ቅድመ ዳሰሳ | ወልቂጤ ከተማ ከ ባህር ዳር ከተማ

በ12ኛ ሳምንት የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ መርሐ ግብር ወልቂጤ ከተማ ከ ባህር ዳር ከተማ የሚያደርጉትን ጨዋታ እንደሚከተለው ተመልክተነዋል። 

በሊጉ 10ኛ ደረጃ ላይ የተቀመጡት ወልቂጤ ከተማዎች በተከታታይ ያስመዘገቡትን የሜዳ ላይ እና የሜዳ ውጪ ድል ለመድገደም 9 ሰዓትን ይጠባበቃሉ።

የወልቂጤ ከተማ ያለፉት 5 ጨዋታዎች አቋም (ከቅርብ ወደ ሩቅ)
አሸነፈ አሸነፈ ተሸነፈ ተሸነፈ ተሸነፈ

በአሰልጣኝ ደግአረገ ይግዛው የሚመራው ቡድኑ ወጣ ገባ አቋም በማሳየት የሊጉን የመጀመሪያ መርሐ ግብሮች ሲያከናውን ቆይቷል። ነገር ግን ቡድኑ ወደ ሀዋሳ አምርቶ 3-1 ከተሸነፈ በኋላ የተደረጉትን ሁለት ተከታታይ ጨዋታዎች (ከድሬዳዋ ከተማ እና ሀዲያ ሆሳዕና) በማሸነፍ ከተደቀነበት የወራጅነት ስጋት ፈቀቅ ብሏል።

በሊጉ ዝቅተኛ ግብ ተጋጣሚ ላይ ካስቆጠሩ ክለቦች መካከል ቀዳሚ የሆኑት ወልቂጤዎች (6) ከፍተኛ የግብ አይናፋርነት ይስተዋልባቸዋል(እስከ 10ኛ ሳምንት በተደረጉ ጨዋታዎች ወልቂጤ ከአንድ ጎል በላይ ተጋጣሚ ላይ አስቆጥሮ አያቅም)። በተለይ በጥብቅ የመከላከል አደረጃጀት የሚጫወት ቡድን ሲገጥማቸው መፍትሄዎችን ለማምጣት ይቸገራሉ። 

ቡድኑ ወደ ሆሳዕና አምርቶ ባሸነፈበት ጨዋታ የተከተለውን የረጃጅም ኳሶች እና የመልሶ ማጥቃት ስልቶች ሒደት በነገውም ጨዋታ ይደግማል ተብሎ ይጠበቃል። እርግጥ ቡድኑ ይህንን አጨዋወት በሀዲያ ሆሳዕናው ጨዋታ ብቻ የተከተለው ባይሆንም ተጋጣሚው ከሚከተለው ኳስን የመቆጣጠር መርህ አንፃር የጨዋታ መንገዱን በባለፉት ጨዋታዎች አይነት ይቃኛል ብሎ እንዲታሰብ አድርጎታል። በዚህም ሳዲቅ ሴቾ እና ጫላ ተሺታ ላይ ያነጣጠሩ ኳሶች በማብዛት የተጋጣሚን ጊዜ ከባድ ለማድረግ ይጥራሉ ተብሎ ይታሰባል።

ባለሜዳዎቹ ወልቂጤ ከተማዎች በነገው ጨዋታ ይበልጣል ሽባባው እና አዳነ ግርማ በጉዳት ምክንያት አያገኙም።

የባህር ዳር ከተማ ያለፉት 5 ጨዋታዎች አቋም (ከቅርብ ወደ ሩቅ)
አሸነፈ ተሸነፈ አሸነፈ ተሸነፈ አሸነፈ

ከሜዳቸው ውጪ ምንም ጨዋታ እስካሁን ያላሸነፉት ባህር ዳር ከተማዎች የመጀመሪያ የሜዳቸው ውጪ ድል ለማግኘት እና ከደረጃ ሰንጠረዡ አናት ላለመራቅ ወደ ወልቂጤ አምርተዋል።

ከሜዳ ውጪ በሚደረጉ ጨዋታዎች በከፍተኛ ሁኔታ የሚፈተነው ቡድኑ ነገም በወልቂጤ ስታዲየም ሊቸገር ይችላል። በተለይ ተጋጣሚው ወልቂጤ ከተማ ካለው ጠንካራ የመከላከል እና ስል የመልሶ ማጥቃት አጨዋወት አንፃር ችግር ውስጥ ሊገባ ይችላል። 

ተጋጣሚ ላይ ካስቆጠረው ጎል እኩል ግብ ያስተናገደው (18) ባህር ዳር ከተማ የሚከተለው የመከላከል አደረጃጀት በመጠኑ ዋጋ እያስከፈለው ይገኛል። በተለይ በማጥቃት አጨዋወት ላይ ተጠምደው የሚቆዩት የባህር ዳር ከተማ አማካዮች ለተከላካይ ክፍሉ የሚገባውን ሽፋን አለመስጠታቸው ቡድኑን ችግር ውስጥ እየከተተው ይገኛል። ነገም አማካዮቹ ወልቂጤ ሊከተል የሚችለውን የጨዋታ እቅድ አንብበተው ተገቢ ሽፋን ለቡድናቸው የኋላ መስመር ካልሰጡ ግብ ሊያስተናግዱ ይችላሉ።

በይበልጥ በግራ መስመር አጋድሎ ጥቃቶችን ለመሰንዘር የሚሞክረው ቡድኑ ነገም ለባለሜዳዎቹ ከፍተኛ የራስ ምታት ሊሆን ይችላል። በተለይ ደግሞ በዚህ መስመር የሚሰለፈው ግርማ ዲሳሳ ከመስመር እየሰበረ በመግባት የሚያደርጋቸው ሙከራዎች፣ የሚያሻግራቸው ኳሶች እና የሚያስጀምራቸው የአንድ ሁለት ቅብብሎች ወልቂጤን ሊረብሽ ይችላል።

በጉዳት እየታመሰ የሚገኘው ባህር ዳር ከተማ አምስት ወሳኝ ተጨዋቾቹን በነገው ጨዋታ አያሰልፍም። በዚህም ወሰኑ ዓሊ፣ ፍፁም ዓለሙ፣ አቤል ውዱ፣ አዳማ ሲሶኮ እና ሳለ አምላክ ተገኝ ወደ ወልቂጤ አልተገለዙም። ከአምስቱ ተጨዋቾች በተጨማሪ በቅዱስ ጊዮርጊሱ ጨዋታ ቀይ ካርድ ያየው ሀሪስተን ሄሱ ቅጣቱን ባለመጨረሱ ወደ ሜዳ አይገባም።

እርስ በእርስ ግንኙነት

– ሁለቱ ቡድኖች በነገው ጨዋታ ለመጀመሪያ ጊዜ ነው የሚገናኙት።

ግምታዊ አሰላለፍ

ወልቂጤ (3-5-2)

ይድነቃቸው ኪዳኔ

ቶማስ ስምረቱ – ዐወል መሀመድ – ዳግም ንጉሴ

አዳነ በላይነህ – አሳሪ አልመሀዲ – በረከት ጥጋቡ – ኤፍሬም ዘካርያስ – ሙሀጅር መኪ

ጫላ ተሺታ – ሳዲቅ ሴቾ

ባህር ዳር ከተማ (4-3-3)

ጽዮን መርዕድ

ሚኪያስ ግርማ – ሄኖክ አቻምየለህ – ሰለሞን ወዴሳ – ሳሙኤል ተስፋዬ

ሳምሶን ጥላሁን – ፍ/ሚካኤል ዓለሙ – ዳንኤል ኃይሉ

ዜናው ፈረደ – ማማዱ ሲዲቤ – ግርማ ዲሳሳ

© ሶከር ኢትዮጵያ