የባህር ዳር ከተማ ተጨዋቾች ወደ ልምምድ ተመልሰዋል

ከደሞዝ እና ጥቅማጥቅም ጋር በተያያዘ ልምምድ አቁመው የነበሩት የጣናው ሞገድ ተጨዋቾች ዛሬ ወደ ልምምድ መመለሳቸው ታውቋል።

ከትላንት በስትያ ከሀዋሳ ባህር ዳር የደረሱት ተጨዋቾቹ “የ4 ወር ደሞዝ ካልተከፈለን እና የሚገባን የማበረታቻ ጥቅማጥቅም ካልተሰጠን ልምምድ አንሰራም” በማለት የትላንቱን መደበኛ ልምምድ ሳያከናወኑ መቅረታቸው ይታወቃል። ቡድኑ ዛሬ ጠዋታ መስራት የነበረበትን ልምምድ አለመስራቱ ነገር ግን ከሰዓት የክለቡ ስራአስኪያጅ፣ የከተማው ከንቲባ እና የደጋፊዎች ማኅበር አመራሮች ከተጨዋቾች ተወያይተው ጉዳዩን እንደፈቱት እና ተጨዋቾቹ ወደ መደበኛ ልምምዳቸው እንዲመለሱ እንደተደረገ ተገልጿል።

ተጨዋቾቹ በአሰልጣኝ ፋሲል ተካልኝ እየተመሩ ከሰዓት 11 ሰዓት ልምምድ እንደሰሩ እና ቅዳሜ ላለባቸው የወልዋሎ ጨዋታ ዝግጅት እንደጀመሩ ተጠቁሟል።


© ሶከር ኢትዮጵያ