ቅድመ ዳሰሳ | ስሑል ሽረ ከ ሀዋሳ ከተማ

ስሑል ሽረዎች ሀይቆቹን የሚያስተናግዱበት ጨዋታን እንደሚከተለው ዳሰነዋል።

ከሰባት ሽንፈት አልባ ጉዞዎች በኃላ በተከታታይ ነጥብ ጥለው ከደረጃቸው የወረዱት ስሑል ሽረዎች ከመሪዎቹ ላለመራቅ እና በድጋሚ ወደ ድል ለመመለስ ወደ ሜዳ ይገባሉ ተብሎ ይጠበቃል።

የስሑል ሽረ ያለፉት 5 ጨዋታዎች አቋም (ከቅርብ ወደ ሩቅ)
ተሸነፈ አቻ አሸነፈ አሸነፈ አሸነፈ

ባለፉት ሳምንታት የማይቀያየረው የመልሶ ማጥቃት አጨዋወት የነበራቸው ስሑል ሽረዎች በነገው ጨዋታ በአጨዋወታቸው ቁልፍ ሚና ያለው ዲድዬ ለብሪ በቅጣት ቢያጡም ከተለመደው አቀራረብ በተለየ ወደ ጨዋታው ይቀርባሉ ተብሎ አይገመትም።

ባለፉት ሁለት ሳምንታት አጨዋወቱን እንደ ቀደሙ በተሳካ ሁኔታ መተግበር ያልቻሉት ስሑል ሽረዎች ዕድሎች ወደ ግብነት የመቀየር  ከፍተኛ ድክመታቸውን ፈተው መቅረብ ካልቻሉ ከጨዋታው ነጥብ ይዞ መውጣት ቀላል አይሆንላቸውም። ባለፉት ሁለት ጨዋታዎች በርካታ ንፁህ ዕድሎች መፍጠር ያልቻለው የቡድኑ አማካይ ክፍልም ጠንካራው የሀዋሳ ተከላካይ ክፍል አልፎ ዕድሎች የመፍጠር  ፈተና ቀላል ይሆንለታል ተብሎ አይጠበቅም።

አሰልጣኝ ሳምሶን አየለ በነገው ጨዋታ ዲዲዬ ለብሪ እና ወደ ቱርክ ለሙከራ ያመራው ምንተስኖት አሎ ግልጋሎትን አያገኙም። ያሳር ሙገርዋም ከውል ጋር በተያያዘ በዚህ ጨዋታ ላይ አይሰለፍም።

የሀዋሳ ከተማ ያለፉት 5 ጨዋታዎች አቋም (ከቅርብ ወደ ሩቅ)
አሸነፈ ተሸነፈ አሸነፈ አቻ አቻ

ባለፉት ጨዋታዎች ባሳኳቸው ነጥቦች ወደ መሪዎቹ የተጠጉት ሀይቆቹ ባለፉት ጨዋታዎች ጥሩ መሻሻል ካሳዩት ቡድኖች ውስጥ ይጠቀሳሉ። ፈጣን አጥቂዎቹን መሰረት ያደረገ አጨዋወት የሚከተሉት በነገው ጨዋታ የመስፍን ታፈሰ ግልጋሎት አለማግኘታቸው ለቡድኑ መጥፎ ዜና ነው። በሜዳቸው በአብዛኛው የኳስ ቁጥጥር ብልጫ ወስደው ወደ አጥቂዎቹ በሚሻገሩ ኳሶች ለማጥቃት ጥረት የሚያደርጉት ሀዋሳዎች በነገው የሜዳ ውጭ ጨዋታ ግን አጨዋወቱን መርጠው ይገባሉ ተብሎ አይጠበቅም።

በዚህም ቡድኑ በዋነኝነት የተጋጣሚን መልሶ ማጥቃት ለመመከት እምብዛም ከራሱ ሜዳ ሳይነቅል ለአጥቂው ብሩክ በየነ በሚሻገሩ ረጃጅም ኳሶች የተመሰረት አቀራረብ ይዞ ይቀርባል ተብሎ ይገመታል። አሰልጣኝ አዲሴ ካሳ ከግዜ ወደ ግዜ ጥሩ መሻሻል እያሳየ የሚገኘው የአማካይ ክፍላቸው እንደ ተጋጣምያቸው አቀራረብ የሚወሰን በማጥቃቱ ላይ ያሳትፋሉ ተብሎ ይጠበቃል። ሆኖም ቡድኑ መስፍን ታፈሰ በጉዳት ማጣቱ በማጥቃት አጨዋወቱ ላይ ክፍተት ይፈጥርበታል።

ሀይቆቹ በነገው ጨዋታ መስፍን ታፈሰ እና እስራኤል እሸቱን በጉዳት አያገኙም።

እርስ በርስ ግንኙነት

ሁለቱ ቡድኖች ሁለት ጊዜ (ዓምና) ተገናኝተው ሀዋሳ ላይ ሀዋሳ 6-1 ሲያሸንፍ ሽረ ላይ ሽረ 4-0 አሸንፏል።

ግምታዊ አሰላለፍ 

ስሑል ሽረ (4-2-3-1)

ወንድወሰን አሸናፊ

ዓወት ገብረሚካኤል – ዮናስ ግርማይ – አዳም ማሳላቺ – ረመዳን የሱፍ

ነፃነት ገብረመድህን – አክሊሉ ዋለልኝ

ዓብዱለጢፍ መሐመድ – ሀብታሙ ሽዋለም – ብሩክ ሐድሽ

ሳሊፍ ፎፋና 

ሀዋሳ ከተማ (4-2-3-1)

ዳንኤል ደርቤ  – መሳይ ጳውሎስ – ላውረንስ ላርቴ – ያኦ ኦሊቨር

 ተስፋዬ በቀለ – አለልኝ አዘነ 

ሄኖክ ድልቢ – ዘላለም ኢሳይያስ – ሄኖክ አየለ

ብሩክ በየነ

©ሶከር ኢትዮጵያ