ነገ ብሩንዲን የሚገጥመው የኢትዮጵያ ከ20 ዓመት በታች የሴቶች ብሔራዊ ቡድንን አስመልክቶ መግለጫ ተሰጠ

ነገ ቡሩንዲን በባህር ዳር ዓለማቀፍ ስታዲየም የሚገጥመው የሴቶች ከ20 ዓመት በታች ብሔራዊ ቡድኑ በዋና አሰልጣኙ እና አምበሉ አማካኝነት መግለጫ ሰጥቷል።

ፓናማ እና ኮስታሪካ በጣምራ ለሚያዘጋጁት የ2020 የሴቶች ከ20 ዓመት በታች ዓለም ዋንጫ ውድድር ላይ ለመሳተፍ የቅድመ ማጣሪያ ጨዋታውን እያደረገ የሚገኘው የኢትዮጵያ ከ20 ዓመት በታች የሴቶች ብሄራዊ ቡድን ነገ የብሩንዲ አቻውን ይገጥማል። ከሁለት ሳምንታት በፊት የመጀመሪያ የቅድመ ማጣሪያ ጨዋታውን ወደ ቡጂንቡራ በማቅናት ያደረገው ቡድኑ አምስት ግቦችን አስቆጥሮ መመለሱ ይታወሳል። ነገም የመልስ ጨዋታውን 10 ሰዓት በባህር ዳር ዓለማቀፍ ስታዲየም ያከናውናል። ይህንን ተከትሎ የቡድኑ አሰልጣኝ ፍሬው ኃይለገብርኤል እና የቡድኑ አምበል እመቤት አዲሱ በሶሊያና ሆቴል መግለጫ ሰጥተዋል።

በቅድሚያ የቡድኑ ዋና አሰልጣኝ ፍሬው ኃይለገብርኤል ስለ መጀመሪያው ጨዋታ፣ ስለ ዝግጅት ጊዜው፣ ስለ ነገው ጨዋታ እና ተያያዥ ጉዳዮች ማብራሪያ ሰጥቷል። 
“ከብሩንዲ መልስ በኢትየጵያ ሆቴል በመቀመጥ ዝግጅታችንን በአዲስ አበባ ለጥቂት ቀናት አከናውነናል። ከዛም ደግሞ ወደ ባህር ዳር በመምጣት በጥሩ ሜዳ ላይ ልምምዶችን በተገቢው መንገድ ሰርተናል። ሁሉም ተጨዋቾች ለነገው ጨዋታ ዝግጁ እንደሆኑ እና በጥሩ ብቃት ላይ እንደሚገኙ ታዝቢያለሁ። ሁላችንም የባለፈው ውጤት እንዳያኩራራን እና ትኩረታችን ለነገው ጨዋታ እንዲሆን ተነጋግረናል።”

ከአሰልጣኙ በመቀጠል የቡድኑ አምበል እመቤት አዲሱ ሃሳቧን በአጭሩ በስፍራው ለተገኙ ጋዜጠኞች አጋርታለች።
“ብሩንዲ በነበረን ቆይታ ጥሩ ጊዜ አሳልፈናል። በውጤትን ደረጃ ይዘን የመጣነው ውጤት ጥሩ ውጤት ነው። እኛ ተጨዋቾች በአጨዋወት ደረጃ አሰልጣኙ የሚፈልገውን ታክቲክ ተግብረናል ብለን እናስባለን። ይህ ቢሆንም ግን ደካማ ጎን አልነበረንም ማለት አደለም። በመጀመሪያው ጨዋታ የነበሩብንን ክፍተቶች ተንተርሰን ልምምዶችን ስንሰራ ቆይተናል። በአጠቃላይ ለነገው ጨዋታ ሁሉም ተጨዋቾች ዝግጁ ናቸው።”

ከአሰልጣኙ እና ከአምበሏ አጭር ንግግር በኋላ የተለያዩ ጥያቄዎች ከጋዜጠኞች ተነስተው ምላሽ ተሰጥቷል።


ቡድኑ ስላለው ጠንካራ ጎን እና ስለ ተጨዋቾቹ እንቅስቃሴ?

የቡድኑ ዋነኛ ጠንካራ ጎን የተጨዋቾቹ አቅም ነው። በቡድኑ ውስጥ ያሉት ተጨዋች የሚገርም አቅም አላቸው። መጀመሪያም ተጨዋቾቹን ስናመጠ ያላቸውን አቅም አይተን ነው። በመጀመሪያው ጨዋታም ተጨዋቾቹ ያሳዩት እንቅስቃሴ ጥሩ ነበር። በተለይ የብሩንዲን የጨዋታ መንገድ ያጠፉበት ሂደት ድንቅ ነበር። በቡድኑ ውስጥ ያሉት አብዛኞቹ ተጨዋቾች አዳዲሶች ናቸው። በጨዋታው  እኛ ተነጋግረን የገባነው ነገር አጋጣሚዎችን መጠቀም የሚለው ጉዳይ ላይ ነበር። ይህም ተሳክቶልን ውጤት አምጥተናል። ይህ ነገር ደግሞ ብሩንዲዎችን በአምሮ ደረጃ አዳክሟቸዋል።

ስለ ተጋጣሚ ቡድን?

የብሩንዲ ብሄራዊ ቡድን የሚናቅ ቡድን አይደለም። እኛ ቀድመን ግብ አስቆጥረን ተነሳሽነታቸውን አጠፋንባቸው እንጂ የሚናቁ አልነበሩም። የውጪ እድልም አግኝተው የሚጫወቱ ተጨዋቾች አሉት። ነገር ግን እኛ የተሻልን ስለነበርን ነው ያሸነፍናቸው። በእኛ ሃገር እድሉን ስላላገኙ እንጂ የተሻሉ ነገሮችን መፍጠር የሚችሉ ተጨዋቾች አሉ። በአጠቃላይ እነሱ በግል የተሻሉ ነገሮችን ለመፍጠር ይሞክራሉ እኛ ደግሞ እንደ ቡድን የተሻሉ ነገሮችን ለመስራት እንጥራለን። 

ስለ ቡድኑ እቅድ?

እግር ኳስ ቀድሞ የሚተነበይ አደለም። ፊት ለፊትህ ባለው 90 ደቂቃ የሚወሰን እንጂ። እኛ ገና ወደ ቀጣይ ዙር ማለፋችንን አላረጋገጥንም። ስለዚህ አሁን ላይ ያለን እቅድ ከፊታችን ያለውን የነገውን ጨዋታ ጨርሰን መውጣት የሚል ነው። ነገር ግን ቡድኑ ቀን በቀን እያደገ ይሄዳል ብዬ ስለማስብ ወደ ፊት የተሻለ ነገር ይኖረናል።

ነገ ስለሚከተለው አጨዋወት?

ነገ ማጥቃት ላይ የተመረኮዘ አጨዋወት ለመተግበር እንሞክራለን። እንደገለፅኩት ጨዋታው አልቋል ብለል ስለማናስብ የነገውን ጨዋታ ለማሸነፍ እንሞክራለን። ስለዚህ ከመጀመሪያው ደቂቃ አንስቶ ለማጥቃት እና ግቦችን ለማስቆጠር እንጥራለን። ይህ ማለት ግን መከላከሉን እንረሳለን ማለት አይደለም። 

በመጨረሻም የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌደሬሽን የህዝብ ግንኙነት ሃላፊ አቶ ባህሩ ጥላሁን በብሩንዲዎች በኩል ስለተፈጠረው ችግር ማብራሪያ ሰጥተዋል። “የብሩንዲ ብሄራዊ ቡድን ዛሬ 5 ሰዓት ባህር ዳር መግባት ነበረበት። ነገር ግን ራሳቸው በቆረጡት ተያያዥ በረራ ወደ ድሬደዋ አምርተዋል። ድሬዳዋ አየር ማረፊያ ደግሞ የፌደሬሽኑ ተወካይ የለም። በካፍ እና በፊፋ ውድድሮች አንድ ብሄራዊ ቡድን ሲወዳደር የሚጫወትበት ሜዳ ቀድሞ ይገለፃል። እኛም ከመጀመሪያው ጨዋታ አስቀድመን ውድድሩን የምናደርግበትን ሜዳ ለብሩንዲዎን አሳውቀናል። ለእነሱ ብቻ ሳይሆን ለካፍም ለፊፋም የውድድሩን ቦታ አሳውቀናል። ይህ ብቻ ሳይሆን ብሩንዲ በነበርንበት ጊዜ ባህር ዳር ከአዲስ አበባ ስንት ኪሎ ሜትር ይርቃል የሚል ጥያቄን ሲጠይቁን ነበር። ስለዚህ የተፈጠረው ችግር የእነሱ የአስተዳደር ችግር ነው። ችግሩ በፌደሬሽኑ የተፈጠረ ነው እየተባለ የሚወራው ወሬ ፍፁም ከእውነት የራቀ ነው።”

ከጉዞ መዘግየት ጋር በተገናኘ የብሩንዲ ብሄራዊ ቡድን አሰልጣኝ እና አምበል በጋዜጣዊ መግለጫው ላይ ሳይገኙ ቀርተዋል።

እሁድ ጥር 14 ባህር ዳር ገብቶ በየቀኑ(ጠዋት) ጠንካራ ልምምድ ሲሰራ የነበረው ቡድኑ ዛሬ ማለዳ ለ1 ሰዓት የቆየ ልምምድ አከናውኗል። በልምምድ መርሃ ግብሩም ቡድኑ የቆመ ኳስ አጠቃቀም ላይ ያተኮሩ ስራዎችን በአትኩሮት እንደሰራ ታይቷል። ከ17 ዓመት በታች ብሄራዊ ቡድን ጥሪ ቀርቦላቸው የነበረው ገነት ሃይሉ፣ ነፃነት ፀጋዬ፣ አረጋሽ ካልሳ፣ ቤቲ ዘውዴ ከቀናት በፊት ቡድኑን እንደተቀላቀሉ ተሰምቷል።

©ሶከር ኢትዮጵያ