የኢትዮጵያ ከ17 ዓመት በታች ሴቶች ብሔራዊ ቡድን ለመልስ ጨዋታው በባህርዳር ዝግጅቱን እያደረገ ይገኛል

በህንድ አስተናጋጅነት ለሚካሄደው የዓለም የሴቶች ከ17 ዓመት ዋንጫ ውድድር ለመሳተፍ የቅድመ ማጣሪያ ጨዋታዎችን እያደረገ የሚገኘው ብሔራዊ ቡድኑ ከዩጋንዳ ጋር ላለበት የመልስ ጨዋታ ልምምዱን እየሰራ ይገኛል።

በአሰልጣኝ ሳሙኤል አበራ (ዋና) እንዲሁም በአሰልጣኝ ሰርካዲስ እውነቱ (ረዳት) አሰልጣኝነት እየተመራ ያለው ብሔራዊ ቡድኑ ከሳምንት በፊት ወደ ካምፓላ አቅንቶ በዩጋንዳ 2-0 መሸነፉ ይታወሳል። ቡድኑ ከሜዳ ውጪ የደረሰበትን ሽንፈትን ቀልብሶ ወደ ቀጣይ ዙር ለማለፍም ከአንድ ሳምንት (ረቡዕ) በፊት የመልሱን ጨዋታ ወደሚያደርግበት ባህርዳር አምርቶ ልምምዶችን እያከናወነ ይገኛል።

ቡድኑ ባህር ዳር ከደረሰ በኋላ ለሦስት ተከታታይ ቀናት በቀን ሁለት ጊዜ ከዛ በኋላ ደግሞ በቀን አንድ ጊዜ የልምምድ መርሐ ግብሮችን እያከናወነ ይገኛል። ዛሬም ከ4 ቀናት በኋላ ላለበት ወሳኝ ጨዋታ ለ2 ሰዓታት የቆየ ልምምድ ከ9 ሰዓት ጀምሮ አከናውኗል። በልምምዱም ቡድኑ ለ2 ተከፍሎ የግማሽ እና የሙሉ ሜዳ ግጥሚያዎችን ሲያደርግ ተስተውሏል። በዋናነት ግን ተጨዋቾቹ ግብ የማስቆጠር ችሎታቸው እና ስልታቸው እንዲጎለብት ግብ ላይ ያተኮረ ስልጠናዎች ሲሰጡ ታይቷል።

ከቡድኑ ጋር በተያያዘ 2 ተጨዋቾች በአዲስ መልክ ጥሪ ቀርቦላቸው ስብስቡን ዛሬ ተቀላቅለዋል። በዚህም አረጋሽ ካልሳ እና ገነት ኃይሉ ትላንት ወደ ባህር ዳር አምርተው ዛሬ ከአጋሮቻቸው ጋር ልምምድ መስራት ጀምረዋል። ከሁለቱ ተጨዋቾች በተጨማሪ የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ግብ ጠባቂ የሆነችው ምህረት ተሰማ ነገ ቡድኑን ልትቀላቀል እንደሆነ ታውቋል። ከዚህ ውጪ ከ20 ዓመት በታች የሴቶች ብሄራዊ ቡድን ጥሪ ቀርቦላቸው ቡድኑን ለቀው የነበሩት ቤተልሄም በቀለ እና ነፃነት ፀጋዬ ዛሬ ዳግም ቡድኑን ተቀላቅለው ልምምድ እየሰሩ ታይቷል።

በሶሊያና ሆቴል መቀመጫውን አድርጎ በባህር ዳር ዓለም አቀፍ ዋና ስታዲየም እና መለስተኛ ስታዲየም ልምምዱን እየሰራ የሚገኘው ቡድኑ ትላንት 9 ሰዓት ሽምብጥ የሴቶች ፕሮጀክት ከተባለ ቡድን ጋር የወዳጅነት ጨዋታ አከናውኖ በሰፊ ጎል አሸንፏል።


© ሶከር ኢትዮጵያ