የኢትዮጵያ እግርኳስ ፌዴሬሽን ለአዳዲስ ኮሚሽነሮች ስልጠና መስጠት ጀመረ

በፌዴሬሽኑ ስር የሚካሄዱ ጨዋታዎችን በታዛቢነት ለመምራት የሚችሉ ተተኪ ኮሚሽነሮችን ለማፍራት ያለመ ሥልጠና እየተሰጠ ይገኛል።

ከጥር 18 ጀምሮ በተለያዩ ባለሞያዎች አማካኝነት ስልጠና በመስጠት ላይ የሚገኘው ፌዴሬሽኑ በዚህ ዓመት ካቀዳቸው ተግባራት መካከል ተተኪ ኮሚሽነሮችን ማፍራተ እንደሆነ የተገለፀ ሲሆን በኢትዮጵያ ወጣቶች ስፖርት አካዳሚ የመሰብሰቢያ አዳራሽ እየተከናወነ ይገኛል።

ስልጠናው ለአምስት ቀን የሚቆይ ሲሆን የክፍል ውስጥ እንዲሁም የተግባር ትምህርት እንዳለው ተገልጿል። ከ100 በላይ ሰልጣኞች የተሳተፉበት ይህ ስልጠና ከመላ ሀገሪቱ የተውጣጡ ሲሆን ሁሉም ኮሚሽነሮች የምልመላ መስፈርቱን ያሟሉ መሆናቸው ተገልጿል።

በተለያዩ ጨዋታዎች ላይ የብቃት ደረጃቸው አስተማማኝ ያልሆነ እና በእድሜ መግፋት ሥራቸውን ለመከወን የሚቸገሩ ኮሚሽነሮች መኖራቸውን የክለብ አመራሮች በተለያዩ ወቅቶች በተለይ በውድድሮች ዓመታዊ ስብሰባዎች ላይ ሲናገሩ በተደጋጋሚ ሲደመጥ እንደመስተዋሉ ስልጠናው ችግሩን በመጠኑም ቢሆን ይቀርፋል ተብሎ ተስፋ ተጥሎበታል።

© ሶከር ኢትዮጵያ