የፋሲል ከነማ ታዳጊዎች ቅሬታ እና የክለቡ ምላሽ

የኢትዮጵያ ዋንጫ እና የኢትዮጵያ አሸናፊዎች አሸናፊ ባለድል ፋሲል ከነማ ‘ለታዳጊ ቡድኑ ትኩረት እየሰጠ አይደለም ‘ በሚል የክለቡ ታዳጊዎች ለሶከር ኢትዮጵያ ያሰሙት ቅሬታ እና የክለቡ ፕሬዝዳንት በጉዳዩ ላይ የሰጡትን ምላሽ እንደሚከተለው አዘጋጅተንላችኋል።

በ2011 የውድድር ዓመት ጥሩ ጊዜ የነበረው የፋሲል ከነማ ተስፋ ቡድን የ20 ዓመት በታች ፕሪምየር ሊግ ምድብ ‘ለ’ በሦስተኝነት በማጠናቀቅ በኢትዮጵያ እግርኳስ ፌዴሬሽንም የስፖርታዊ ጨዋነት ዋንጫ ተሸላሚ በመሆን አሳልፏል። ሆኖም በበድኑ ውስጥ የሚገኙት ታዳጊዎች በርካታ ቅሬታዎች እንዳላቸው ለድረ ገፃችን ገልፀዋል።

ታዳጊዎቹ በአግባቡ ትጥቅ ካለማግኘት ጀምሮ ጥራት የሌለው ትጥቅ በሚቀርብበት ተስፋ ቡድኑ ውስጥ ከልምምድ በኋላ የሚመገቡት በቂ ምግብ እና የመጠጥ ውሃ ጭምር እንደማይቀርብላቸው ገልፀዋል። በቁሳቁስ ደረጃም ኳሶች ፣ ኮኖች ፣ የልምምድ መለያዎች እንዲሁም ሌሎች ለልምምድ አስፈላጊ የሚባሉ ቁሳቁሶች እጥረት እንዳለባቸው የሚያስረዱት ተጫዋቾቹ ለውድድር እንዲሁም ለዝግጅት ዋናው ስታድየም እንዲፈቀድላቸው እንዲሁም ምክትል አሰልጣኝ ፣ የግብ ጠባቂ አሰልጣኝ እና የህክምና ባለሙያ እንደሚያስፈልጋቸው ለሶከር ኢትዮጵያ አስረድተዋል።

በደምወዝም ላይ ቅሬታ ያላቸው ታዳጊዎቹ የሚሰጣቸው የኪስ ገንዘቡ በቂ አለመሆኑን የገለፁ ሲሆን ለትራንስፖርት በወር እስከ ስድስት መቶ ብር የሚያወጡ ታዳጊዎች እንዳሉ እና ገንዘቡ ከትራንስፖርት የዘለለ ጥቅም እንደ ሌለው እና በግላቸው ተጨማሪ ምግብ ለመመገብ እንኳን እንዳልቻሉ ተናግረዋል። በቅርቡ ወድድር የሚጀምሩት ታዳጊዎቹ ከ20 ዓመት በታች ፕሪምየር ሊግ ላይ የሚሳተፉ ሲሆን በርካታ ፈተናዎች እንዳሉባቸው እና ለውድድር ዝግጅት ላይ በመሆናቸው ያለውን ነገር ክለቡ በአስቸኳይ እንዲቀርፍላቸው ደጋፊዎችም ያሉባቸውን ችግሮች እንዲያውቁላቸው ሀሳባቸውን ይሰጣሉ።

ዋናውን ፕሪምየር ሊግ ከተቀላቀለ አራተኛ ዓመቱን የያዘው ፋሲል ከነማ ታዳጊዎችን የማሳደግ ልምድ ቢኖረውም ለተስፋው ቡድን ትኩረት መንፈጉ ይህ አካሄዱ ላይ እክል ሊፈጥርበት ይችላል። የክለቡ መሰረት የአጨዋወት ባህሉን ይዘው በሚያድጉ ታዳጊዎች ላይ እንዲቆምም ችግሮችን ከወዲሁ ለመፍታት መሞከር ወሳኝ እንደሆነ ዕሙን ነው። በመሆኑም የታዳጊዎቹን ጥያቄ በመያዝ ከክለቡ ፕሬዝዳንት አቶ አብዮት ብርሀኑ ጋር ቀጣዩን ቆይታ አድርገናል።

ለፋሲል ከነማ ተስፋ ቡድን የሚመደብ ዓመታዊ በጀት ይኖር ይሆን ?

“ለተስፋ ቡድን ተብሎ የሚሰራለት በጀት የለም። ለፋሲል ከነማ ስፖርት ክለብ ተብሎ የሚመደብ በጀት ነው ያለን። ይህም ከከተማ አስተዳደሩ ፣ ከስፖንሰር ሽፕ ሚያገኘው እና ሌሎች ተጨማሪ ስራዎችን ሰርተን የምናገኘው ነው። ከነዚህ ገቢዎች ተነስተን ነው ‘ለተስፋ ቡድኑ ምን ያስፈልገዋል ? ለሴቶች ቡድን ምን ያስፈልገዋል ?’ የሚለው የክለቡን ደረጃ በሚመጥን መልኩ የሚደለደለው።”

በልምምድ ጊዜ የሚመደብላችው የትጥቅ ፣ የምግብ እና የውሃ አቅርቦት በቂ አለመሆኑን ታዳጊዎቹ ገልፀውልናል። ይህ እጥረት ከምን የመጣ ነው?

“ትጥቅ ዘግይቶባቸዋል ፤ እሱ እርግጥ ነው። በአጭር ጊዜ ውስጥ እናስተካክላለን። በዋነኝነት ግን በተስፋ ቡድኑ ውጥ በMRI ምርመራ ምክንያት ታዳጊዎቹ ተሟልተው አልገቡም። ስብስቡ ተሞልቶ ባልተያዘበት ሁኔታ ስለማናቀርብ ነው። ባለው ሁኔታ በክለቡ ተመዝግበው ሙሉ በሙሉ ሲጨርሱ እና ይዘናቸው የምንቀጥላቸውን ተጫዋቾች ስናውቅ ነው የምናቀርበው። በክለቡ የምናውቃቸው 14 ወይም 15 ተጫዋቾች ናቸው። ከዓምናው ወደ ዘንድሮ የቀጠሉት አሰልጣኞች የሚሰጧቸውን ልምምድ እየሰሩ ነው። ተጨማሪ ተጫዋቾችን መልምለን MRI ሲያልፉ 12 ልጆችን ወደ ቡድኑ የምንቀላቅል ይሆናል። ለ26 ታዳጊዎች በክለቡ አቅም መሰረት የሚሟላው ነገር ሁሉ እንዲሞላላቸው እናደርጋለን። ሌላው የምግብ እና የውሃ አገልግሎቶች የቆዩ ችግሮች ሊኖሩ ይችላሉ። ነገር ግን በዚህ ዓመት በጠየቁት ልክ ልምምድ በሚሰሩበት ቀን ሳይገደብ አሰልጣኞች ባቀረቡት ፕሮፖዛል መሰረት ምግብ ቤት ላይ ምግብ እና ውሃ ይቀርብላቸዋል። ያን እየተጠቀሙ ነው ያሉት ። በእርግጥ የልምምድ ሜዳ ላይ ውሃ እየቀረበላቸው አይደለም ፤ ጥያቄው ተገቢ ነው። እሱን ለማስተካከል ያቀድነው አሰራር ስላለ በቅርቡ ይስተካከልላቸዋል።”

ተጫዋቾቹ ካምፕ የላቸውም። ከሙሉ ጎንደር ከተማ የተወጣጡ እንደመሆናቸው ከ600 ብር በላይ በትራንስፖርት ያጠፋሉ። ለነዚህ ታዳጊዎች 900 ብር ክፍያ በቂ ነው ማለት ይቻላል ?

“ክለቡ ላይ የተዳጊ ወጣቶች ብቻ ሳይሆን የደሞዝ ማሻሻያ ጥያቄዎች ብዙ አሉ። በታዳጊዎች በኩል በሌሎች ክለቦች ውስጥ ያለውን ተሞክሮ እያየን ነው። ከኛ ያነሰ ከኛ በላይም የሚከፍሉ ክለቦች አሉ። አማካዩን ወስደን ከኛ ክለብ አቅም እና ደረጃ አንፃር መስተካከል ካለበት እናስተካክለዋለን። ታዳጊዎች ይህንን ጥያቄ አቅርበውልን ጥናቱን ጀምረነዋል። ከከተማው ውጪ የመጡ በክለቡ ደረጃ የሚታወቁ ተጫዋቾች የሉም ካሉም ያመጣቸው ሰው ነው የሚጠየቅባቸው። በክለቡ ደረጃ የማምጣት ዕቅድ የለንም። ‘ቤተሰብ አለኝ ዘመድ አለኝ’ የሚል ሰው ግን መቀላቀል ይችላል ስፖርት ክለቡ የሁላችንም ስለሆነ ።”

የተስፋ ቡድኑ ዋና አሰልጣኝ እና ቡድን መሪ ብቻ ነው ያለው። ምክትል አሰልጣኝ ፣ የግብ ጠባቂ አሰልጣኝ እና የህክምና ባለሙያ የለውም። ይህ ለተጫዋቾቹ ተፈላጊ ዕድገት እንቅፋት አይሆንም ?

“ከዚህ በፊት የነበረውን አሰራር አላውቅም። አሁን ባለው ነገር ግን የአሰልጣኞች አባላትን በተደራጀ መንገድ ማጠናከር እንፈልጋለን። ታዳጊ ቡድን አለን ለማለት ብቻ ሳይሆን ችሎታ ያላቸውን ታዳጊዎች አፈላልጎ በመመልመል ወደ ተስፋ ቡድኑ ውስጥ በመቀላቀል ብድኑ የሚጠናከርበት ሁኔታ እንዲፈጠር ማድረግ እንፈልጋለን። ከተስፋ ቡድኑ በተጨማሪ ከ17 ዓመት በታች እንዲሁም ከዛም በታች ታዳጊዎችን በመያዝ ተመጋጋቢ በሆነ መልኩ ለማዘጋጀት ዕቅድ አዘጋጅን በጀት በመጠበቅ ላይ ነን። ስለዚህ እነዚህን ነገሮች ስናሟላ ከ20 ዓመት በታች ቡድን ላይም የሚሞላ ነገር ነው። ማሟላት ብቻ ሳይሆን አሁን ላይ ያሉት አባላትም መፈተሽ ስላለባቸው የጎደለውን ማሞላት ብቻ ሳይሆን ‘ያለውም ለቦታው ብቁ ነው ወይ ?’ የሚለውን ነገር በደንብ አይተን ማስተካከል እንፈልጋለን።”

ፋሲል ከነማ በኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ተፎካካሪ ከሚባሉ ክለቦች መካከል አንዱ ነው። በዚህ ደረጃ ያለ ክለብ ተስፋ ቡድኑ እንዴት በዚህ መጠን ችግር ውስጥ ተገኘ ? ደጋፊውም ችግሩን እንዲረዳ እና ድጋፍ እንዲያደርግ ምን መልዕክት አለህ ?

“የከተማው ሰው እንደእኔ የተስፋ ቡድኑን ወይም የሴት ቡድኑን ሳይሆን እንደ አጠቃላይ ክለቡን እንዲረዳ ነው የምፈልገው። ምክንያቱም ብቻውን የወጣት ቡድን ወይም የሴቶች ቡድን ተለይቶ ስለሌለ ድጋፍ የሚያደርግ ሰው ክለቡን ይደግፍልን። ክለቡ ነው ሀብቱን በተገቢው መንገድ ለሁሉም ቡድኖች የሚያከፋፍለው። ያ ካልሆነ ለአስተዳደር ያስቸግራል። በአጠቃላይ በዚህ ዓመት ክለቡ ተፎካካሪ ሆኖ እንዲቀጥል እየሰራን ነው። ለምሳሌ በዚህ ዓመት ለክለቡ ይመጥናሉ ያልናቸውን ተጫዋቾች ከመቼውም ጊዜ በላይ እንዲቀላቀሉ አድርገናል። በክለቡም የጎንደር ልጆች ላይ ትኩረት ሰጥተን ለስራት ሞክረናል። ለምሳሌ በዋናው ቡድን ላይ 33% በቢጫ ቴሴራ የጎንደር ልጆች ናቸው ያሉት። ከ25 ውስጥ ደግሞ 25% የጎንደር ልጆች ናቸው። የአካባቢው

ታዳጊዎች በሂደት ወደ ዋናው ቡድን እንዲቀላቀሉ እንሰራለን። እኔ እንኳን ከመጣሁበት ጥቂት ጊዜ አንስቶ ይሄን ነገር ነው በዕቅድ እየሰራን ያለነው። ይህን ለማድረግ ታዳጊ ወጣቶችን በደንብ ማጠናከር አለብን እንጂ ታዳጊዎችን የማያነሳሳ ትኩረት የሚነፍግ አሰራር የለንም። የዕይታ ጉዳይ ነው ሊሆን የሚችለው። ዕይታውን ማስተካከል ነው። የፋይናንስ ችግሮች አሉ ፤ ችግሩ ተለይቶ ለታዳጊ ወጣቶች ብቻ አይደለም። እንደ ክለብ የፋይናንስ ችግር አለ። እነሱን ለማስተካከል እየሰራን ነው። በፋይናንስ ስትጠናክር የክለቡን እና የሌሎች ክለቦች ደረጃ በጠበቀ መንገድ መሆን አለበት። ይህን ካደረግን የሁሉንም ቡድኖቻችንን ችግሮች ደረጃ በደረጃ የምንፈታበት መንገድ ይመጣል። ነገር ግን ሳይፈቱ የቆዩ ሲንከባለሉ የመጡ በርካታ ችግሮች አሉ። እኔ ማስተላለፍ የምፈልገው ታዳጊዎች ያሉትን ችግሮች በትዕግስት ቢያልፉ ለክለቡም ለነሱም የእግርኳስ ዕድገት ጠቃሚ መሆኑን ነው።”


© ሶከር ኢትዮጵያ

error: