በፕሪምየር ሊግ ክለቦችና በዳሽን አሞሌ መካከል ስለተፈፀመው የትኬት ሽያጭ ስምምነት ማብራሪያ ተሰጠ

አሞሌ በተሰኘው ዘመናዊ የባንኪንግ አገልግሎት የስታዲየም የመግቢያ ትኬቶች ለመሸጥ ከስምምነት በደረሱ የፕሪምየር ሊግ ክለቦች እና በዳሽን አሞሌ መካከል ስለተደረገው ስምምነትና በእስካሁኑ ሂደት ስላጋጠሙ ተግዳሮቶች ዛሬ ከሰዓት በዳሽን ባንክ ዋና መስሪያ ቤት ጋዜጣዊ መግለጫ ተሰጥቷል።

በጋዜጣዊ መግለጫው ላይ አቶ ካሴ እሸቱ (የዳሽን ባንክ ኦልተርኔት ቻናል ተጠባባቂ ዳይሬክተር)፣ አቶ ሳምሶን ጌቱ (የሞኔታ ቴክኖሎጂ አ.ማ ተወካይ)ን ጨምሮ የኢትዮጵያ ቡና እና የቅዱስ ጊዮርጊስ ክለብ ተወካዮች በጋራ በመሆን ሰጥተዋል።

ሞኔታ ቴክኖሎጂ አ.ማ ከዳሽን ባንክ በመሆን አሞሌ በተሰኘው ዘመናዊ የክፍያ ስርዓት በ14ኛው የአዲስ አበባ ከተማ ዋንጫ ላይ የቀደመውን የጨዋታ ቀን የእጅ በእጅ የትኬት ሽያጭ በማስቀረት ዘመናዊ የኤሌክትኖኒክስ የትኬት ሽያጭን የጀመረው ተቋሙ በአዲስ አበባ ከተማ ዋንጫ የተገኙትን ልምዶችና አዎንታዊ ምላሽን መነሻ በማድረግ በኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ተካፋይ ከሆኑ አራት ክለቦች ማለትም ኢትዮጵያ ቡና፣ ቅዱስ ጊዮርጊስ፣ ሰበታ ከተማ እና እንዲሁም በቅርቡ ከጅማ አባጅፋር ጋር የትኬት ሽያጩ በአሞሌ በኩል እንዲፈፀሙ ስምምነት መፈፀሙ ይታወሳል።

በአዲስ አበባ ከተማ ዋንጫ የትኬት ሽያጮቹ አሞሌን በመጠቀም በመዲናይቱ በሚገኙ 185 ቅርንጫፎች ጨምሮ በመላ ሀገሪቱ ከ400 በላይ በሚሆኑ የባንኩ ቅርንጫፎች ሲከናወኑ መቆየታቸው ይታወቃል። በመግለጫው ላይ በአዲስ አበባ ከተማ ዋንጫ ላይ የትኬት ሽያጩ በአሞሌ በኩል መከወኑ የደጋፊዎች እንግልትንና በጨዋታ ቀን ይደርስ የነበረው መጨናነቅና የደህነነት ስጋት ከማስቀረት በዘለለ ይደርሱ የነበሩትን የገንዘብ ጉድለቶችንም ስለማስቀረቱ በስፋት ተነስቷል።

በዚሁ ዘመናዊ አሰራር ትኬት ሽያጭ ሲደረግ በቀጥታ ለየክለቦቹ የሂሳብ ማሳወቂያ የሚደርሳቸው ሲሆን በጨዋታው ማግስትም ለክለቦቹ አጠቃላይ በትኬት የሽያጭ የተሰበሰበው ገንዘብ ገቢ እንደሚደረግላቸው ለማወቅ ተችሏል።

በመግለጫው ላይ ኢትዮጵያ ቡናን በመወከል የተገኙት በድጋሚ ወደ ኢትዮጵያ ቡና ስራ አስኪያጅነት የተመለሱት አቶ ገዛኸኝ ወልዴ በሊጉ በሜዳቸው ባደረጓቸው ሁለት ጨዋታዎች ላይ በትኬት አሻሻጥና የጨዋታ ቀን ስላጋጠሙ ተግዳሮቶች ማብራሪያ ሰጥተዋል። በማብራሪያቸውም በተለይ ባሳለፍነው ሳምንት ከሀዋሳ ከተማ ጋር ባደረጉት ጨዋታ በእለቱ ከፍተኛ ቁጥር ያለው ደጋፊ ወደ ስታዲየም በመምጣቱ ጋር ተያይዞ ባጋጠሙ ከአቅም በላይ በሆኑ ችግሮች የተነሳ የተወሰነ ደጋፊዎች የትኬት ቁጥጥር ሳይደረግበት በነፃ እንዲገቡ ስለመፈቀዱም ገልፀዋል።

አቶ ገዛኸኝ የገጠሙ ችግሮችን በተለያየ መልኩ ለማስቀመጥ ሞክረዋል። በዚህም መሠረት ካነሷቸው ችግሮች መካከል አንኳሮቹ፡-

-በዳሽን ባንኮች ቅርጫፎች በኩል ከሲስተምና ኔትወርክ ጋር በተያያዙ ችግሮች አገልግሎት ያለመስጠት

-በባንኩ ቅርንጫፎች ለተመሳሳይ ጥያቄዎች የተለያዩ ምላሾችን መስጠት በተለይም አመታዊ ትኬትና መሰል ጉዳዮችን በተመለከተ

-ከባንክ ውጭ ያሉ ሌሎች የትኬት መግዣ አማራጮች በስፋት ያለማስተዋወቅ

-በስታደየም ዙርያ ያሉ ባንኮች በጨዋታ ቀን ሙሉ ለሙሉ ሽያጭ ማቆማቸው

– በፋይናስ ተቋማት አካባቢ ባለተፈቀደ መልኩ በቁጥር በርከት ብሎ የክለብ መዝሙር እየዘመሩ ወደ ባንኮች መጥተው ትኬት ለመግዛት መሞከር

– ትኬቶችን ከጨዋታው በፊት ባሉት ቀናት መግዛት እየቻለ የጨዋታ ቀናት ሲቃረቡ ለመግዛት ማሰብ (ለማሳያነት ቡና ከሀዋሳ ባሳለፍነው ቅዳሜ ለተደረገው ጨዋታ ትኬቱ ከሰኞ ጀምሮ ለገበያ ቢውልም ሰኞና ማክሰኞ የተገዛው ትኬት 105 እና 305 ብቻ ሲሆን በአንፃሩ አርብ 5800 እንዲሁም ቅዳሜ 9000 መሆኑን ገልፀዋል።)

– በጨዋታ ቀን የፀጥታ አስከባሪዎች አስቀድመው ቢገኙም ትኬት ተቆጣጣሪዎችና የክለብ አስተባባሪዎች በወቅቱ በስፍራው ያለመገኘት ይገኙበታል።

አቶ ገዛኸኝ አይይዘውም በጨዋታ ቀን እሁድን ሳይጨምር እስከ 6 ሰዓት ባለው ወቅት ብቻ በስታዲየም አቅራቢያ የሚገኙ የዳሽን ባንክ ቅርንጫፎች የትኬት ሽያጮች እንዲካሄዱ ከመግባባት ስለመደረሱና በቀጣይ በጨዋታ ቀን ምንም አይነት የትኬት ሽያጭ እንደማይኖር ገልፀዋል። በተጨማሪም ደጋፊው ከባንኮች በተጨማሪ በቀላሉ በፓስታ ቤት፣ በተለያዩ መተግበሪያዎች ጭምር ትኬት ሊገዛባቸው በሚችልባቸው አማራጮች ዙሪያ ሰፊ የግንዛቤ ማስጨበጫ ሥራዎች ለመሥራት ስለመታቀዱ ገልፀዋል።

ቅዱስ ጊዮርጊስን በመወከል በመግለጫው ላይ የተገኙት የክለቡ የህዝብ ግንኙነት ኃላፊ አቶ አየነው አዲሱ በበኩላቸው አዲሱ አካሄድ የደጋፊዎችን እንግልት የሚያስቀር መሆኑን ገልፀው ክለባቸው ደጋፊዎቹ እንዲገላቱ በምንም አይነት ሁኔታ እንደማይፈልግ ገልፀዋል። አይይዘውም የኦንላይን ሲስተም እክል በሚገጥመው ወቅት ሊያገለግሉ የሚችሉ አማራጮችን ቢጤኑ እንዲሁም ትኬት ለመግዛት ደጋፊዎች ወደ ባንክ ሲሄዱ አካውንት እንዲከፍቱ የሚገደዱባቸው ቅርንጫፎች ከመሰል ድርጊቶች እንዲታቀቡ ሊደረጉ በሚችሉባቸው መንገዶች ላይ ስራዎች መሰራት እንደሚኖርባቸው ጠቁመዋል።

በመርሃግብሩ ላይ የአሞሌ ቴክኖሎጂን የሚያቀርበው ሞኒታ ቴክኖሎጂ አ.ማ ተወካይ የሆኑት አቶ ሳምሶን የዘመናዊ ክፍያ ስርዓት አገልግሎት አንዱና ዋነኛው ጥቅሙ ደንበኞች በፈለገበት ሁኔታ ውስጥና ሰአት ውስጥ አገልግሎት እንዲያገኝ ማስቻል መሆኑን ገልፀው በቀጣይ ደጋፊዎች በአንድ አጋጣሚ ብቻ ወደ ባንክ በማምራት በስልክ ቁጥራቸው የኢ ዋሌት አካውንት ከ5 ደቂቃ ባነሰ ጊዜ ውስጥ በመክፈት በኢ-ዋሌታቸው ገንዘብ በማስቀመጥ ቀጣይ የትኬት ግዥዎችን ባሻቸው ቦታ ሆነው በስልካቸው መፈፀም ለማስቻል ዝግጅታቸውን ስለማጠናቀቃቸው ገልፀዋል።

ከባንክ በተጨማሪ ትኬት መግዛት የሚፈልጉ ሰዎች በኢትዮጵያ ፖስታ አገልግሎት ቅርንጫፎች
በኩል እንዲሁም በተለያዩ መተግበሪያዎች (ሜዳ ቻት፣ ሸክላ፣ ቪ-ሞል፣ ቴሌግራም) ላይ መግዛት የሚችሉበት አማራጮች ስለመመቻቸታቸው ገልፀዋል። በተጨማሪም በ6294 ላይ በመደወል ከትኬት ሽያጭ ጋር ለሚገጥም ችግር መረጃ ማግኘት እንደሚችሉም አስታውቀዋል።


© ሶከር ኢትዮጵያ