ቅድመ ዳሰሳ | ቅዱስ ጊዮርጊስ ከ ስሑል ሽረ

ቅዱስ ጊዮርጊስ በሜዳው ስሑል ሽረን የሚያስተናግድበት ጨዋታን እንደሚከተለው ተመልክተነዋል።

በሜዳቸው በሚያደርጓቸው ጨዋታዎች ከተለመደው የቡድኑ አጨዋወት በተለየ መንገድ ለኳስ ቁጥጥር ብልጫ የተሻለ ቅድምያ ሰጥተው የሊግ ጨዋታዎቻቸው እንደሚያደርጉ ፍንጭ የሰጡት ቅዱስ ጊዮርጊሶች በዚህ ጨዋታም ከባለፉት ጨዋታዎች የተለየ አቀራረብ ይኖራቸዋል ተብሎ ባይጠበቅም ደካማው የስሑል ሽረ የመከላከል አደረጃጀትን ኢላማ አድርገው መግባታቸው አይቀሬ ነው።

ቡድኑ ምንም እንኳ ለኳስ ቁጥጥር አመቺ የሆኑ አማካዮች ቢይዝም በዚህ ጨዋታ ግን ከባለፉት ጨዋታዎች ለየት ባለ መንገድ በቀጥተኛ አጨዋወት የሚገባበት ዕድል የሰፋ ነው።

በባለፉት ጨዋታዎች በጉዳት ምክንያት አጥተዋቸው የነበሩት ጌታነህ ከበደ፣ አሜ መሐመድ፣ ናትናኤል ዘለቀ እና ሳላሀዲን በርጌቾን ከጉዳት መልስ ማግኘቱ መልካም ዜና ሲሆን ፓትሪክ ማታሲ፣ ሳልሀዲን ስዒድ እና ለዓለም ብርሀኑ አሁንም ከጉዳት አላገገሙም።

በበርካታ የሜዳ ውጪ ጉዳዮች ተወጥረው የቆዩት እና ወሳኝ ተሰላፊዎቻቸውን በደሞዝ ምክንያት ያጡት ስሑል ሽረዎች በነገው ጨዋታ ነጥብ ማግኘት ካልቻሉ ገና በሊጉ ጅማሬ ላይ አጣብቂኝ ውስጥ ስለሚገቡ ከወሳኙ ጨዋታ ነጥብ ይዞ መመለስ የግድ ይላቸዋል።

ባለፈው ሳምንት ከወልዋሎ ጋር ባደረጉት ጨዋታ ጨምሮ በሌሎችም ሊጉ ጨዋታዎች የተጋጣሚን የማጥቃት አጨዋወት ለመከላከል ሲቸገሩ የተስተዋሉት ሽረዎች በዚህ ጨዋታ ይህን ችግር ቀርፎ መግባት የግድ ይላቸዋል። በዚህም ጫና ፈጥሮ እንደሚጫወት የሚጠበቀው ቅዱስ ጊዮርጊስን በተደራጀ መከላከል ለመግታት አልመው ወደ ሜዳ ይገባሉ ተብሎ ይጠበቃል።

ከዚህ በተጨማሪም ወሳኝ አጥቂዎቻቸው በደሞዝ ምክንያት በጨዋታው የማያገኙ በመሆኑ እስካሁን ጎል ያልተቆጠረበት የፈረሰኞቹ የኋላ መስመርን ለመስበር እንደሚቸገሩ ሲገመት በነገው ጨዋታ በአዲስ የአጥቂዎች ጥምረት ሲቀርቡ ከተለመደው የመስመር አጨዋወት ወጣ ያለ አቀራረብ ይኖረዋል ተብሎ አይጠበቅም።

ቡድኑ በነገው ጨዋታ ሳሊፍ ፎፋና፣ ያስር ሙገርዋ፣ አክሊሉ ዋለልኝ እና ዲድዬ ለብሪን በደሞዝ ምክንያት ሲያጣ ቋሚ ግብ ጠባቂያቸው ምንተስኖት አሎም በጉዳት አይሰለፍም።

እርስ በርስ ግንኙነት

– ሁለቱ ቡድኖች በሊጉ ለመጀመርያ ጊዜ የተገናኙት ዐምና ሲሆን አዲስ አበባ ላይ ቅዱስ ጊዮርጊስ 4-0 ሲያሸንፍ ሽረ ላይ 0-0 መለያየታቸው ይታወሳል።

ግምታዊ አሰላለፍ

ቅዱስ ጊዮርጊስ (4-3-3)

ባህሩ ነጋሽ

ዓብዱልከሪም መሐመድ – ፍሪምፖንግ ሜንሱ – ምንተስኖት አዳነ – ሄኖክ አዱኛ

ያብስራ ተስፋዬ – ሙሉዓለም መስፍን – ሀይደር ሸረፋ

አቡበከር ሳኒ – ዛቦ ቴጉይ – አቤል ያለው

ስሑል ሽረ (4-2-3-1)

ወንድወሰን አሸናፊ

ዓብዱሰላም አማን – ዮናስ ግርማይ – አዳም ማሳላቺ – ረመዳን የሱፍ

ሙሉዓለም ረጋሳ – ነፃነት ገብረመድኅን

መድኃኔ ብርኃኔ – ኃይለአብ ኃይለሥላሴ – ዓብዱለጢፍ መሐመድ

ብሩክ ሐድሽ


© ሶከር ኢትዮጵያ