ወላይታ ድቻ በአሰልጣኝ ገብረክርስቶስ ቢራራ ጉዳይ ምላሽ ሰጥቷል

በዚህ ሳምንት መነጋገርያ በሆነው የወላይታ ድቻ እና አሰልጣኝ ገብረክርስቶስ ቢራራ ጉዳይ ዙርያ ክለቡ ምላሹን ለሶከር ኢትዮጵያ ሰጥቷል።

የክለቡ የሥራ አመራር ቦርድ በታኅሳስ ወር ክለቡ እያስመዘገበ ያለው ወጤት በቀጣይ ሁለት ጨዋታዎች ላይ መሻሻል እንደሚገባው እና ይህ የማይሆን ከሆነ ክለቡ የራሱን ውሳኔ እንደሚያሳውቅ ለአሰልጣኝ ገብረክርስቶስ ቢራራ እና ለምክትሎቻቸው መገለፁ የሚታወቅ ሲሆን አሰልጣኙም በስሑል ሽረ 2-0 በሆነ ውጤት ሽንፈት ካስተናገዱ በኃላ ለመገናኛ ብዙኀን አስተያየታቸውን ሲሰጡ የክለቡ ቦርድ በሥራቸው ለመቀጠል በሁለት ጨዋታዎች ላይ ውጤታቸውን እንዲያስተካከሉ የሰጠው እድል ባለመሳካቱ ከዚህ በኋላ በኃላፊነታቸው የመቀጠላቸው ነገር እንዳበቃለት ተናግረው እንደነበር ይታወቃል። ከትላንት በስቲያ ደግሞ ቦርዱ አሰልጣኙ ስልካቸውን አጥፍተው መገኘት ባለመቻላቸው በራሳቸው ፍቃድ እንደለቀቁ ተደርጎ በምትኩ ደለለኝ ደለልቻ በጊዜያዊነት እንዲመራ መሾሙን መዘገባችን የሚታወስ ነው።

በትናትናው ዕለት ደግሞ አሰልጣኝ ገብረክርስቶስ ለድረገፃችን በሰጡት አስተያየት የክለቡ ህጋዊ አሰልጣኝ እርሳቸው እንደሆኑ እና ከክለቡ ጋር በስንብት ዙርያ ሳይነጋገሩ እንደማይለያዩ፤ ለቀጣይ ጨዋታ የልምምድ መርሐ ግብር እየተዘጋጁ እንደሆነም ገልፀዋል።

በዚህ ጉዳይ ላይ ያናገርናቸው ክለቡን በጊዜያዊ ሥራ አስኪያጅነት እየመሩ ያሉት አቶ ምትኩ ኃይሌ ለሶከር ኢትዮጵያ ይህን ብለዋል። ” ከመገናኛ ብዙኀን ከምንሰማው ውጭ ክለቡ አላሰናበታቸውም። ለክለቡ ሳያሳውቁ በስራ ገበታቸው ላይ ባለመገኘታቸው በተደጋጋሚ ስልክ ብንደውልም ስልካቸውን ሊያነሱ ባለመቻላቸው ሰኞ ዕለት (ጥር 4) ባወጣነው ማስታወቂያ ከጅማ አባ ጅፋር ጋር ላለበት ጨዋታ ቡድኑን እንዲያዘጋጁ እና እንዲመሩ ለመጥራት ተገደናል። አሰልጣኙ በስራ ገበታቸው ላይ በቀጣይ የማይገኙ ከሆነ ክለቡ የራሱን እርምጃ ለመውሰድ እንደሚገደድ ነው የተናገርነው” ብለዋል።

አሰልጣኙ ወደ ስራ ገበታቸው እንዲመለሱ ያሳሰበበት ማስታወቂያ 👇


© ሶከር ኢትዮጵያ