አዳማ ከተማዎች ወደ ድሬዳዋ ያመራሉ

ባለፉት ቀናት ከደሞዝ ጋር በተያያዘ በተፈጠረ ቅሬታ ልምምድ ያልሰሩት የአዳማ ከተማ ተጫዋቾች ወደ ድሬዳዋ ለማምራት ተዘጋጅተዋል።

ክለቡ ደሞዝ አልከፈለንም በሚል ቅሬታ ከሳምንቱ መጀመርያ ወዲህ ቡድኑ መደበኛ ልምምድ ሳይሰራ የቆየ ሲሆን ይህም የ9ኛው ሳምንት ጨዋታን ስለማድረጉ አጠራጥሮ ቆይቷል።

ቡድኑ በአሁኑ ሰዓት ወደ አዲስ አበባ ጉዞ እያደረገ የሚገኝ ሲሆን ዛሬ በኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ልምምድ ካከናወኑ በኋላ በጠዋቱ በረራ ወደ ድሬዳዋ እንደሚያቀኑ ታውቋል። አሰልጣኝ አሸናፊ በቀለ ከመደበኛ ስራቸው ውጭ በአሸማጋይነት ባደረጉት ጥረት ቡድኑ ወደ ድሬደዋ እንደሚጓዝ ይታወቅ እንጂ የተጫዋቾቹ የደሞዝ ይከፈለን ጥያቄ እስካሁን ምላሽ እንዳላገኘ ሰምተናል።

አዳማ ከተማ በ9ኛው ሳምንት ከድሬዳዋ ከተማ ጋር ነገ በ9፡00 ድሬዳዋ ላይ እንደሚጫወት ይታወቃል።


ሶከር ኢትዮጵያ