ድሬዳዋ ከተማ ለተጫዋቾቹ ማስጠንቀቂያ መስጠቱን ቀጥሎበታል

በተደጋጋሚ ለተጫዋቾቹ የማስጠንቀቂያ ደብዳቤን እየሰጠ የሚገኘው ድሬዳዋ ከተማ አሁን ደግሞ ለአጥቂው ዳኛቸው በቀለ የፅሁፍ ሰጥቷል፡፡

በውድድር ዓመቱ ወጣ ገባ በሆነ የውጤት ጎዳና ላይ የሚገኘው የአሰልጣኝ ስምኦን ዓባዩ ድሬዳዋ ከተማ በተጫዋቾቹ ላይ የማስጠንቀቂያ እርምጃ በሚወስድባቸው ወቅቶች መጠነኛ መሻሻሎችን ሲያሳይ የተስተዋለ ሲሆን ከዚህ ቀደም ለቢኒያም ጡመልሳን፣ ከድር አዩብ፣ ፈርሀን ሰዒድ፣ ፍሬድ ሙሸንዲ እና ዘንድሮ ክለቡን ለቀላቀለው ናይጄሪያዊው አጥቂ ባጅዋ አዴሰገን (ለሁለት ጊዜያት) እና የአሰልጣኞች ቡድን አባላትን ጨምሮ ማስጠንቀቂያ መስጠቱ አይዘነጋም። አሁን ደግሞ በርካታ ጨዋታዎች ላይ ተጠባባቂ ሲሆን ለምንመለከተው አጥቂው ዳኛቸው በቀለ ማስጠንቀቂያ መስጠቱን በይፋዊ የፌስቡክ ገፁ ክለቡ አስታውቋል፡፡ ክለቡ እንደገለፀው ከሆነ ተጫዋቹ በሜዳ ላይ እያሳየ የመጣው አቋሞ አመርቂ አይደለም ይህ ካልሆነ ግን በውሉ መሠረት ወደ ተፈለገው እርምጄ እንገባለንም ሲል ክለቡ በማስጠንቀቂያው ጠቁሟል፡፡

ከክለቡ ጋር በተያያዘ ሶከር ኢትዮጵያ ባገኘችው መረጃ መሠረት ከሀያ ቀናት በኋላ በሚከፈተው የዝውውር መስኮት ክለቡ እንደሚሳተፍ የተሰማ ሲሆን አቋማቸው አስተማማኝ አይደሉም ከተባሉ ጥቂት የክለቡ ተጫዋቾች ጋር ደግሞ ሊለያይ እንደሚችልም ሰምተናል፡፡ ከዚህ በተጨማሪ ክለቡን በክረምቱ በሙከራ የተቀላቀለው እና እስከ አሁን አንድም ግብ ማስቆጠር ካልቻለው ናይጄሪያዊው አጥቂ ባጅዋ አዴሴጎን ጋር ሊለያዩ እንደሚችሉ ያገኘነው መረጃ ይጠቁማል፡፡

© ሶከር ኢትዮጵያ