ፕሪምየር ሊግ 11ኛ ሳምንት – ዐበይት ጉዳዮች (፩) | ክለብ ትኩረት

11ኛ ሳምንት የሊጉ መርሐ ግብሮች በሳምንቱ አጋማሽ ሲካሄዱ መሪ መቐለ መሪነቱን ያስቀጠለበትን፣ ቅዱስ ጊዮርጊስ ወደ ሁለተኛ ደረጃ ከፍ ያለበት ውጤቶች ተመዝግበዋል። በተጨማሪም ወልቂጤ እና ድሬዳዋ ከተማ ከወራጅ ቀጠናው የተላቀቁበትም ሳምንት ነበር። እኛም በ11ኛ ሳምንት የተመለከትናቸው ክለብ ነክ ጉዳዮችን በተከታዩ መልክ አቅርበናቸዋል።



👉 ሲዳማ ቡና በግብ ሲንበሸበሽ ወልዋሎን ምን ነክቶት ይሆን?

በ11ኛ ሳምንት በትላንትናው ዕለት በተደረገው ብቸኛ ጨዋታ ዋና አሰልጣኛቸው ዮሐንስ ሳህሌን በ5 ጨዋታ ቅጣት ያጡት ወልዋሎዎች በሀዋሳ ሰው ሰራሽ ሜዳ በሲዳማ ቡና 5-0 ሽንፈት ደርሶባቸዋል።

ዘንድሮ በቀደመ አስደናቂ አቋማቸው ላይ እንደማይገኙ ሲስተዋል የነበረው ሲዳማ ቡናዎች ፍፁም ተሻሽለው በቀረቡበት በዚህ ጨዋታ ከአጥቂዎች ጀርባ ከነበረው ዳዊት ተፈራ በሚነሱ ተደጋጋሚ ኳሶች የወልዋሎን የተከላካይ መስመር ሲያስጨንቁ የዋሉ ሲሆን የአጥቂዎች የአጨራረስ ድክመት ምስጋና ይግባ እንጂ የጨዋታው ውጤት ከዚህም በከፋ ነበር።

ከሰሞኑ ከግብ ተራርቀው የነበሩት ሦስቱም የሲዳማ ቡና አጥቂዎች ወደ ግብ አስቆጣሪነት በተመለሱበት በዚህ ጨዋታ ሲዳማ ቡናዎች ከወልዋሎ አቅም በላይ ሆነው ተስተውሏል። ሲዳማ በተመሳሳይ በ2ኛ ሳምንት የሊጉ መርሃግብር ስሁል ሽረ ላይ 4 ግቦችን በሜዳቸው ማስቆጠሩም ይታወሳል። የትላንቱ ውጤት ሰሞነኛ የውጤት መንገራገጭ ውስጥ ለሚገኙት ሲዳማ ቡና ተጫዋቾች ጥሩ የሞራል ስንቅ ይሆናቸዋል ተብሎ ይጠበቃል።

በአንፃሩ ውጤታማ በነበሩባቸው የመጀመሪያ ሳምንታት ለተጫዋቾች በየጨዋታው ይሰጡት በነበረው ተለዋዋጭ ሚና አድናቆት ሲጎርፍላቸው የሰነበቱት ወልዋሎዎች አሁን ላይ ግን ከተጫዋቾች አጠቃቀም ጋር ጥያቄዎች እየተነሱባቸው ይገኛል። ጠንካራ የነበረው የመከላከል መስመራቸው በተለይ ከወሳኙ አምበላቸው ዓይናለም ኃይለ ጉዳት በኃላ በቀላሉ በተጋጣሚዎች ሲሰበር እየተስተዋለ ቡድኑን ዋጋ እያስከፈለውም ይገኛል።



👉 ቅዱስ ጊዮርጊስ እየተሻሻለ ይገኛል

በአሰልጣኝ ሰርዳን ዝቮጂኖቭ የሚመሩት ፈረሰኞቹ ከጨዋታ ጨዋታ መሻሻል ላይ ለመገኘታቸው ሰሞነኛ ውጤታቸው ምስክር ነው። ያለፉትን ሁለት ጨዋታዎች በደጋፊያቸው ታግዘው ሙሉ ሦስት ነጥብ መያዝ የቻሉት ቅዱስ ጊዮርጊሶች በ11ኛው ሳምንት በተጠባቂው ሸገር ደርቢ ኢትዮጵያ ቡናን 1-0 በረቱበት ጨዋታ የነበራቸው የሜዳ ላይ እንቅስቃሴ በርካታ የክለቡን ደጋፊዎች ያስደሰተ ነበር። በተለይ በሁለተኛው አጋማሽ ቡድኑ ኳስን ለመንጠቅ ያደርጉት የነበረው ጥረት በተጫዋቾች ዘንድ ከዕለት ወደ ዕለት እየተሻሻለ የመጣው የመጫወት ፍላጎትና ትጋት በቀጣይ የክለቡ ደጋፊዎች ከተጫዋቾቹ ብዙ እንዲጠብቁ የሚያደርጉ ናቸው።

ላለፉት ሁለት ዓመታት ከዋንጫ የራቀው ቡድኑ ከሜዳ ውጭ ያለውን ደካማ ክብረወሰን የሚያሻሽል ከሆነና ካለው የመከላከል ጥንካሬ አንፃር በየጨዋታው ግቦችን በማስቆጠሩ የሚዘልቅ ከሆነ ዘንድሮ ለዋንጫው ከሚፉካከሩ ክለቦች በቀዳሚው ተርታ ስለመቀመጣቸው አያጠያይቅም።



👉 የወልቂጤ ከተማ ተከታታይ ድል

ተከታታይ ውጤት አልባ ጉዞ ላይ የሰነበቱት ወልቂጤ ከተማዎች በዚህኛው ሳምንት ደግሞ በርካታ አነጋጋሪ ክስተቶች በተስተናገዱበት ጨዋታ ከሜዳቸው ውጪ ሀዲያ ሆሳዕናን 2-1 በመርታት የመጀመሪያ ተከታታይ ድላቸውን በሊጉ አስመዝግበዋል።

በቶጓዊው ጃኮ አራፋት ትዕግሥታቸው የተሟጠጠ የሚመስሉት ወልቂጤዎች በጭንቅ ወቅት ተስፋ በተጣለበት ሳዲቅ ሴቾ ፊት አውራሪነት የውጤት ማንሰራራት እያሳዩ ይገኛሉ። ሳዲቅም ለሁለተኛ ተከታታይ ሳምንት ኳስን ከመረብ አዋህዷል። በውድድሩ አጋማሽ የፊት መስመራቸውን ለማጠናከር ወደ ገበያ እንደሚወጡ የሚጠበቁት አሰልጣኝ ደግአረግ ይግዛው በከፍተኛ ወጪ የመጣው ጃኮ አራፋትን ከስብስብ ውጭ በማድረግ በእነ ሳዲቅ ላይ ያሳደሩት ተስፋ እየከፈላቸው ይገኛል። በተጨማሪም ከምክትል አሰልጣኝነት ሚና በዘለለ በሁለቱ ጨዋታዎች ላይ በተጫዋችነት ቡድኑን እያገለገለ የሚገኘው አንጋፋው አዳነ ግርማ ለቡድኑ ሚዛንና የራስ መተማመንን ከፍ ስለማድረጉ መመልከት ይቻላል።



👉 የፋሲል ከነማ ደካማ የሜዳ ውጭ ውጤት

ከሜዳ ውጭ ማሸነፍ ብርቅ በሆነበት ሊጉ ለዋንጫ በሚደረገው ፉክክር ላይ በተለይም በአንፃራዊነት ከሜዳቸው ውጭ በርከት ያሉ ጨዋታዎችን የሚያሸንፉ ቡድኖች ወደ ዋንጫን ለማንሳት የተሻለ እድል እንደሚኖራቸው ለመተንበይ የሊጉን ያለፈውን ዓመት ቻምፒዮን መቐለ መመልከት በቂ ነው። ዓምና ለጥቂት ያጡትን ዋንጫ ዘንድሮ ለማሳካት የሚያልሙት ፋሲሎችም በእስካሁኑ የሊጉ ጉዞ በዚህ ረገድ በሚጠበቅባቸው ልክ እየተጓዙ አይደለም።

በዚህኛው ሳምንት ወደ ጅማ ያመሩት ዐፄዎቹ ከጅማ ያለ ሦስት ነጥብ ተመልሰዋል። ፋሲሎች የኳስ ቁጥጥር የበላይ በነበሩበት ጨዋታ የማሸነፊያ ግብ ማግኘት ሳይችሉ አሁንም ከሜዳ ውጭ ያላቸው ደካማ ጉዞን ያስቀጠለ ውጤት አስመዝግበዋል። በቀጣይም ቡድኑ በዚህ ረገድ የቤት ሥራዎች ይጠብቁታል።



👉 ችግር የማያጣው የመቐለ የአጥቂ መስመር እና የሚባክኑት የፍፁም ቅጣት ምቶች

የዐምና የሊጉ ክብራቸውን ለማስጠበቅ ጥረት እያደረጉ የሚገኙት መቐለዎች በ11ኛ ሳምንት በሜዳቸው ከስሑል ሽረ ከፍተኛ ፈተና ቢጠብቃቸውም በስተመጨረሻም በኦኪኪ አፎላቢ ግብ አሸንፈው መውጣት ችለዋል።

ባሳለፍነው ሳምንት አማኑኤል ገ/ሚካኤል በጉዳት በማጥታቸው የተነሳ ቀጥተኛ አጨዋወታቸው ሳንካ ገጥሞት ሽንፈት ያስተናገዱ ሲሆን በዚህኛው ሳምንት ደግሞ ናይጄሪያዊው ግዙፍ አጥቂ ኦኪኪ አፎላቢ ከግቧ መቆጠር በኃላ መለያውን በማውለቁ በሁለተኛ ቢጫ ከሜዳ ሊወገድ ችሏል። ይህም በቀጣይ ቡድኑ ከሜዳው ውጭ ጅማን በሚገጥምበት ጨዋታን ሊያከብድበት ይችላል ተብሎ ይጠበቃል።

የቡድን ጥልቀት ችግር ያለበት ቡድኑ በተለይ የአጥቂ መስመሩ ችግሮች አላጡት ብለዋል። ለሳምንታት ከግብ ርቆ ሰንብቶ ከሰሞኑ ወደ ግብ አግቢነት የተመለሰው ኦኪኪ ለቡድኑ መልካም ዜና ይዞ ቢመጣም በሁለተኛ ቢጫ የቀድሞ ክለቡን አለመግጠሙ ጥሩ የሚባል አጋጣሚ አይደለም።

በተያያዘም ቡድኑ በሊጉ ካሉ ቡድኖች ከዐምና አንስቶ በፍፁም ቅጣት ምት አጠቃቀም ረገድ የጎሉ እንከኖች ያሉበት ቡድን ሆኗል። ባለፉት ሶስት ሳምንታት ውስጥ ቡድኑ ያገኛቸውን ሁለት የፍፁም ቅጣት ምቶች (ኦኪኪ በዚህ ሳምንት ያመከነውን ጨምሮ) የቡድኑ ተጫዋቾች ወደ ግብነት መቀየር ሳይችሉ ቀርተዋል። ይህም እንደ ረቡዕ አይነት እጅግ ፈታኝ ጨዋታዎች ላይ ለቡድኑ ጨዋታዎችን ማክበዱ አይቀሬ ነው።



👉 በሽርፍራፊ ሰከንዶች ነጥብ ያጡት የድቻና አዳማ አሳዛኝ አጨራረስ

በ11ኛ ሳምንት ሀዋሳ እና ባህርዳር ስታዲየሞች ላይ በአቻ ውጤት ሊጠናቀቁ ተቃርበው የነበሩ ጨዋታዎች በመጨረሻ ሽርፍራፊ ሰከንዶች በተገኙ ግቦች የውጤት ለውጥ ተመዝግቦቧቸው በባለሜዳዎቹ የበላይነት ሊጠናቀቁ ችለዋል። አስቀድመው በሚቆጠሩ ግቦችና በጠባብ ውጤት መሸናነፍ በተለመደበት ሊግ መሰል የመጨረሻ ደቂቃ ግቦች የተለመዱ አይደሉም። ዘንድሮ ግን መጠነኛ ለውጦች ያሉ ይመስላል፤ የቅርብ ጊዜ ትውስታችን የሆነውና በተጨማሪ ደቂቃዎች በተቆጠሩ ሁለት ግቦች ሰበታ ከፋሲል 3 አቻ የተለያዩበትን ጨዋታ ጨምሮ በዚህኛው ሳምንት ፍቃዱ ወርቁ እና አለልኝ አዘነ ለየክለቦቻቸው ባስቆጠሯቸው ግቦች ባህርዳር አዳማን እንዲሁም ሀዋሳ ድቻን የረቱባቸው ጨዋታዎች በሊጉ አዲስ ክስተት ናቸው። መቐለ እና ወልቂጤ ያሸነፉባቸው ጎሎች የተገኙትም በመጨረሻዎቹ 10 ደቂቃዎች ነበር።


©ሶከር ኢትዮጵያ