“የተሰጠኝን ዕድል በአግባቡ እየተጠቀምኩ ነው” የጅማ አባ ጅፋር ግብጠባቂ ሰዒድ ሀብታሙ

ከፍተኛ ሊግ እየተሳተፈ ከሚገኘው አርባምንጭ ከተማ ነው በዘንድሮ የውድድር ዓመት አባ ጅፋሮችን የተቀላቀለው። በአራቱም የፕሪምየር ሊግ ጨዋታዎች በቋሚነት የጅማ አባ ጅፋር የግብ ክልልን እየጠበቀ ይገኛል። እስካሁን በሊጉ በሲዳማ ቡና ብቻ ከተቆጠሩበት ሁለት ጎሎች ውጪ መረቡን አላስደፈረም። አባ ጅፋር ከሜዳው ውጭ በተከታታይ አራት ጨዋታ ከማድረጉ አኳያ እና ቡድኑ ካለበት ውስብስብ ችግር የተነሳ እስካሁን ሙሉ ሦስት ነጥብ አያገኝ እንጂ በግሉ ለክለቡ ጥሩ አገልግሎት እየሰጠ ይገኛል።


የቡድኑ አንደኛ እና ሁለተኛ ግብጠባቂዎች በተለያዩ ምክንያቶች አለመጫወታቸውን ተከትሎ የመጀመርያ አሰላለፍ ውስጥ በመግባት አቅሙን በማሳየት ላይ የሚገኘው የጅማ አባ ጅፋር ግብጠባቂ ሰዒድ ሀብታሙ በወቅታዊ አቋሙ ዙርያ ከሶከር ኢትዮጵያ ጋር አጭር ቆይታ አድርጓል፤ እንዲህ አቅርበነዋል።

ጅማ አባ ጅፋርን ስትቀላቀል እንዲህ የመሰለፍ እድል አገኛለው ብለህ አስበህ ነበር ?

በጭራሽ በወቅቱ በከፍተኛ ሊግ እየተሳተፈ ከሚገኘው ቡድን በፕሪሚየምየር ሊግ ወደሚሳተፍ ቡድን ስመጣ ቅድሚያ አስቤ የመጣሁት ዋናው ነገር ልምድ ለማግኘት ነው። ምክንያቱም የውጪ ዜጋው ግብጠባቂ መሐመድ ሙንታሪ በአዳማ ሲቲ ካፕ ላይ የተሻለ አቅም እንዳለው አሳይቷል። እንዲሁም ዘሪሁን ታደለም በትልቅ ክለብ እና በብሔራዊ ቡድን ደረጃ የተጫወተ ልምድ ያለው ግብጠባቂ ነው። ሁለቱም ከእኔ በልምድ የተሻሉ በመሆናቸው እንዲህ በፍጥነት እድል አገኛለው ብዬ አላሰብኩም።

በአርባምንጭ ከተማ እያለህ የመሰለፍ ዕድሎችን አግኝተሀል?

አዎ ተጫውቻለው። በቁጥር ከሰባት እስከ ዘጠኝ ጨዋታዎችን ተሰልፌያለው። ሆኖም ወጣቱ ግብጠባቂ ፅዮን መርድ የነበረ በመሆኑ እርሱ ከእኔ በተሻለ ብዙ ጨዋታዎች ላይ ተሰልፏል። ያም ቢሆን እርሱ ሲጎዳ ባገኘሁት ዕድል እና በተጫወትኩበት ጊዜ የምችለውን ለማድረግ ጥሩ እንቀሳቀስ ነበር።

ከፕሪምየር ሊጉ ጨዋታ አስቀድሞ በአባ ጅፋር የትኛውም ጨዋታ ላይ የመጀመርያ አሰላለፍ ውስጥ አለመግባትህ በሊጉ ላይ አልተቸገርክም?

ምንም ጥያቄ የለውም ከብዶኝ ነበር። እንደ አጋጣሚ ነው የሁለቱም ግብጠባቂዎች አለመኖር እኔን ወደ መጀመርያ አሰላለፍ እንድገባ ያደረገኝ። ያው የግብጠባቂ አሰልጣኜ መሐመድ ለእያንዳንዱ ጨዋታ ምን ማድረግ እንዳለብኝ በሚገባ ያዘጋጀኝ ስለነበር ከባዱን ነገር አቅልሎልኛል። ቁጭ ብለህ ምንም ሳትጫወት በቀጥታ በአራት ተከታታይ ጨዋታ መጫወት በጣም ከባድ ነው።

የወልዋሎን የተከታታይ አሸናፊነት ጉዞን ነጥብ ተጋርቶ እንዲወጣ በማድረግ የማሸነፍ ጉዞውን እንዲገታ በማድረግ በጨዋታው ጥሩ ላይ ተንቀሳቅሰሀል። እንዴት ነበር ጨዋታው?

ወልዋሎዎች እስካሁን ባለው ጨዋታ ጎል እያስቆጠረ፣ እያሸነፈ የመጣ ቡድን ነው። በዚህም ምክንያት እኛን ሊፈትኑን እንደሚችሉ አስበናል። እኔ በግሌ ምን ማድረግ እንዳለብኝ ተዘጋጅቼ ነው ወደ ሜዳ የገባሁት። ከፈጣሪ ጋር መረቤን ሳላስደፍር ጥሩ ተንቀሳቅሼ ወጥቻለው።

ሦስተኛ ግብጠባቂ ሆነህ በመጣህበት ክለብ እንዲህ ያለ አቋም ለማሳየት በአዕምሮ ረገድ የሰራህው ስራ አለ?

እውነት ለመናገር ብዙም አላሰብኩም ነበር። ከእኔ የተሻለ ልምድ ያላቸው ግብጠባቂዎች ነበሩ። እንድ አጋጣሚ እኔ እንደምጫወት ሲነገርኝ የተወሰነ መደናገር ነበረብኝ። ያም ቢሆን ይህን እድል በማግኘቴ በጣም ደሰተኛ ነኝ። አሰልጣኜ መሐመድንም በጣም ማመስገን እፈልጋለው። ኃላፊነት ወስዶ ከከፍተኛ ሊግ ነው የመጣሁት፤ ለሊጉ አዲስ ነኝ። በእኔ አምኖ ብዙ ሲለፋ ሲያዘጋጀኝ ቆይቷል። ይህ የእርሱን በራስ መተማመን ያሳያል። በእኔ ላይ ደግሞ ከፍተኛ በራስ መተማመንን ጨምሯል። በእኔ በጣም ለፍቷል፤ ፈጣሪም አላሳፈረኝም፤ እስካሁን ያለው ነገር ጥሩ ነው።

የአባ ጅፋርን የሊጉ ጉዞ እስካሁን እንዴት አየህው?

ቡድናችን በወጣት ተጫዋቾች የተገነባ ነው። ሜዳ ውስጥ ስንገባ ሁላችንም አሰልጣኞቻችን የሚሰጡንን ነገር ለመተግበር በጣም ፍላጎት ያለን። እስካሁን በሦስት ጨዋታ አቻ በአንድ ጨዋታ ሽንፈት ብናስተናግድም ከሜዳችን ውጭ እንደመጫወታችን ብዙ የሚያስከፋ ውጤት አይደለም። በቀጣይ በሜዳችን መጫወት ስንጀምር ከደጋፊዎቻችን ጋር በመሆን ወደ አሸናፊነት በመምጣት በሊጉ የተሻለ ደረጃ ይዘን እንጨርሳለን።

የተሰጠህን አጋጣሚ በመጠቀም ጥሩ ጅማሮን እያደረግክ ነው። ስለ ቀጣይ ምን ታስባለህ?

በመጀመርያ ፈጣሪ ይመስገን፤ የተሰጠኝን እድል እየተጠቀምኩ ነው። አንድ ተጫዋች ደግሞ የመጫወት ዕድል ሲሰጠው ዕድሉን ለመጠቀም ጥሩ መንቀሳቀስ እና የተሻለ ሥራ ለመስራት ራሱን በአዕምሮ ማዘጋጀት ይኖርበታል። ፈጣሪም ረድቶኝ ጥሩ ነገር እያሳየው እገኛለው። ወጣት ግብጠባቂ ነኝ፤ ገና ከዚህ በተሻለ ብዙ ነገር ነው ማድረግ የምፈልገው። በብሔራዊ ቡድን ደረጃም ሀገሬን ማገልገልን አስባለው።


© ሶከር ኢትዮጵያ