ከፍተኛ ሊግ ሀ | ልደቱ ለማ ሐት-ትሪክ ሲሰራ ለገጣፎ፣ ኮምቦልቻ እና ፌዴራል ፖሊስ አሸንፏል

ትላንት በተካሄዱ ሁለት ጨዋታዎች የከፍተኛ ሊጉ ምድብ ሀ ዛሬ ሲቀጥል ለገጣፎ ለገዳዲ፣ ወሎ ኮምቦልቻ እና ፌዴራል ፖሊስ ድል አስመዝግበዋል።

ለገጣፎ ላይ ለገጣፎ ለገዳዲ ከደሴ ከተማ ያደረጉት ጨዋታ አወዛጋቢ ክስተቶች እና ጠንካራ ፉክክር አስተናግዶ በባለሜዳው 4-3 አሸናፊነት ተጠናቋል። በወጣቱ አሰልጣኝ ዳዊት ሀብታሙ የሚመራው ለገጣፎ በቀድሞ ተጫዋቾቹ ልደቱ ለማ እና ፋሲል አስማማው አማካኝነት ወሳኝ ሦስት ነጥብ አሳክቶል።

ገና በጊዜ ጎል ማስቆጠር የጀመሩት ለገጣፎዎች በ8ኛው ደቂቃ ልደቱ ለማ ግብ አግብቶ መሪ መሆን ቢችሉም በ42ኛው ደቂቅ አኩዬር ቻም የአቻነቱን ግብ ለደሴ አስቆጥሮ ወደ እረፍት አምርተዋል። ከእረፍት መልስ በ49ኛው ደቂቃ አንዋር አብዱልጀባል በሁለት ቢጫ ካርድ ከሜዳ በመወገዱ በጎዶሎ መጫወት የጀመሩት ጣፎዎች በይበልጥ በማጥቃት በልደቱ ለማ አማካኝነት በ56ኛው ደቂቃ በጨዋታ እና በ64ኛው ደቂቃ በፍፁም ቅጣት ምት እንዲሁም በ68ኛው ደቂቃ ፋሲል አስማማው በጨዋታ በተከታታይ ባስቆጠሯቸው ግቦች 4-1 ቢመሩም አኩዬር ቻም እንዲሁም ማታይ ሉል ሁለት ግቦች ለደሴ ከተማ አስቆጥረው ልዩነቱን አጥብበዋል። በጨዋታው መጠናቀቂያ ላይ የደሴው ማታይ ሉል በክርኑ በመማታቱ በቀጥታ ቀይ ካርድ ከሜዳ ወጥቷል። ሙሉ የጨዋታው ክፍለ ጊዜም በለገጣፎ 4-3 አሸናፊነት ተጠናቋል።

ኮምቦልቻ ላይ ወሎ ኮምበልቻ አቃቂ ቃሊቲን አስተናግዶ 2-1 አሸንፏል። በ24ኛው ደቂቃ ላይ ሚኪያስ ደምሴ አቃቂን ቀዳሚ ቢያደርም ከዕረፍት መልስ የሻምበል መላኩ ልጆች ሁለት ግቦች በማስቆጠር ሶስት ነጥብ ማሳካት ችለዋል። በ56ኛው ደቂቃ ሀብታሙ ወርቁ እንዲሁም በ78ኛው ደቂቃ ላይ እዮብ ወልደማርያም ያሻማውን ኳስ የአቃቂ ተከላካይ በራሱ ላይ አስቆጥረዋል።

ሼህ መሐመድ አላሙዲን ስታዲየም ላይ ወልዲያ ፌዴራል ፖሊስን አስተናግዶ 1-0 ሽንፈት ገጥሞታል። ለፌዴራል ፖሊስ ብቸኛዋን ጎል ያስቆጠረው በ22ኛው ደቂቃ ላይ ነቢዩ አህመድ ነው።

አክሱም ላይ አክሱም ከተማ አዲስ አዳጊው ሰሜን ሸዋ ደብረ ብርሃንን አስተናግዶ 1-1 አቻ ወጥቷል። አክሱሞች በ22ኛው ደቂቃ ፈጣኑ የፊት መስመር ተጫዋች ዘካርያስ ፍቅሬ ግብ አስቆጥሮ መሪ መሆን ቢችሉም የእዮብ ማለ ቡድን በ53ኛው ደቂቃ ሀብታሙ ነጋሽ ባስቆጠረው ግብ ታግዘው አንድ ነጥብ ማሳካት ችለዋል ።

ትላንት በተካሄዱ ሁለት ጨዋታዎች ደደቢት ከኤሌክትሪክ 1-1 ሲለያዩ ሶሎዳ ዓድዋ ከሜዳው ውጪ ገላን ከተማን 3-0 አሸንፏል።


© ሶከር ኢትዮጵያ