የአሰልጣኞች አስተያየት | ሀዲያ ሆሳዕና 2-1 ሲዳማ ቡና

በአቢዮ ኤርሳሞ ስታዲየም ሀድያ ሆሳዕና የመጀመሪያ ድሉን ሲዳማ ቡና ላይ ካስመዘገበ በኃላ የሁለቱ ቡድን አሰልጣኞች ሀሳባቸውን ሰጥተዋል፡፡


👉 “ውጤቱም ይገባናል ብዬ አምናለሁ” ኢዘዲን አብደላ (ሀዲያ ሆሳዕና-ምክትል አሰልጣኝ)

ስለ ጨዋታው

ከጨዋታው በፊት ተጨዋቾቻችን ጫና ውስጥ ነበሩ። ተጨዋቾቻችን ብቻ ሳይሆኑ ሁላችንም በጫና ውስጥም ሆነን ነው ለጨዋታው የቀረብነው። በጨዋታውም ያስመዘገብነው የመጀመሪያ ድላችንም በጣም ደስ አሰኝቶናል። ደጋፊዎቻችን ያለንበት ነገር ባይመጥናቸውም የዛሬው ድላችን ወደ ጥሩ መንገድ እንድንገባ እና እንድንደረደር ያደርገናል። የዛሬውም ውጤት ይገባናል ብዬ አስባለሁ።

የዛሬውን ድል ስለማስቀጠል

እንደሚታወቀው ሁሌ በእግር ኳስ የምታስበውን ነገር ላታገኝ ትችላለህ። እኛ ካለን የቡድኑ ስብስብ አንፃር የምንፈልገውን አላገኘንም። ምናልባት የዛሬው ድላችን መነሻ ይሆነናል ብለን እናስባለን። ለዚህም ደግሞ የተጨዋቾቻችን አቅም ወደ ፊት ያሳድገናል ብለን እናምናለን። በእስካሁኖቹ ጨዋታዎች ጥቃቅን ስህተቶች ነበሩብን። በእነኚህ ስህተቶች ደግሞ ብዙ ዋጋ አስከፍለውናል። ከዛሬው ጨዋታ በፊትን ችግራችን ላይ ስንሰራ ነበር። በዚህ ረገድ ደግሞ የሰራነው ተሳክቶልናል ብለን እናምናለን፡፡ የኛ ደጋፊ ለየት ይላል። ስለነበረውም ትዕግስት እያመሰገንን ቀጣይም ከጎናችን ሆኖ እንዲቀጥል እና የምንፈልገው ደረጃ ላይ እንድንደርስ በጋራ እንድንሰራ እንጠይቃለን።

👉 “እጅግ አሳፋሪ ጨዋታ ነው” ዘርዓይ ሙሉ (ሲዳማ ቡና)

ስለጨዋታው

እጅግ አሳፋሪ ጨዋታ ነው። ይሄ እግር ኳስ አይደለም። ኳስ እኛ እያመላለስን የምንጫወትበት ነገር ያሳፍራል። ገና ከእረፍት ጀምሮ አንድ ጎል እንዳገቡ ኳስ መደበቅ ጀመሩ። አራተኛ ዳኛው ይሄን ደጋግሞ ማስጠንቀቅ ነበረበት። ዘጠናውንም ደቂቃ እኛ ኳስ እያመላለስን ነው የተጫወትነው። እነሱ ከሰላሳ ደቂቃ በኃላ ምንም አልተጫወቱም። ፌድሬሽኑ ራሱ የሚያሳፍር ነው። ይሄን እርሻ ሜዳ የመጫወቻ ሜዳ ብሎ መፍቀዱ ያሳዝናል። በዚህ ሜዳ ላይ እግር ኳስ አየን ማለት በጣም ይከብዳል። ዳኛውም ፍትሃዊ አልነበረም። ከእረፍት በፊት ንፁህ የፍፁም ቅጣት ምት ከልክሎናል። ይህቺ አጋጣሚ ደግሞ ጨዋታውን የምትቀይር ነበረች። በአጠቃላይ በዛሬው ጨዋታ በፍፁም ኳስ አልተጫወትንም፡፡

© ሶከር ኢትዮጵያ