የአሰልጣኞች አስተያየት | ስሑል ሽረ 1 – 0 ሰበታ ከተማ

በኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ሰባተኛ ሳምንት የመክፈቻ ጨዋታ ስሑል ሽረ ሰበታ ከተማን 1-0 ካሸነፈ በኋላ የሀለለቱ ቡድኖች አሰልጣኞች አስተያየታቸውን ሰጥተዋል። 

👉 “በሁለቱም አጋማሾች በጣም ያለቀላቸው ዕድሎች አምክነናል፤ ከ1-0 በላይ ማሸነፍ እንችል ነበር” ሳምሶን አየለ (ስሑል ሽረ)

ስለ ጨዋታው

የዛሬ ጨዋታ በጣም ጠንካራ ፉክክር የታየበት ነው። ሦስት ነጥቡ በጣም ያስፈልገን ነበር።
ድል ካደረግን የቡድናችን በራስ መተማመን በከፍተኛ ሁኔታ ሰለሚጨምር ተጫዋቾቻችን በሁለቱም አጋማሾች የተሰጣቸውን ታክቲክ በሚገባ ተግብረዋል።

በሁለቱም አጋማሾች በጣም ያለቀላቸው ዕድሎች አምክነናል፤ አንድ ለባዶ ሳይሆን ከዛ በላይ ማሸነፍ እንችል ነበር። የተጋጣሚያችንን የጨዋታ አቀራረብ ቀድመን አውቀናል። በአጫጭር ኳስ የሚጫወት እና በራሳቸው ሜዳ ላይ ኳሱን በመልቀቅ በራሳችን ሜዳ ሲገቡ ተጭነን ኳሱን በመውሰድ በመልሶ ማጥቃት የምንፈልገውን ነገር ለማሳካት ችለናል። በአጠቃላይ ጨዋታው ጥሩ ነበር፤ ተጫዋቾቼ ለከፈሉት መስዋዕትነት ምስጋና ይገባቸዋል።

በጨዋታው ስለ ባከኑ ዕድሎች

ቡድናችን ካለበት መሰረታዊ ችግር አንፃር የቡድናችን የራስ መተማመን ደረጃ ገና ነው። ገና ከአሁን በኃላ ነው እየተስተካከለ የሚሄደው። በመከላከል ላይ የነበሩብንን ክፍተቶች አርመን አሁን ጥሩ የመከላከል አቅም አለን። ባለፉት ሦስት ጨዋታዎች ብዙ ጎሎች አልገቡብንም። በተደጋጋሚ ወደ ተጋጣሚ የግብ ክልል መድረስ ችለናል አጨራረስ ላይ ያሉትን ችግሮች ደግሞ በሂደት እናስተላክላለን”

👉  “ለነሱ በሚመች መንገድ ነበር ስንጫወት የነበረው፤ ከምናምንበት ነገር ባንወጣ ጥሩ ነበር” ውበቱ አባተ (ሰበታ ከተማ)

ስለ ጨዋታው

ጨዋታው ክፍት ነበር። በሁለታችንም በኩል በርካታ ግቦች መቆጠር ይችሉ ነበር። አጨቃጫቂ ቢሆንም በፍፁም ቅጣት ምት ጎል አግብተውብናል። ከሱ ይልቅ በነሱ በኩል ጎል መሆን የሚችሉ በርካታ ኳሶች አምክነዋል። እኛም ብዙ የግብ ዕድሎች ፈጥረናል። ለኛ ጥሩ ባይሆንም ለተመልካች ግን ጥሩ ጨዋታ ነበር።

ቡድኑ ከዕረፍት በኋላ ስላደረገው የአጨዋወት ለውጥ

አንዳንዴ ሰዓት እየገፋ በሄደ ቁጥር ቶሎ ግብ ለማስቆጠር ከማሰብ አንፃር ከእንቅስቃሴ የምንወጣባቸው አጋጣሚዎች ነበሩ። በመጀመርያው አጋማሽ ጥሩ ነበርን፤ በሁለተኛው አጋማሽ ግን እነሱ ያለውን ነገር እያስጠበቁ በመልሶ ማጥቃት ሲሄዱ ነበር። ለነሱ በሚመች መንገድ ነበር ስንጫወት የነበረው፤ ከምናምንበት ነገር ባንወጣ ጥሩ ነበር።

ስለ ዳኝነት

በዳኝነት ላይ ማሳበብ አልፈልግም። በመጨረሻዎቹ ደቂቃዎች እነሱ ውጤት አስጠብቀው ለመውጣት ጊዜ ማባከኖች ነበሩ። ከዛ አንፃር የተሰጠው ደቂቃ አሳማኝ አይደለም። የተጨመረው ደቂቃም አልተጫወትነውም ማለት ይቻላል። ከተጨመረም እሱ ነገር ነው የቀጠለው።
ለጭማሪ ሰዓቶች ዋጋ አልተሰጡም።


© ሶከር ኢትዮጵያ