የፕሪምየር ሊግ ስድስተኛ ሳምንት ዐቢይ ጉዳዮች

የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ስድስተኛ ሳምንት ጨዋታዎች በሳምንቱ መጨረሻ መከናወናቸው ይታወሳል። ሳምንቱን ተንተርሰው የሚነሱ ዋና ዋና ጉዳዮችንም እንደሚከተለው ተመልክተናቸዋል።

1. ክለብ ትኩረት

የፋሲል የሜዳ ጥንካሬ

ፋሲል ከነማ በሜዳው በሚያደርጋቸው ላይ ጨዋታዎች ተጋጣሚዎቹ ሦስት ነጥቦች ማሳካት ቀርቶ በጠባብ ጎል ልዩነት ሽንፈት አስተናግዶ መመለስ አዳጋች እየሆነባቸው መጥቷል። ባሳለፍነው ቅዳሜ ባህር ዳር ከተማን 3-0 የረታው የሥዩም ከበደ ስብስብ የ2012 ውድድር ከተጀመረ ወዲህ በሜዳው በ3 ጨዋታዎች 11 ጎሎች አስቆጥሮ ምንም ያልተቆጠረበት ሲሆን በአጠቃላይ ከግንቦት 2010 በኋላ ለተከታታይ 20 ጨዋታዎች ምንም ሽንፈት አላስተናገደም። ያለፉትን ስምንት ተከታታይ የሜዳው ጨዋታዎች ያሸነፈ ሲሆን 6-1፣ 5-0፣ 4-0፣ 3-0 የመሳሰሉ ውጤቶች በዐጼ ፋሲለደስ ስታዲየም ተለምደዋል።

አሁን ጥያቄው ክለቡ በሜዳው የሚያደርገውን እንቅስቃሴ እና አሸናፊነት ከሜዳው ውጪም ይደግማል? የሚለው ነው።

– ሲዳማ ቡና በሜዳው…

በአራተኛው ሳምንት በመቐለ 70 እንደርታ 2-1 መሸነፉን ተከትሎ ከ21 ተከታታይ የሜዳው ጨዋታዎች በኋላ ሽንፈት የገጠመው ሲዳማ ቡና በዚህ ሳምንትም በድጋሚ በድሬዳዋ ከተማ ተሸንፏል። ቡድኑ ባለፉት ዓመታት ከሜዳው ውጪ ከሚያስመዘግበው ደካማ ውጤት በተቃራኒው በሜዳው የማይቀመስ መሆኑ በቻምፒዮንነት ፉክክሩ ረጅም ርቀት እንዲጓዝ የረዳው ሲሆን ዘንድሮ ከወዲሁ በሜዳው ተደጋጋሚ ሽንፈት ማስተናገዱን ከቀጠለ የውድድር ዓመቱን ጉዞ ፈታኝ ሊያደርግበት እንደሚችል ዕሙን ነው።

ቡድኑ በሜዳው ከወዲሁ ሽንፈቶች ለማስተናገዱ ከሚጠቀሱት ጉዳዮች አንዱ የአጨዋወት ባህርዩ ተገማች መሆኑ ነው። ቡድኑ በመስመር በሚደረግ ፈጣን ሽግግር እና አጥቂዎቹ ከተከላካይ ጀርባ የሚያገኙትን ቀዳዳ በፍጥነት በመጠቀም ላይ ይበልጥ ጥገኛ መሆኑ ለጎል ክልላቸው ቀርበው የሚጫወቱ ቡድኖችን ሲገጥሙ እንዲቸገሩ እያደረጋቸው ይገኛል። በእርግጥ ቡድኑ ኳስ በመቆጣጠር እና መሐል ለመሐል በማጥቃት ተጋጣሚን ለማስከፈት ቢሞክርም እምብዛም ስኬታማ አይደለም።

ከድሬዳዋው ሽንፈት ጋር በተያያዘ ቡድኑ የተቆጠረበት ሁለተኛ ጎል አጨቃጫቂ እንደነበር ይታወሳል። ቡድኑ በሚያጠቃበት ወቅት ከጨዋታ ውጪ ተብሎ ረዳት ዳኛው ምልክት በማሳየታቸው የመልስ ምት እንደሚመታ ቢጠብቁም እንቅስቃሴው ቀጥሎ ጎል እንደተቆጠረባቸው በመግለፅ ክስ ማስመዝገባቸው በሳምንቱ ትኩረት ከሳቡ ጉዳዮች አንዱ ነው።

– የድሬዳዋ ከተማ ማንሰራራት

የምስራቁ ክለብ በተከታታይ ጨዋታዎች ካስመዘገው ሽንፈት በኋላ በሦስተኛው ሳምንት ወደ ድል ቢመለስም በባህር ዳር ከተማ 4-1 መሸነፉን ተከትሎ በድጋሚ ወደ አስቸጋሪ የውድድር ዘመን ጅማሮ ተመልሶ ካለፉት ሁለት ጨዋታዎች ደግሞ አራት ነጥቦችን በማሳካት ወደ ጥሩ ጎዳና መመለስ ችሏል። በተለይም በዚህ ሳምንት ከሜዳው ውጪ ሲዳማ ቡና ላይ ያሳካው ድል ከ9 ተከታታይ የሜዳ ውጪ ሽንፈት በኋላ የተገኘ ነው።

– ወልቂጤ ከተማ

ወልቂጤ ከተማ በታሪኩ ለመጀመርያ ጊዜ የፕሪምየር ሊግ ጨዋታ ያደረገው በዚህ ሳምንት ከስሑል ሽረ ጋር ያለ ጎል በተለያየት መርሐ ግብር ነበር። የሊጉ ዐቢይ ኮሚቴ የወልቂጤ ስታዲየምን ውድድር ለማድረግ ብቁ እንዳልሆነ በመግለፁ ተከታታይ ሦስት የሜዳው ጨዋታዎቹን በተለዋጭ ሜዳዎች ያደረገው ቡድኑ በነዚህ ወቅቶች መጥፎ የማይባል ውጤት ማስመዝገቡን ተከትሎ በደጋፊዎቹ ፊት መጫወት መጀመሩ ለቀጣይ ጉዞው አዎንታዊ ተፅእኖ እንደሚፈጥርለት ይጠበቃል።

– አዳማ “አቻ” ከተማ

የተረጋጋ የቡድን ስብስብ ካላቸው ጥቂት ሊጉ ክለቦች አንዱ የሆነው አዳማ ከተማ ለማሸነፍ እየተቸገረ ይገኛል። ካለፈው ዓመት ጀምሮ እስካለፈው ሳምንት ድረስ ካደረጋቸው ያለፉት 10 ጨዋታዎች አንድ ድል ብቻ ያስመዘገበ ሲሆን ያለፉት አራት ተከታታይ ጨዋታዎችን በአቻ ውጤት አጠናቋል።

ቡድኑ በተደጋጋሚ አቻ እየወጣ እንደሆነ በአራተኛው ሳምንት ከሽረ ጋር ነጥብ ከተጋራ በኋላ በሰጡት አስተያየት የገለፁት አሰልጣኝ አሸናፊ በቀለ ለዚህ ደካማ ጉዞ በቶሎ መፍትሄ ማበጀት ይጠበቅባቸዋል። በተለይም ካለው በርካታ የማጥቃት ተጫዋቾች አማራጭ አንፃር ለጥንቃቄ ቅድሚያ የሚሰጡት አሰልጣኝ አሸናፊ ጎሎችን በብዛት የሚያገኙበትን መንገድ መፈለግ ትልቁ የቤት ሥራቸው ነው።

2. ተጫዋች ትኩረት

– የባህር ዳር ከተማ የውጪ ተጫዋቾች

ሦስቱ የባህር ዳር ከተማ የውጪ ዜጋ ተጫዋቾች ሀሪስተን ሄሱ፣ ማማዱ ሲዲቤ እና አዳማ ሲሶኮ በስድስተኛው ሳምንት ቡድኑ በፋሲል ከነማ 3-0 በተሸነፈበት ጨዋታ ከደሞዝ ጋር በተያያዘ ቅሬታ አለመሰለፋቸው ይታወሳል። የጣና ሞገዶቹ የወሳኝ ተጫዋቾቻቸው አለመኖር በጨዋታው ተፅዕኖ እንደፈጠረባቸው በጉልህ ታይቷል።

ቤኒናዊው ጎል ጠባቂ ሀሪስተን ሄሱ አለመኖሩን ተከትሎ ፅዮን መርዕድ በዓመቱ ለመጀመርያ ጊዜ የተሰለፈ ሲሆን እምብዛም የጎል እድል ባልፈጠሩት ፋሲሎች ሦስት ጎሎች አስቆጥሯል። ከዚህ በተጨማሪ የባህር ዳር ጥንካሬ የሆነው የቆመ እና ተሻጋሪ ኳስ አጠቃቀም በማማዱ ሲሶኮ እና ማማዱ ሲዲቤ አለመኖር ምክንያት ደካማ እንደነበር ተስተውሏል። ከመስመር የሚሻገሩት ኳሶች በቀላሉ ሲባክኑ የታየ ሲሆን በመከላከሉ ረገድም ሁለት የጭንቅላት ኳሶች እና አንድ ከመሐል ሜዳ የተሻገረ ኳስ ተቆጥረውባቸዋል።

– የቅዱስ ጊዮርጊስ አጥቂዎች ጥምረት

በጌታነህ ከበደ እና ሳላሀዲን ሰዒድ የተዋቀረው የቅዱስ ጊዮርጊስ የአጥቂ መስመር በ6ኛ ሳምንት የሊጉ ጨዋታ ላይ ተስፋ የሰጠ ጥምረት አሳይቷል። የሁለቱ አንጋፋ አጥቂዎች ሳላሀዲን እና ጌታነህ ጥምረት ብቻ ሳይሆን የአቤል ያለው ትጋት ቡድኑን ጥንካሬ አላብሶታል። በትላንቱ ጨዋታ የታየው የጌታነህ ወደ አማካይ ክፍሉ የመሳብ እና የአቤል ወደ አጥቂ መስመሩ በፍጥነት መጓዝ የቡድኑን የፊት መስመር እንዳይገመት ከማድረጉ በተጨማሪ ሳልሃዲን በምቹ ቦታ ከሁለቱ የሚያገኘውን የኳስ አማራጭ እንዲጠቀም እድል ከፍቶለታል። ይህ ደግሞ አይምሬው አጥቂ በተደጋጋሚ እድሎችን በመፍጠር ለቡድኑ ጎሎችን እንዲያስቆጥር በር ይከፍትለታል።

በወረቀት ላይ በ4-4-2 የተጨዋች አደራደር ወደ ሜዳ የገባው ቡድኑ የተጋጣሚን የተከላካይ መስመር ለመበታተን የተጠቀመው ስልት የሚደነቅ ነበር። ጨዋታው ሲጀምር በግራ መስመር አማካይነት ወደ ሜዳ የገባው አቤል በተደጋጋሚ በሚያደርጋቸው የፈጠኑ ሩጫዎች ሳልሃዲን እና ጌታነህን እንዲረዳ አድርጎታል። ከእሱ በተጨማሪም በተቃራኒ መስመር የተሰለፈው ጋዲሳ ወደ መሃል እየገባ የተጋጣሚ የመከላከል ወረዳ ላይ የቁጥር ብልጫ እንዲኖር አስችሏል።

– ሪችሞንድ አዶንጎ

ጋናዊው አጥቂ ድሬዳዋ ከተማ በዓመቱ ካስቆጠራቸው አራት ጎሎች መካከል ሦስቱን አስቆጥሯል። ቡድኑ ሲዳማን በረታበት ጨዋታ ከቅጣት ምት የተሻገረን ኳስ ተጠቅሞ ያስቆጠረው ሪችሞንድ ዘንድሮ ያስቆጠራቸው ሦስቱም ጎሎች መነሻቸው ከቆመ ኳስ መሆኑ አስገራሚ ያደርገዋል። በጨዋታ ጥቂት የጎል ዕድል የሚፈጥረው ድሬዳዋ ለአጥቂው በርካታ እድል ባይፈጥርለትም የቆሙ ኳሶችን እያነፈነፈ ይገኛል።

3. ዲሲፕሊን

– ከሜዳ የሚጫወቱ ቡድኖች

በዚህ ሳምንት 33 ቢጫ እና 1 ቀይ ካርድ በስምንቱ ጨዋታዎች ተመዟል። ከነዚህ ካርዶች መካከል 28 ቢጫ እና 1 ቀይ ካርድ የተመዘዘባቸው ከሜዳ ውጪ የሚጫወቱ ቡድኖች ናቸው። ይህ ቁጥራዊ መረጃ ከሜዳ ውጪ ስለሚጫወቱ ቡድኖች የሚነግረን ብዙ ነገር ቢኖርም የአጨዋወት ባህርያቸው እና የዲሲፕሊን ጉዳይ ትልቁን ቦታ ይይዛል።

አመዛኞቹ ቡድኖቻችን ከሜዳቸው ውጪ በሚያደርጓቸው ጨዋታዎች በመከላከል አቀራረብ ላይ አመዝነው ወደ ሜዳ መግባታቸው የማጥቃት ጫናዎች እንዲበረክትና ለስህተት ብሎም ጥፋቶችን በመስራት የተጋጣሚን የማጥቃት እንቅስቃሴ ለማበላሸት በሚያደርጉት ጥረት በርካታ የማስጠንቀቂያ ካርዶችን ሲመለከቱ ይታያል። በጨዋታዎች መገባደጃ ላይ የተጋጣሚን ፍጥነት ለማቀዝቀዝ ሜዳ ላይ ሆን ብሎ በመተኛት ሰዓት ለማባከን በሚደረጉ ጥረቶች የሚመዘዙ ማስጠንቀቂያ ካርዶች ከፍተኛውን ቁጥር ሲይዙ “ከሜዳ ውጪ የሚጫወቱ ቡድኖች ላይ ዳኞች ጫና ያሳድራሉ ” በሚሉ ተለምዷዊ እምነቶች የዳኛ ውሳኔን ካለመቀበል በሚፈጠሩ ሰጣ ገባዎች የሚመዘዙ ካርዶችም የትየለሌ ናቸው።

– ስሑል ሽረ

በዚህ ሳምንት ከተመዘዙ ካርዶች መካከል ለስሑል ሽረው ረዳት አሰልጣኝ መብራህቶም ፍስሀ የተሰጠው ይጠቀሳል። የቡድኑ የአሰልጣኞች ቡድን አባላት በአራተኛው ሳምንት ከጊዮርጊስ ጋር ባደረጉት ጨዋታ ከዳኞች ጋር በፈጠሩት ሰጣ ገባ በሊጉ ዐቢይ ኮሚቴ የቃለ መጠይቅ ጥሪ እንደደረሳቸው የሚታወስ ሲሆን በዚት ሳምንትም ድርጊቱ መደገሙ አስገራሚ ሆኗል። ከጨዋታው በኋላ ዋና አሰልጣኙ ሳምሶን አየለ በሰጡት አስተያየት ክስተቱን አምነው የረዳቶቻቸው ወጣት መሆን ስሜታዊ እንዳደረጋቸው መግለፃቸው ይታወሳል።

4. ደጋፊዎች

– የፋሲል ከነማ ደጋፊዎች በዚህ ሳምንት የሀገራችንን ብቻ ሳይሆን የአፍሪካ እግርኳስ ጋዜጠኞች እና ክለቦችን ትኩረት ስበዋል። ቡድኑ ባህር ዳርን በረታበት የሳምንቱ ተጠባቂ ጨዋታ ላይ በስታዲየም መከታተል ያልቻሉ ደጋፊዎች ከሜዳው አቅራቢያ በሚገኘው ተራራ ላይ ተምጠው ሲከታተሉ ተስተውሏል። ሁኔታው ከዚህ ቀደምም በተደጋጋሚ የሚስተዋል ሲሆን በዚህ ሳምንት ደግሞ በቁጥር ከፍተኛ ደጋፊ ከስታዲየም ውጪ ባገኘው አማራጭ ሁሉ ሲከታተል የተስተዋለበት ነበር።

5. ጎሎች

ባለፉት ሳምንታት በአንፃራዊነት በበርካታ ጎሎች ሲንበሸበሽ የነበረው ፕሪምየር ሊጉ በዚህ ሳምንት በጎል ድርቅ ተመትቷል። 15 ጎሎች የተቆጠሩበት ይህ ሳምንት በተለይ በሦስት ጨዋታዎች (ኢትዮጵያ ቡና 5-0 ሀዲያ ሆሳዕና እና ፋሲል ከነማ 3-0 ባህር ዳር) ላይ በርካታ ጎሎች ባይቆጠሩበት ሳምንቱ ዝቅተኛ ጎሎች የተቆጠረበት ይሆን ነበር።

ቡድኖች በተለይም ከሜዳ ውጪ የሚጫወቱ ቡድኖች አሉታዊ አቀራረብ፣ የክለቦቻችን በተለይም የባለሜዳ ክለቦች ተገማች አቀራረብ እና የሚዋዥቅ አቋም በርካታ ጎሎች እንዳይቆጠሩ ምክንያት ሲሆን ተስተውሏል።

© ሶከር ኢትዮጵያ