የአሰልጣኞች አስተያየት| ስሑል ሽረ ከ ወልዋሎ

ወልዋሎዎች በጁንያስ ናንጂቦ እና ገናናው ረጋሳ ግቦች ስሑል ሽረን ካሸነፉ በኃላ የሁለቱም ቡድን አሰልጣኞች የሚከተለውን ሃሳብ ሰጥተዋል።

“ውድድሩ ገና ነው፤ ለዋንጫ ቀርቶ ለደረጃ የሚያኩራራ ነገር የለም” ዮሐንስ ሳህሌ

ስለ ጨዋታው

የሰራነውን ነው ያገኘነው፤ ሰርተንበታል በደንብ ተዘጋጅተንበታል። ባለፈው ሳምንት ሁለት ተጫዋቾች በአንዳንድ የግል ጉዳይ ምክንያት ጎድለውብን ነበር። እነሱ ተመልሰው በማግኘታችን በሙሉ ልብ ነው የተጫወትነው። ያሰብነውን ነው ያደረግነው። በመልሶ ማጥቃት ለመጫወት ፈጣን ተጫዋቾች ስላሉን እሱን መጠቀም አለብን ብለን ነው እንደዛ ያደረግነው። በመከላከል ደረጃም ተጋጣሚ ወደኛ ግብ ክልል እንዳይጠጉ ነበር አንዳንድ ታክቲካል ነገሮች የሰራነው። እሱንም ተጫዋቾቹ በጥሩ መንገድ ተግብረውታል ማለት እንችላለን።

ስለ ቡድኑ ጥሩ አጀማመር እና እቅድ

ገና በርካታ ጨዋታዎች አሉብን። ከዋንጫ ጋር የሚያገናኝ ነገር የለውም። ለምንጫወተው ጨዋታ ኃላፊነት ወስደን ጨዋታውን መወጣት አለብን። ሌላው ግዜ የሚፈታው ነገር ነው። አዲስ ቡድን ነው፤ የማቀናጀት ስራ አለብን። ብዙ ብዙ የምንሰራቸው ስራዎች አሉ፤ ማስተካከል አለብን። ስላሸነፍን ብቻ አይደለም። ውድድሩ ገና ነው። ለዋንጫ ቀርቶ ለደረጃም የሚያኩራራ ነገር የለም።

“በመከላከል ላይ ያለን ክፍተት ዋጋ እያስከፈለን ነው” ሳምሶን አየለ

ጨዋታው ጠንካራ ፉክክር የነበረበት ነው። ግን እስካሁን ድረስ እንደ ችግር የሚታየው የተከላካይ መስመራችን ከፍተኛ ክፍተት አለበት። በስጋት ደረጃም እሱ ላይ ጠንክረን እየሰራን ነው። በመከላከል ላይ ያለን ክፍተት ነው ዋጋ እያስከፈለን ያለው። ከዛ ውጭ በአማካይም በአጥቂም ቶሎ ቶሎ ወደ ግብ የሚደርስ ጥሩ አቅም ያለው ቡድን ነው ያለን። በጥቃቅን ታክቲካል ስህተቶች ጎል እየገቡብን ዋጋ እያስከፈሉን ነው። ለቀጣይም እሱ ላይ ጠንክረን እንሰራለን።

ስለ ቡድኑ ችግሮች

ታክቲካሊ በመከላከል ላይ የአቋቋም ክፍተቶች አሉ። የተለያዩ ተጫዋቾች ቀያይረን እየሞከርን ነው፤ እሱ ላይ ያለንን ክፍተት እንቀርፋለን። ከቡድን ስሜት ጋር በተያያዘ ትልቁ ችግር ከደሞዝ ጋር በተያያዘ ጉዳይ ዛሬ ጠዋት ስራ አስፈፃሚው መጥቶ እስከ ቀጣይ ሳምንት ድረስ በተሟላ ሁኔታ እንደሚከፈል ተናግረዋል።

የተጋጣሚን የመልሶ ማጥቃት ለመመከት ስለነበራቸው ቅድመ ዝግጅት

ተዘጋጅተንበት ነበር የገባነው። ቅድም እንዳልኩት የመናበብ ችግር ነው። ከነሱ የሚመጡት ረጃጅም ኳሶች በማሸነፍ እና ኳሶች እያንሸራሸርን ለመጫወት ነበር ያቀድነው። ግን እነሱን ተግባራዊ የማድረግ ችግሮች ነበሩ።


© ሶከር ኢትዮጵያ