የአሰልጣኞች አስተያየት | ፋሲል ከነማ 3-0 ሀዲያ ሆሳዕና 

በአራተኛው ሳምንት የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ጎንደር ላይ ሀዲያ ሆሳዕናን ያስተናገደው ፋሲል ከነማ 3-0 ካሸነፈበት ጨዋታ በኋላ የሁለቱ ቡድን አሰልጣኞች አስተያየታቸውን እንደሚከተለው ሰጥተዋል።

” ጨዋታው በቀጥታ ስለታየ ሰው ሁሉ ሊፈርድ ይችላል፤ ዳኛው ምኑ ላይ እንደተሳሳተ አልገባኝም” የፋሲል ከነማ አሰልጣኝ ሥዩም ከበደ

ስለ ጨዋታው

በአጠቃላይ እንደምታየው የቡድኑ ቅንጅት በጣም ጥሩ ነው። ተጋጣሚዎች ደግሞ አቅደውት የሚመጡት ለመከላከል ነው። የኛ ተጫዋቾች በነፃነት እንዳይጫወቱ ለማድረግ ሰው በሰው ለመያዝ እንደሚያስቡ እናውቃለን። በመጀመሪያው አጋማሽ እንደተመለከትነው ኳስን መስርተን ለመሄድ በምንሞክርበት ሰዓት መሀል ላይ እያጨናገፉብን ነበር፤ በጣም ኃይል ይቀላቅሉም ነበር። በሚፈልጉት መልክ ነገሮችን ለማበላሸት ሞክረዋል። እኛ ደግሞ ፕላን ቢ አድርገን በያዝነው እቅድ ሰብረን ለመግባት ወይም በመልሶ ማጥቃት ለማግባት ሙከራ አድርገን እሱም ተሳክቶልን ግብ አስቆጥረናል።

በእረፍት ሰዓት ችግራች በምን ዙሪያ እንደሆነ ተነጋግረናል። በተለይ የመሃል ሜዳ ተጫዋቾች ችግራቸው በማስተካከል ተጋጣሚ ላይ ከፍተኛ ጫና መፍጠር እንዲሁም ማስከፈት ነበረባቸው ። ከመጀመሪያው አጋማሽ ሁለተኛው አጋማሽ ቀሎናል። ስለዚህ ያገኘነው ውጤት ይገባናል ብዬ ነው የማስበው።

ከቀይ ካርዱ በኋላ ተጨማሪ ጎል ማግባት አይቻልም ነበር?

ይቻል ነበር፤ ግን የጨዋታው ድባብ ከባድ ሆነ። በሆሳዕና በኩል ደግሞ ትንሽ ስሜታዊ ሆኑ። ያ ጨዋታ ደግሞ ሁላችንም ለጉዳት ይዳርገናል። ሶስት ካገባን በኋላ ቀዝቀዝ የማለት ነገር ፈልገን ነበር። አጠቃለይ ግን በፈለግነው መልክ ሄዶልናል ማለት እችላለሁ ። 

ዳኝነት

ጨዋታው የቀጥታ ስርጭት ሽፋን አግኝቷል። ያየው ሰው ሁሉ ሊፈርድ ይችላል። ዳኛው ምኑ ላይ እንደ ተሳሳተ አልገባኝም። በመጀመሪያው አጋማሽ ጥሩ የመጡበት ጊዜ አለ። እኛም ደግሞ በሁለተኛው አጋማሽ አሻሽለን የመጣንበት ሂደት አለ።

”ጨዋታው በቴሌቪዥን ስለተላለፈ ዳኝነቱን ሁሉም የሚፈርደው ነው” የሀዲያ ሆሳዕና ምክትል አሰልጣኝ ኢዘዲን አብደላ

ስለ ጨዋታው

የጨዋታው እንቅስቃሴ እንደተመለከታችሁት ነው፤ ሁለቱም ቡድን ውጤት ይዞ ለመውጣት የአቅሙን ተጫውቷል። ግን ይሄ ነው በማይባል ምክንያት ውጤቱን አጥተናል። ይሄ ሊሻሻል የማይችል ምክንያት ስለሆነ መቀበል ነው እንግዲህ። በተለይ ከዳኝነት ጋር በተያያዘ አሳሳቢ ነው። ወደፊትም በዳኝነት ዙሪያ ሊስተካከል የሚገባው ብዙ ነገር አለ። ዳኝነቱ ካልተስተካከለ ምንም ብትለፋ ውጤቱ ላይ ትልቅ ተፅዕኖ አለው። አሁንም በደንብ መፈተሽ እና መስተካከል ያለበት ነገር አለ ።

ዳኝነቱ ላይ በግልፅ ተበደልን የምትሉት ነገር አለ?

ያው በቴሌቪዥን የተላለፈ ስለሆነ ሁሉም የሚፈርደው ነው የሚሆነው፤ ዳኝነቱ ትክክል አይደለም። ዳኝነት ፍትሀዊ መሆን አለበት። “ባለሜዳ” – “ከሜዳ ውጭ የሚጫወት ቡድን” መባል የለበትም። ዳኛ ስራውን ሊሰራ ነው መግባት ያለበት። ከዚህ ውጭ ምንም ምለው ነገር የለም።


© ሶከር ኢትዮጵያ