ሪፖርት | በርካታ ቢጫ ካርዶች በተመዘዙበት ጨዋታ ዐፄዎቹ ነብሮቹን አሸንፈዋል

በአራተኛው ሳምንት የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ውሎ ፋሲል ከነማ በሜዳው ሀዲያ ሆሳዕናን አስተናግዶ 3-0 በሆነ ውጤት ማሸነፍ ችሏል።

ሁለቱም ክለቦች ከሽንፈት መልስ በተገናኙበት ጨዋታ ፋሲል ከነማ በወልቂጤ 1-0 ከተሸነፈው ስብስብ በጉዳት ምክንያት ያሬድ ባየን በዓለምብርሀን ይግዛው በመተካት የተከላካይ ስፍራ ላይ የቦታ ሽግሽግ በማድረግ ወደ ሜዳ ገብቷል። በእንግዳዎቹ ሀዲያ ሆሳዕናዎች በኩል ደግሞ ወደ ድሬድዋ አቅንቶ በድሬድዋ ከተማ 1-0 ከተሸነፈው ስብስብ በርከታ ለውጦች ተደርጓል። በዚህም ግብ ጠባቂው ታሪክ ጌትነትን ጨምሮ በሀይሉ ተሻገር፣ መሀመድ ናስር እና ፍራኦል መንግስቱ አርፈው አቤር ኦቮኖ፣ ቢስማርክ ኦፖንግ፣ ሱራፌል ዳንኤል እና አብዱሰመድ ዓሊ የመጀመሪያ ተሰላፊ ሆነዋል።

በጨዋታው መጀመሪያ ኳስን በፋሲል ከነማ ግብ ክልል በማንሸራሸር ጥሩ አጀማመር ያደረጉት ሀዲያ ሆሳዕናዎች በተደጋጋሚ ወደግብ ቢደርሱም ኳሶቹ ኢላማቸውን መጠበቅ ያልቻሉ አልያም ግብ ጠባቂውን የፈተኑ አልነበሩም። በባለሜዳዎቹ በኩልም አልፎ አልፎ ተቃራኒ ግብ ክልል ውስጥ በመግባት አጋጣሚ ይፈጥሩ ነበር። 10ኛው ደቂቃ ላይ በግራ መስመር ሱራፌል ዳኛቸው ራሱ ላይ በተሰራ ጥፋት የተገኘውን የቅጣት ምት ወደ ግብ አክርሮ ሞክሮ ግብ ጠባቂ ያዳነበት ጥሩ የሚባል ሙከራ ነበር። ከአንድ ደቂቃ በኋላ ግብ ጠባቂ የመለሰውን ኳስ ሽመክት ጉግሳ ከቀኝ መስመር ወደ ሳጥን ሲያሻማ ኦሲ ማውሊ ኳሱ መሬት ሳይወርድ በመምታት ድንቅ ግብ አስቆጥሮ ዐፄዎቹን መሪ ማድረግ ችሏል።

የማጥቃት እንቅሰቃሴው በተቀዛቀዘው ፋሲል ከነማ በኩል በመጀመሪያው አጋማሽ መገባደጃ ጭማሪ ደቂቃ ላይ ሱራፌል ዳኛቸው የግብ ጠባቂውን መውጣት ተከትሎ ወደ ግብ አክርሮ የመታው ኳስ ሌላ ቡድኑ ወደ ግብ የቀረበበት አጋጣሚ ነበር።

ሀድያ ሆሳዕናዎች በመጀመሪያው አጋማሽ በርካታ ሙከራዎችን መድረግ ቢችሉም የፋሲልን ግብ መድፈር አልቻሉም። 3ኛው ደቂቃ ላይ ቢስማርክ ኦፖንግ በግራ መስመር ወደ ግብ ክልል የሞከረው ኳስ ኢላማውን ያልጠበቀ ሲሆን 6ኛው ደቂቃ ላይ ከቅጣት ምት አፈወርቅ ኃይሉ የመታው እና በግብ ጠባቂው የመለሰበት ሌላው ሙከራቸው ነበር።

ንክኪ በበዛበት የሁለቱ ቡድኖች አጨዋወት አይን የሆኑ ቦታዎች ላይ ሀዲያዎች ጥሩ ጥሩ የተባሉ ቅጣት ምቶች ቢያገኙም መጠቀም አልቻሉም። በ18ኛው ደቂቃ ይሁን እንደሻው ራሱ ላይ በተሰራ ጥፋት የተገኘውን የቅጣት ምት ወደ ግብ ሞክሮ ግብጠባቂው ያወጣበት መከራ በዚህ በኩል ተጠቃሽ ነው። በጨዋታ እንቅስቃሴ ከተደረጉ ሌሎች ሙከራዎች መካከል ቢስማርክ አፒያ በግራ በኩል ይዞት የገባውን ኳስ ወደ ግብ አክርሮ ሞትቶት የግቡን ቋሚ ተጠግቶ የወጣው በመጀመሪያው አጋማሽ በነብሮቹ በኩል የሚጠቀስ ከባድ ሙከራ ነበር።

ሁለተኛው አጋማሽ ከመጀመሪያው አንፃር ውጥረት የተሞላበት፣ ከ4ኛ እና ከመሀል ዳኛው ጋር በርካታ ሰጣ ገባዎች የተፈጠሩበት እንዲሁም ተጠባባቂ ወንበር ላይ ያሉ ተጫዋቾች ካርድ እስከመመልከት የደረሱበት ነበር። በአጋማሹ ጥሩ የተንቀሳቀሱት ባለሜዳዎቹ 53ኛው ደቂቃ ላይ ከግብ ጠባቂ የተፋውን ኳስ ሙጂብ ቃሲም አግኝቶት ወደ ግብ በሞከረበት አጋጣሚ ዕድሎችን መፍጠር ቀጥለዋል። ቢስማርክ አፒያ 48ኛው ደቂቃ ከማዕዘን የተሻማ ኳስ ከተከላካዮች ተገጭቶ ሲመለስ በጭንቅላት የገጨው ኳስ ግብጠባቂ ያዳነበት በሁለተኛው አጋማሽ የሚጠቀስ የእንግዶቹ ሙከራ ነበር። ያም ቢሆን ኢላማውን የጠበቀ ኳስ ለመሞከር የተቸገሩት ነብሮቹ ከመጀመሪያው አጋማሽ የወረደ እንቅስቃሴ አድርገዋል።

በቀጣዮቹ ደቂቃዎችም የተሻለ ወደ ግብ መድረስ የጀመሩት ዐፄዎቹ በተደጋጋሚ ወደ ሳጥን ለመግባት በሚያደርጉት ጥረት በሚሰሩባቸው ጥፋቶች የሚገኙትን በርካታ የቅጣት ምት አጋጣሚዎች ሱራፌል ዳኛቸው በቀጥታ ቢሞክርም አልተሳካለትም። ሆኖም 70ኛው ደቂቃ ላይ ሙጂብ ቃሲም ወደ ሳጥን ውስጥ ሲገባ በተሰራበት ጥፋት ምክንያት የተሰጠውን ፍፁም ቅጣት ምት ራሱ አስቆጥሮ የቡድኑን መሪነት ወደ ሁለት ከፍ አድርጓል። በዚህ አጋጣሚ የተሰጠው የፍፁም ቅጣት ምትን በመቃወም ከዳኛው ጋር ሰጣ ገባ የገባው ሱራፌል ዳንኤል በቀይ ካርድ ከሜዳ ተሰናብቷል። ከሱራፌል በተጨማሪም ሌሎች የሆሳዕና ተጫዋቾች በተደጋጋሚ ከዳኛ ጋር ሰጣ ገባ ውስጥ በመግባት በርካታ ካርዶች ተመልክተዋል።

74ኛው ደቂቃ ላይ ሽመክት ጉግሳ ከኢዙ አዙካ የተሻገረለትን ኳስ ወደ ግብ አክርሮ መትቶ ግብ ጠባቂ የመለሰበት አጋጣሚ ሌላኛው የዐፄዎቹ ከባድ ሙከራ ነበር። የተጫዋች ጉዳት ቡድኑን ያሳሳባቸው አሰልጣኝ ሥዩም ከበደ በርካታ ተጫዋቾችን ከሚናቸው ውጪ ያጫወቱ ሲሆን በመጨረሻ ደቂቃዎች ቀይረው ያስገቡት በዛብህ መለዮም ግብ አስቆጥሮላቸዋል። 90ኛው ደቂቃ ላይ ከግራ መስመር አምሳሉ ጥላሁን የተሻማውን ኳስ ነበር በዛብህ መለዮ በጭንቅላት በመግጨት ያስቆጠረው። ተጫዋቹ ግብ ካስቆጠረ በኋላ ያደገበት ክለብ ላይ ደስታውን ባለመግለፅ ያለውን ክብር አሳይቷል። ጨዋታውም በፋሲል ከነማ 3-0 አሸናፊነት ተጠናቋል።

በጨዋታው ሆሳዕና ተጫዋቾች የእለቱ ዳኛ ተፈሪ አለባቸው በሚወስናቸው ውሳኔዎች ላይ በተደጋጋሚ እሰጥ እገባ ሲፈጥሩ የተስተዋለ ሲሆን በሒደቱም 8 ቢጫ እና አንድ ቀይ ካርድ ተመዞባቸዋል።

ውጤቱን ተከትሎ ፋሲል ከነማ በደረጃ ሰንጠረዡ በሰባት ነጥብ ሁለተኛ ደረጃ ላይ ሲቀመጥ በአንፃሩ ሀድያ ሆሳዕና በአንድ ነጥብ 16ኛ ደረጃ ላይ ይገኛል።


© ሶከር ኢትዮጵያ