ሎዛ አበራ በማልታ ግብ ማምረቷን አጠናክራ ቀጥላለች

ትላንት ምሽት በተደረገ ተጠባቂ የማልታ የሴቶች አንደኛ ዲቪዝዮን ጨዋታ ላይ ኢትዮጵያዊቷ ሎዛ አበራ ቡድኗ ሦስት ነጥብ ይዞ እንዲወጣ አድርጋለች።

ቢርኪርካራዎች ምጋር ዩናይትድን ጋብዘው 3-1 ባሸነፉበት ጨዋታ ላይ ሎዛ ጥሩ እንቅስቃሴ በማድረግ ሁለት ጎሎች አስቆጥራለች። 0-0 በሆነ ውጤት ወደ መልበሻ ክፍል ያመሩት ቢርኪርካራዎች በሁለተኛው አጋማሽ ጅማሮ ላይ አና ማሪ ሰዒድ ባስቆጠረችው የ56ኛ ደቂቃ ጎል መሪ ሆነዋል። ከአስራ አንድ ደቂቃዎች በኋላም ሎዛ በአምስት ደቂቃ ውስጥ አከታትላ ባስቆጠረቻቸው ሁለት ጎሎች ቡድኗ የሊጉን ጠንካራ ክለብ እንዲያሸንፍ እና የሊጉን ደረጃ ሰንጠረዥ በብቸኝነት እንዲመራ ሆኗል።

ሎዛ በማልታ ሊግ እስካሁን ባደረገቻቸው 9 ጨዋታዎች 21 ጎሎችን በማስቆጠር የከፍተኛ ግብ አግቢነቱን እየመራች ትገኛለች። በተለያዩ ውድድሮች በተሰለፈችበት 11 አጠቃላይ ጨዋታዎች ደግሞ 25 ግቦችን ለክለቧ በማስቆጠር ጠንካራነቷን አስመስክራለች።


© ሶከር ኢትዮጵያ