ከፍተኛ ሊግ ሐ | አርባምንጭ፣ ነገሌ አርሲ እና ባቱ ከተማ አሸንፈዋል

ትላንት የተጀመረው የኢትዮጵያ ከፍተኛ ሊግ ዛሬም ቀጥሎ ሲደረግ በምድብ ሐ ነገሌ አርሲ በሜዳው፣ አርባምንጭ ከተማ እና ሻሸመኔ ከተማ ከሜዳቸው ውጪ አሸንፈዋል።

ቡታጅራ ከተማ ከፕሪምየር ሊግ የወረደው ደቡብ ፖሊስን አስተናግዶ ያለ ጎል አቻ ተለያይቷል። አሰልቺ እና በሙከራዎች ያልታጀበው የመጀመርያው የጨዋታ ክፍለ ጊዜ በሁለቱም ቡድኖች በኩል ይህ ነው የሚባል የጠራ የግብ እድሎችን ባያስመለክትም ቀስ በቀስ እየተሟሟቀ ሄዷል። ኳስ ተቆጣጥሮ በመጫወት እንዲሁም ጨዋታውን ከራሳቸው የግብ ክልል በመጀመር መስርተው ለመውጣት የሚጥሩት ሁለቱም ቡድኖች በተመሳሳይ መልኩ የሜዳው መሐለኛው ክፍል ላይ ሲደርሱ በሚቆራረጥ አጨዋወት ተስተውሎባቸዋል።

በባለሜዳዎቹ በኩል አብዱልከሪም ቃሲም እና በላይነህ ገዛኸኝ በመጀመሪያው አጋማሽ ለግብ የቀረበ ሙከራዎች ማድረግ የቻሉ ሲሆን ከኤርምያስ ሳብሬ ከቀኝ መስመር በሚጣሉት ኳሶች ጫና ማድረግም ችለው ነበር። በመጀመርያው አጋማሽ የመጨረሻ ደቂቃ ላይ ድንቅነህ ከበደ አማካኝነት ጥሩ የግብ ሙከራ ማድርግም ችለዋል። በደቡብ ፖሊሶች በኩል ኤሪክ ሙራንዳ እና ብሩክ ኤልያስ የግብ ሙከራ ማድረግ ችለዋል።

ከመጀመሪያው አጋማሽ የተሻለ እንቅስቃሴ ያስመለከተው ሁለተኛው አጋማሽ ሙከራ ለማስተናገድ ደቂቃዎች አልፈጀበትም። በ46ኛው ደቂቃ ተደራጅተው ወደ ደቡብ ፖሊሶች የግብ ክልል የደረሱት የአሥራት አባተ ተጨዋቾች በአብዱልአዚዝ አሚን አማካኝነት ጥሩ ሙከራ በማድረግ የፖሊሶችን ግብ ፈትሸዋል።

ኳስ ለተጋጣሚ ሰጥተው ጨዋታቸውን ማድረግ የቀጠሉት ደቡብ ፖሊሶች ከየአቅጣጫው ጥቃቶች ሲሰነዘርባቸው ውሏል። በተለይም በ58ኛው ደቂቃ ላይ የግል ክህሎትን ተጠቅሞ አብዱላዚዝ አራት ተጫዎቾችን በማለፍ ወደ ግብ አክርሮ የመታው ኳስ ግብ ጠባቂው ሲያድንበት በ78ኛው ደቂቃ ላይ በቀጥተኛ አጨዋወት ወደ ደቡብ ፖሊሶች የግብ ክልል ያመሩት ቡታጅራዎች በበላይ አማካኝነት ግብ ለማስቆጠር ሞክረው የነበረ ቢሆንም ፋሪስ አላዊ አድኖበታል።

እጅጉን ተጭነው የተጫወቱት ቡታጅራዎች ከዕረፍት መልስ ግብ ለማስቆጠር ቢጥሩም በለስ ሳይቀናቸው ቀርቷል። በተቀራኒው እጅጉን ወደኋላ በመሳብ በራሳቸው የግብ ክልል ላይ ብቻ ለመጫወት ጥረት ያደረጉት ደቡብ ፖሊሶች በጨዋታው መጠናቀቂያ ላይ የማጥቃት እንቅስቃሴውን ከባለሜዳው በመውሰድ ጫና ያደረጉም ሲሆን ሙፊድ እንድሪስ ከርቀት የመታውን ኳስ የግቡን የማዕዘን ብረት ለትሞ የወጣበት ፖሊስ ከሜዳ ውጪ ሦስት ነጥብ ይዞ ለመመለስ እጅጉን ያቃረበች ነበረች። ጨዋታውም ግብ ሳይታይበት ተጠናቋል።

አዲስ አበባ ኦሜድላ ሜዳ ላይ የካ ክፍለ ከተማ በአዲስ አዳጊው ባቱ ከተማ 2-1 ተሸንፏል። በ24ኛው ደቂቃ እንድሪስ በክሪ ጎል አስቆጥሮ የካን ቀዳሚ ቢያደርግም በመጨረሻዎቹ 20 ደቂቃዎች ባቱ ከተማዎች ድል ያስመዘገቡባቸውን ጎሎች አስቆጥረዋል። 70ኛው ደቂቃ ታሪኩ ክንፉ እንዲሁም በተጨማሪ ደቂቃ ብርሀኑ ሆራ ናቸው ጎሎቹን ያስቆጠሩት።

ነገሌ አርሲ በሜዳው ጌዲኦ ዲላን ገጥሞ 2-1 አሸንፏል። ዲላዎች በታምሩ ባልቻ ጎል ቀዳሚ መሆን ቢችሉም በመጀመሪያው አጋማሽ ታየ ጋሻው እንዲሁም ሁለተኛውን አጋማሽ አላዛር ዝናቡ ያስቆጠሯቸው ጎሎች ነገሌን አሸናፊ አድርገዋል።

ወደ አዲስ አበባ ተጉዞ ዊንጌት ኮሌጅ ሜዳ ላይ ኮሌፌ ቀራኒዮን የገጠመው አርባምንጭ በመጨረሻው ደቂቃ በተቆጠረ ጎል ሦስት ነጥቦች አሳክቷል። ለአዞቹ 89ኛው ደቂቃ ላይ አሸናፊ ኤልያስ ግቡን አስቆጥሯል።

ሺንሺቾ ከስልጤ ወራቤ ያለምንም ግብ የተጠናቀቀ ሌላው የዚህ ምድብ ጨዋታ ሲሆን ቂርቆስ ክፍለ ከተማ ከኢትዮጵያ መድን ሊያደርጉት የነበረው ጨዋታ ወደ ሌላ ጊዜ ተሸጋግሯል።


© ሶከር ኢትዮጵያ