤ ስታዲየም የመጀመርያ ሳምንት የሜዳውን ጨዋታውን ወደ ባቱ ከተማ ሼር ሜዳ በመጓዝ አድርጎ የነበረ ቢሆንም የዛሬውን ጨዋታ ወደ በሆሳዕናው አቢዮ ኤርሳሞ መታሰቢያ ስታዲየም በመቀየር ፋሲል ከነማን አስተናግዷል።

ፌደራል ዳኛ ሐብታሙ መንግስቴ በመረው በዚህ ጨዋታ የመጀመርያው አጋማሽ በሁለቱም ቡድን በኩል ማራኪ እንቅስቃሴ ሳይታይበት መድረሻቸው የማይታወቁ ረዣዥም ኳሶች በዝተውበት ነበር። ለዚህም ምክንያቱ ኳሱን ይዞ ክፍት ሜዳ ለመፈለግ ሜዳው ኳስን መሬት አድርጎ ለመጫወት አመቺ አለመሆኑ ነው። ሆኖም ይህ የረዥም ኳስ አጠቃቀም ለፋሲሎች ሲያስቸግር ለወልቂጤ ከተማዎች በአንፃሩ ምቾት የሰጣቸው ይመሰል ነበር።

ጨዋታው ጎል ያስተናገደውም ገና በስድስተኛው ደቂቃ ላይ ነበር። ተከላካዩ ዐወል መሐመድ ከፋሲሎች በኩል የመጣውን የማጥቃት እንቅስቃሴ በማቋረጥ በረዥሙ የጣለውን ኳስ ጃኮ አራፋት ከፋሲል ተከላካዮች በፍጥነት በመውጣት ተረጋግቶ እየገፋ ሳጥን ውስጥ በመግባት ጎል አስቆጥሯል። ይህች ጎል ዘንድሮ ወደ ኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ላደገው ወልቂጤ ከተማ በታሪኩ የመጀመርያ ጎል ስትሆን፣ ለጃኮ አራፋትም የውድድር ዓመቱ የመጀመርያው ጎል ሆናለች።

ዐፄዎቹ ከድል የመምጣታቸውን ያህል ብዙም መልካም እንቅስቃሴ ማድረግ ባይችሉም በ23ኛው ደቂቃ ሱራፌል ዳኛቸው በረጅሙ የተጣለለትን ሙጂብ በሁለት ተከላካዮች መሐል አልፎ ኳሱ ደርሶ። የክትፎዎቹ ግብጠባቂ ሶሆሆ ሜንሳህ ከግብ ክልሉ በመውጣት ኳሱን በግንባሩ ገጭቶ ለማራቅ ሲሞክር ሙጂብ እግር ስር ገብታ ወደ ጎል የመታት ኳስ አቅጣጫዋን ስታ ለጥቂት ወደ ውጭ ወጥቶባቸዋል።

ፋሲሎች ወደ ጨዋታው በፍጥነት ለመመለስ ጥረት በሚያደርጉበት ወቅት ስኬታማ በሆነው የመልሶ ማጥቃት አጨዋወታቸው ወልቂጤዎች በፈጣኑ የመስመር አጥቂ ጫላ ተሺታ አማካኝነት ጥሩ የጎል አጋጣሚ አግኝተው ሳይጠቀሙበት ቀርተዋል።

ጨዋታው አስቀድመን በገለፅነው የአየር ላይ ኳስ በዝቶበት ሲቀጥል ፋሲሎች በአስገዳጅ ሁኔታ ሽመክት ጉግሳ ጉዳት በማስተናገዱ ምክንያት በእርሱ ምትክ በዛብህ መለዮን ሲያስገቡ በእንቅስቃሴው ጥሩ ያልነበረውን ኢዙ አዙካን በኦሰይ ማውሊ በመቀየር ወደ ጨዋታው ለመመለስ ጥረት አድርገዋል። በ34ኛው ደቂቃም ኦሰይ ማውሊ ከግራ መስመር ያሻገረውን ሙጂብ ቃሲም በነፃ አቋቋም ከሳጥን ውጭ ለነበረው ለሱራፌል ዳኛቸው በግንባሩ አቀብሎት ሱራፌል በጥሩ ሁኔታ ኳሱ አየር ላይ እያለ መሬት ለመሬት ቢመታውም ለጥቂት የግቡ ቋሚን ተኮ ወጥቶበት ጨዋታው በወልቂጤ 1–0 በሆነ መሪነት እረፍት ወጥተዋል።


የወልቂጤው አሰልጣኝ ደግአረገ ይግዛው ውጤቱን አስጠብቆ ለመውጣት የጥንቃቄ አጨዋወት በመምረጥ በሁለተኛው አጋማሽ ጅማሬ ላይ የመስመር አጥቂውን ሄኖክ አወቀን በአልሳሪ እንዲሁም አዳነ አባይነህን በአቤኔዘር ኦቴ በመቀየር የተጫዋች ለውጥ አድርገው ገብተዋል።

ዐፄዎቹ ከመጀመርያው አጋማሽ በተሻለ መንቀሳቀስ በቻሉበት በሁለተኛው አጋማሽ በ50ኛው ደቂቃ ከፋሴሎች የሜዳ ክፍል ከቅጣትም በረጅሙ ወደ ጎል ከድር ኩሊባሊ የመታውን በዛብህ መለዮ ሳይታሰብ ከተከላካዮች መሐል ያገኛትን ነፃ ኳስ በግንባሩ ቢመታውም ወደ ውጭ ሊወጣበት ቻለ እጂ ጥሩ የጎል አጋጣሚ ነበር።

የሜዳው ኳስን ይዞ እንዴት መጫወት የገባቸው ፋሲሎች ብዙም ሳይቆይ በመሐል ሜዳ ኦሰይ ማውሊ፣ ሱራፌል ዳኛቸው እና በዛብህ መለዮ በጥሩ የደብል ኳስ ቅብብል ኦሰይ ማሊ በመጨረሻም ወደ ግብ ክልሉ ገብቶ በግራ እግሩ ወደ ጎል የመታው ኳስ ለጥቂት ወደ ውጭ ወጥቶበታል።


ዐፄዎቹ በዚህ ሁሉ ጫና ፈጥረው በሚያደርጉት እንቅስቃሴ ውስጥ ወልቂጤዎች በመልሶ ማጥቃት ከግብ ክልላቸው ለማራቅ ተከላካዮች የመቱትን ኳስ የመጀመርያውን ጎል ባስቆጠረበት መንገድ ነፃ ኳስ ጃኮ አግኝቶ ከውሳኔ ችግር ሳይጠቀምበት የቀረው የማግባት አጋጣሚ አደገኛ ነበር።

በመልሶ ማጥቃት የሚሰነዘርባቸውን ጥቃት እየፈተናቸው ባሉበት አጋጣሚ ፋሲሎችን አቻ ማድረግ የሚችል አጋጣሚ በ57ኛው ደቂቃ አግኝተው ነበር። ሱራፌል ከቀኝ ወደ መሐል ኳሱን አጥቦ ያሻገረውን ኳስ የግብ ክልሉን በዛሬው ዕለት በንቃት ሲጠብቅ የዋለው የወልቂጤው ግብጠባቂ ሶሆሆ ሜንሳህ በቀላሉ እይዛለው ብሎ በመትፋቱ የፋሲሎች አጥቂ ኦሰይ ማውሊ አግኝቶ በቀጥታ ወደ ጎል የመታው ኳስ ጎል ሆነ ሲባል በዛሬው ጨዋታ በቶማስ ስምረቱ ምትክ የገባው መሐመድ ሽፋ እንደምንም ኳሱን ተደርቦ ወደ ውጭ ያወጣት ኳስ ለዐፄዎቹ የምታስቆጭ የጎል አጋጣሚ ሆና አልፋለች።

የጨዋታው እንቅስቃሴ ቀጥሎ በሌላ አጋጣሚ ፋሲሎች 70ኛው ደቂቃ ላይ ሱራፌል ዳኛቸው ያሻገረውን ሙጂብ ቃሲም ለተከላካዮች ጀርባውን ሰጥቶ ኳሱን ወደ ጎል አዙሮ ቢመታውም ኳስ ፊት ለፊት የተመታ በመሆኑ ሶሶ ሜንሳ በቀላሉ ይያዘው እንጂ ጎል የመሆን የሚችል ጥሩ ዕድል ነበር።

በጥሩ የመከላከል አደረጃጀት እና የመልሶ ማጥቃት አጨዋወት እየተከተሉ ውጤቱን አስጠብቀው ለመውጣት በከፍተኛ ፍላጎት ብርቱ ትግል እያደረጉ ባለበት ወቅት ወልቂጤዎች በቀሪው አስራ አምስት ደቂቃ ትልቅ ፈተና ይሆንባቸዋል የተባለ ክስተት አጋጥሟቸዋል። በ75ኛው ደቂቃ ኤፍሬም ዘካርያስ በሱራፌል ዳኛቸው ላይ ጥፋት ሰርተሃል በማለት የዕለቱ ዳኛ በሁለት ቢጫ በቀይ ካርድ ከሜዳ አስወጥተውታል።

ዐፄዎቹ ከእረፍት መልስ እንደፈጠሩት ጫና በቀሩት ደቂቃዎች የወልቂጤን የተጫዋች ቁጥር መቀነስ ተከትሎ ጎል ያስቆጥራሉ ተብሎ ቢገመትም የሆነው በዚህ ተቃራኒ ነው። የፈጣኑን የመስመር አጥቂ የጫላ ተሺታን ፍጥነት መቆጣጠር የተቸገሩት ዐፄዎቹ 82ኛው ደቂቃ ላይ በመልሶ ማጥቃት ጫላ ያሬድ ባዬን በፍጥነት ቀድሞ ግብጠባቂው ሳማኬ ሚኬል በማይታመን መልኩ ያዳነበት፤ በጨዋታው መጨረሻ 90ኛው ደቂቃ በፍጥነቱ እየተጠቀመ ከመስመር ወደ መሐል እያጠበበ ወደ ጎል የሚደርሰው የዛሬው ለዐፄዎችን ፈተና ሆኖ የዋለው ጫላ ተሺታ ከድር ኩሊባሊን ቀድሞ ለብቻው ከግብጠባቂው ሳማኬ ሚኬል ተገናኝቶ በጥሩ መንገድ ወደ ጎል ቢመታውም በድጋሚ ሳማኬ በአስደናቂ ሁኔታ ያዳነበት ጨዋታውን ክትፎቹ ከአንድ ጎል በላይ አሸንፈው እንዲወጡ ማድረግ የሚችሉባቸው ግልፅ የጎል እድሎች ነበሩ።


ጨዋታው በወልቂጤ ከተማ 1-0 አሸናፊነት መጠናቀቁን ተከትሎ ዘንድሮ ወደ ኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ያደገው ወልቂጤ ከተማ በታሪኩ የመጀመርያ የሊጉ ድሉን ሲያሳካ የጃኮ አራፋት ጎልም በክለቡ የፕሪምየር ሊግ ታሪክ የመጀመርያዋ ሆናለች።

የወልቂጤ ከተማ ደጋፊዎች በሚገርም ስፖርታዊ ጨዋነት ከደስታቸው ጎን ለጎን የፋሲል ከነማ ደጋፊዎችን በህብረ ዝማሬ በሰላም ግቡ እያሉ የሸኙበት ሁኔታ የወልቂጤ ደጋፊዎችን የሚያስመሰግን በሌሎች ሜዳዎችም ሊለመድ የሚገባ ተግባር ነው።


© ሶከር ኢትዮጵያ