ሪፖርት | ወልቂጤ ከተማ ተከታታይ ድሉን አስመዘገበ

በ11ኛ ሳምንት የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ መርሐ ግብር ወልቂጤ ከተማ ወደ አቢዮ ኤርሳሞ መታሰቢያ ስታድየም አምርቶ ሀዲያ ሆሳዕናን 2-1 በሆነ ውጤት አሸንፏል።

ባለሜዳዎቹ ሆሳዕናዎች እሁድ በአዳማ ከተሸነፉበት ስብስብ ውስጥ የሦስት ተጫዋች ለውጥ በማድረግ ለጨዋታው ቀርበዋል። በዚህም አቤር ኦቮኖ ፣ ፍራኦል መንግስቱ እና አብዱልሰመድ ዓሊን አሳርፈው ታሪክ ጌትነት ፣ በኃይሉ ተሻገር እና ኢዩኤል ሳሙኤልን ወደ ሜዳ አስገብተዋል። በጨዋታ ከአንድ ጎል በላይ ማስቆጠር አልሆን ብሏቸው የነበሩት ወልቂጤዎች በበኩላቸው በ10ኛ ሳምንት የሊጉ መርሐ ግብር ድሬዳዋን ካሸነፈው ስብስብ ውስጥ ፍፁም ተፈሪ ፣ ይበልጣል ሽባባው እና አህመድ ሁሴንን በበረከት ጥጋቡ ፣ ሙሀጅር መኪ እና አዳነ በላይነህን ተክተው ወደ ሜዳ ገብተዋል።

ሳቢ ባልነበረው እና የጠሩ የግብ ዕድሎች ባላስመለከተው የመጀመርያው አጋማሽ ወልቂጤዋች ለአጥቂዎቻቸው በሚሻገሩ ረጃጅም ኳሶች ለማጥቃት ሲሞክሩ ሆሳዕናዎች በተለመደው የመስመር አጨዋወታቸው ጎል ለማግኘት ጥረዋል። ሀዲያ ሆሳዕናዎች በመጀመሪያው ደቂቃ ወደ ተጋጣሚያቸው የሜዳ ክፍል በመድረስ በአፈወርቅ ኃይሉ አማካኝነት ከርቀት ሙከራ አድርገዋል። ምንም እንኳን ቡድኑ ገና በመጀመሪያው ደቂቃ የግብ ማግባት ሙከራ ቢያደርግም አንድ ደቂቃ ባልሞላ ጊዜ ውስጥ አዳነ ግርማ ያገኘውን የቅጣት ምት በቀጥታ ሞክሮ ግባቸውን ፈትሿል። እንግዶቹም በመስመር በሚሻሙ እንዲሁም በመልሶ ማጥቃት ኳሶች ቶሎ ቶሎ ወደ ግብ በማድረስ በጫላ እና ሳዲቅ አማካኝነት ሙከራዎች ቢያደርጉም ግብ ጠባቂው ታሪክ ጌትነት አድኖባቸዋል።

በአንፃራዊነት በተጋጣሚ የሜዳ ክፍል መቆየት የቻሉት ባለሜዳዎቹ በመጀመርያው አጋማሽ ጥሩ አጀማመር እንደማድረጋቸው እና በኳስ ቁጥጥርም ብልጫ ወስደው እንደመታየታቸው በርካታ ንፁህ የግብ ዕድሎች ባይፈጥሩም በተወሰኑ አጋጣሚዎች ግብ ለማስቆጠር ተቃርበው ነበር። በተለይም በ38ኛው ደቂቃ አዩብ በቀታ ያደረገው የግብ ሙከራ ነብሮቹን መሪ የሚደርግ ክስተት ነበር። በ42ኛው ደቂቃ ከሆሳዕናዎች በኩል የመጣውን የማጥቃት እንቅስቃሴ ያቋረጠው ዓወል መሀመድ በረጅሙ ወደ መስመር የጣለውን እና ወደ ውስጥ የተሻማውን ኳስ ሳዲቅ ሲቾ በግንባሩ አስቆጥሯል።

ጎሉን ተከትሎ የጨዋታው ዳኞች እና የቡድናቸው አመራር ላይ ተቃውሞ ሲያሰሙ የነበሩት የሆሳዕና ደጋፊዎች ተቃውሟቸው አይሎ ለጥቂት ደቂዎች የተቋረጠ ሲሆን በድጋሚ ከተጀመረ በኋላ የመጀመሪያው አጋማሽ ተጨማሪ ግብ ሳያስመለክተን በሰራተኞቹ መሪነት ተጠናቋል።

ከዕረፍት መልስ የወልቂጤው አሰልጣኝ ደግአረገ ይግዛው ውጤቱን አስጠብቆ ለመውጣት የጥንቃቄ አጨዋወት በመምረጣቸው ቡድኑ ወደራሱ የግብ ክልል አዘንብሎ ተጫውቷል። በአንፃሩ ነብሮቹ ከመጀመርያው አጋማሽ በተሻለ ሲንቀሳቀሱ በ50ኛው ደቂቃ ከሆሳዕና የሜዳ ክፍል በረጅሙ ወደ ጎል የተመታውን ኳስ ቢስማርክ ኦፖንግ ሳይታሰብ ከተከላካዮች መሐል አግኝቶ በግንባሩ ቢገጭም ወደ ውጪ ሊወጣበት ቻለ እንጂ ለቡድኑ ጥሩ አጋጣሚ ነበር። ነብሮቹ በዚህ ሁኔታ ጫና ፈጥረው በሚያደርጉት እንቅስቃሴ ውስጥ ወልቂጤዎች ከግብ ክልላቸው በረጅሙ ያራቁትን ኳስ ሳዲቅ ሲቾ አግኝቶ ሳይጠቀምበት የቀረበት የማግባት አጋጣሚም በአደገኝነቱ የሚነሳ ነበር።

ሀዲያዎች በመልሶ ማጥቃት የሚሰነዘርባቸው ጥቃት እየፈተናቸው ባሉበት አጋጣሚ አቻ ሊያደርጋቸው የሚችል ዕድል በ67ኛው ደቂቃ አግኝተው ነበር። ይሁን ከቀኝ ወደ መሐል ኳሱን አጥቦ ሲያሻግር የግብ ክልሉን በዛሬው ዕለት በንቃት ሲጠብቅ የዋለው የወልቂጤው ግብ ጠባቂ ይድነቃቸው ቀድሞ በመውጣት አጥቂው ሳይድረስ አድኖበታል። እንዲሁም ከ70ኛው ደቂቃ ከኃላ ወደ መስመር የተጣለውን ኳስ አጥቂው ኦፖንግ አግኝቶ በቀጥታ ሞክሮ ግብ ሆነ ሲባል ቶማስ ስምረቱ እንደምንም ተደርቦ ወደ ውጪ ያወጣት ቅፅበት ለነብሮቹ የሚያስቆጭ ሆኖ አልፏል። በ75ኛው ደቂቃ በጨዋታው ጥሩ ሲንቀሳቀስ የነበረው ይሁን አደገኛ የግብ ክልል ውስጥ ኳስ ይዞ ሲገባ በአዳነ በላይነህ አማካኝነት ጥፋት ሰርቷል በሚል ፍፁም ቅጣት ምት ያገኙት ሆሳዕናዎች በሄኖክ አርፍጮ አማካይነት አቻ መሆን ችለዋል። ነገር ግን ከግቡ መቆጠር በኋላ እጅጉን የተጫኑት እንግዶቹ ከማዕዘን በተሻገረ ኳስ መነሻነት አሳሪ አልመሐዲ በግንባሩ ገጭቶ ባስቆጠረው ግብ በድጋሚ መሪ መሆን ችለዋል። ከግቡ መቆጠር በኋላ የአቻነት ግብ ፍለጋ የተጉት ሆሳዕናዎች በለስ ሳይቀናቸው ቀርቷል። ጨዋታውም በወልቂጤ 2-1 አሸናፊነት ተጠናቋል።

በዕለቱ ጨዋታውን በሚመሩት አርቢትር ውሳኔ አሰጣጥ ክፉኛ ሲበሳጩ የነበሩት የሀዲያ ሆሳዕና ደጋፊዎች በመጀመሪያው አጋማሽ ማብቂያ ላይ ጨዋታው እንዲቋረጥ ምክንያት የሆኑ ሲሆን ከሁለተኛው አጋማሽ መጠናቀቅ በኃላም በዕለቱ ዳኛ እንዲሁም በቡድናቸው ላይ ባሰሙት ተቃውሞ ወደ ሜዳ ውስጥ አላስፈላጊ ቁሶችን በመወርወራቸው ምክንያት ልዩ ኃይል ጣልቃ በመግባት በአስለቃሽ ጭስ ጭምር እርምጃ እንዲወስድ ሆኗል። በሁኔታውም በእንግዳው ቡድን ደጋፊዎች እና ተሽከርካሪ ላይ ጉዳት ደርሷል። ሆኖም ሁኔታው ይበልጥ ወደከፋ ደረጃ ሳይሸጋገር የሆሳዕና ቡድን አመራሮች እና የፀጥታ ኃይሉ በትብብር ሊቆጣጠሩት ችለዋል። የተከሰተው ሁኔታም ለክለቡ እና ለአወዳዳሪው አካል ትልቅ የቤት ሥራ ጥሎ ያለፈ ሆኗል።

© ሶከር ኢትዮጵያ