የአሰልጣኞች አስተያየት | ሀዋሳ ከተማ 3-1 ወልቂጤ ከተማ

በዘጠነኛው ሳምንት የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ሀዋሳ ከተማ በሜዳው ወልቂጤ ከተማን 3-1 ካሸነፈበት ጨዋታ በኃላ የሁለቱ ክለብ አሰልጣኞች ከሶከር ኢትዮጵያ ጋር ተከታዩን ቆይታ አድርገዋል፡፡

👉 “የመከላከል ችግራቸውን በሚገባ ተጠቅመናል” አዲሴ ካሳ – ሀዋሳ ከተማ

ስለጨዋታው

ይሄ ነጥብ ለኛ ከሁለት ሽንፈት እና ከሦስት ዕኩል ለዕኩል በኃላ የመጣ ውጤት ስለሆነ ወሳኝ ነበር። እንደሚታወቀው አንድ ቡድን ሲያሸንፍ ላይ ነው ሲሸነፍ ደግኖ ታች ነው ፤ ስለዚህ ውጥረት ነው፡፡ በተለይ ወልቂጤዎች በስምንት ጨዋታ አራት ጎል ነው የገባባቸው ፤ ሁለት ጎል ነው ያገቡትም። ይሄን የእነሱን ጎን ተነጋግረን ነበረ የገባነው ፤ ሜዳም ላይ ያየነው ይሄን ነው፡፡ ማግባት ግን ይከብደናል ብዬ ነበር፡፡ ከምንግዜውም የተሻለ ነበር ያገባነው። እነሱም የፈለጉት ማሸነፍን ስለነበር ክፍተቶችን አይተንባቸዋል፡፡ የመከላከል ችግራቸውን በሚገባ ተጠቅመናል፡፡

ጨዋታውን ተቀይሮ ገብቶ መለወጥ የቻለው ዘላለም ኢሳያስ በመጀመሪያ አሰላለፍ ውስጥ አለመካተቱ

ኳስ ጨዋታ እንደዚህ ነው። የመጀመሪያውን አሰላለፍ ለማውጣት ከልምምድ ካለው ነገር ትነሳለህ። እንደዚህ ዓይነት ችግሮች ሲፈጠሩ ደግሞ ማንን ማስገባት አለብኝ የሚለውን ታያለህ። ዘላለም ዛሬ ተቀይሮ ገብቶ በጣም ጥሩ ነበር። የሚቀማበት ፣ የሚታገልበት መንገድ እና አመራሩ በጣም ጥሩ ነበር፡፡ ከዚህ በፊት ከሲዳማ ጋር ስንጫወት ሃያ ዘጠኝ ደቂቃዎች ተሰልፎ ተጫውቷል፡፡ ያን ያደረግነው በምክንያት ነው። በወቅቱ በሱ የገባሁም ዮሀንስ ሴጌቦ ነበር፡፡ በጨዋታው ዳዊት ተፈራን ሊያቆም አልቻለም፡፡ ዘላለም በራሱ ብቻ ነበር በዛን ጨዋታ ቀይረን አስወጣነው ፤ ያኔም ብናቆየው ይሻል ነበር፡፡ ምክንያቱም የሚጠብቀው እና ሜዳ ላይ የሚሆነው ነገር አንድ አይደለም። ዛሬ ግን በዘላለም ላይ የተሻለ ነገር ነው ያየሁት፡፡ ኳስ ይቀማል ፣ ይሰጣል አንድ ተጫዋች ደግሞ ወደ መስመሩ ሲገባልህ ጥሩ ነው፡፡ ኳስ ጨዋታ ደግሞ ይሄው ነው።

👉 ” በጨዋታው ሀዋሳ ማሸነፍ ይገባዋል” ደግአረግ ይግዛው – ወልቂጤ ከተማ

ስለጨዋታው

ተጫዋቾቻችን መረጋጋት አይታይባቸውም ነበር፡፡ በጨዋታው ሀዋሳ ማሸነፍ ይገባዋል። ምክንያቱም የቡድኔን ጨዋታ አልነበረም ዛሬ ስንጫወት የነበረው። ልጆቻችን ጭንቀት ውስጥ ናቸው ፤ ውጤት ለማግኘት። ይህ ደግሞ ሜዳ ላይ ሲንፀባረቅ በጉልህ ያየንበት ጨዋታ ነው፡፡ በተረፈ የሚችሉትን ያህል ጥረት አድርገዋል፡፡ ለቀጣይ ክፍተቶቻችንን አርመን ልጆችን በስነልቡናው አዘጋጅተን ወደ ሜዳ እንመለሳለን ብዬ ተስፋ አደርጋለሁ፡፡ ወጣቶች በመሆናቸው ስሜት ውስጥ ሆነው ይገባሉ። ጎል ሲገባም ደግሞ ቶሎ ይወርዳሉ። ዕረፍት ላይ ያሉብንን ክፍተቶች አርመን ለመግባት ሞክረናል፡፡ ነገር ግን ተጭነን እየተጫወትን እና ሁለተኛ ጎል እየፈለግን ባለንበት ወቅት ሁለተኛ ጎል ባልጠበቅነው ሁኔታ አስተናግደናል፡፡ ይሄ አወረደን እንጂ እንደሁለተኛው አጋማሽ አጀማመራችን ጥሩ ነበር። የመጀመሪያው አጋማሽ ስህተታችንንም ለማረም ጥረት አድርገን ነበር ፤ ልጆቹም ጥሩ ነበሩ። ከዛም ውጪ የሚገባንን ፍፁም ቅጣት ምት ጨዋታው ላይ ተከልክለናል። እነዚህ እነዚህ ነገሮች ልጆቻችንን አውርደዋቸዋል ብዬ አስባለሁ፡፡

ስለ ቡድኑ የመከላከል ክፍተት

እነዚህ አሁን ካለፉት ጨዋታ ጀምሮ ያየናቸው እንቅስቃሴዎች ናቸው፡፡ በንግግር እና በሜዳ ላይ ለማረም ጥረት እናደርጋለን፡፡ ትልቁ ነገር ስነልቡና ነው፡፡ ጨዋታውን ተቆጣጥረው አሸንፈው እንደሚወጡ እርግጠኛ ያለመሆን ድክመትን በተከታታይ ጨዋታዎች እያየን ነው። እናም በቀላሉም ጎሎችን ለማስተናገድ ተገደናል። ይሄንን ለማረምም ጥረት እናደርጋለን፡፡


© ሶከር ኢትዮጵያ