ሪፖርት| ስሑል ሽረዎች ወደ አሸናፊነት ተመልሰዋል

በኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ 12ኛ ሳምንት መቐለ ላይ ሀዋሳ ከተማን ያስተናገደው ስሑል ሽረ 3-0 በማሸነፍ ወደ ድል ተመልሷል።

ሽረዎች በመቐለ ሽንፈት ከደረሰበት ስብስብ መካከል ሸዊት ዮሐንስ፣ ዲዲዬ ለብሪ እና ያሳር ሙገርዋን በረመዳን የሱፍ፣ ሙሉዓለም ረጋሳ እና ስዒድ ሐሰን ተክተው ሲገቡ ሀይቆቹ ወላይታ ድቻን ካሸነፈው ስብስብ መስፍን ታፈሰን በዳንኤል ደርቤ ብቻ ተክተው ወደ ሜዳ ገብተዋል።

ሁለቱም ቡድኖች እየተፈራረቁ የበላይነት በወሰዱበት ጨዋታ ስሑል ሽረዎች በመጀመርያዎቹ ሀያ ደቂቃዎች ብልጫ ወስደው ሲጫወቱ እንግዶቹ ሀዋሳዎች በተቀረው የመጀመርያው አጋማሽ ደቂቃዎች ብልጫ አሳይተው የግብ ሙከራዎችም አድርገዋል።

ዓወት ገብረሚካኤል ከመስመር አሻምቶት ሳሊፍ ፎፋና በግንባሩ ገጭቶ ባደረገው እጅግ ለግብ የቀረበ ሙከራ ጥቃታቸውን የጀመሩት ሽረዎች ምንም እንኳ የተለመደው ፈጣን የመልሶ ማጥቃት አጨዋወታቸው ለመተግበር ቢቸገሩም ብልጫ በወሰዱባቸው ደቂቃዎች የተሻለ ኳስን ተቆጣጥረው ተጫውተዋል። በተጠቀሱት ደቂቃዎችም የአንጋፋው ሙሉዓለም ረጋሳ ድርሻ የጎላ ነበር። በሀያኛው ደቂቃም ነፃነት ገብረመድህን ከአማካዩ ሀብታሙ ሸዋለም የተነሳውን ቅጣት ምት በግምባሩ በማስቆጠር ቡድኑን ቀዳሚ ማድረግ ችሏል።

ከግቡ በኋላ ሽረዎች ተዳክመው የታዩ ሲሆን ሀይቆቹ በአንፃሩ በቀጥተኛ አጨዋወት የስሑል ሽረን ተከላካይ ክፍል ሲፈትኑ ውለዋል። ቡድኑ ምንም እንኳ ግብ ባያስቆጥርም በበርካታ አጋጣሚዎች አቻ ለመሆን ተቃርቦ ነበር። ከነዚህም ሄኖክ አየለ በረጅሙ የተሻገረውን ኳስ ተጠቅሞ ከግብ ጠባቂው አንድ ለአንድ ተገናኝቶ በመምታት ወንድወሰን አሸናፊ በሚያስደንቅ ብቃት ያወጣው ኳስ እና በተመሳሳይ አጥቂው ከዘልአለም ኢሳይያስ የተሻገረለት ንፁህ የግብ ዕድል መቶ ወንድወሰን አሸናፊ የመለሰው ኳስ በእንግዶቹ በኩል አስቆጪ ሙከራዎች ነበሩ። ብሩክ በየነ በመጀመርያው አጋማሽ የመጨረሻ ደቂቃ ከጠበበ አንግል መትቶ አዳም ማሳላቺ ከመስመሩ የመለሰው ኳስም ሀዋሳ ከተማን አቻ ለማድረግ የተቃረበ ሙከራ ነበር።

ስሑል ሽረዎች ተሻሽለው በገቡበት ሁለተኛው አጋማሽ ምንም እንኳ በርካታ ሙከራዎች ባይታይበትም በሁለቱም ቡድኖች በኩል የታየው የጨዋታ መንፈስ ጨዋታውን ከመጀመርያው አጋማሽ የተሻለ እንዲሆን አድርጎታል።
ስሑል ሽረዎች በጨዋታው ኮከብ በነበረው አብዱለጢፍ መሐመድ አማካኝነት በርካታ ዕድሎች ቢፈጥሩም በሳሊፍ ፎፋና የቦታ አያያዝ ችግር እና በሀዋሳ ከተማ ተከላካዮች ከፍተኛ ተጋድሎ ግብ ከመሆን ተርፈዋል። በተለይም ፈጣኑ አማካይ በመስመር ሰብሮ ገብቶ ለሳሊፍ ፎፋና አሻግሮለት አጥቂው ያመከነው ኳስ እና በተመሳሳይ አማካዩ በሁለት አጋጣሚዎች ከመስመር አሻግሯቸው ያኦ ኦሊቨር እና ላውረንስ ላርቴ ያወጧቸው ኳሶች ንፁህ የግብ ዕድሎች ነበሩ።

በጨዋታው ጥቂት ለግብ የቀረበ ሙከራ ያደረጉት ሀዋሳ ከተማዎችም በአለልኝ አዘነ ከርቀት ሙከራ አድርገው ወንድወሰን አሸናፊ መልሶባቸዋል። ከዛ ውጭም መሳይ ጳውሎስ ከዘላለም ኢሳይያስ የተሻገረውን ኳስ በግንባሩ ገጭቶ ያደረገው ሙከራ ይጠቀሳል።

በሰባኛው ደቂቃ ሀይልአብ ኃይለሥላሴን ቀይረው ያስገበት ስሑል ሽረዎች በብዙ መንገድ ተሻሽለው ታይተዋል። ተጫዋቹ በፍጥነት ረገድ ቀርፋፋ የሚባል አይነት ቢሆንም በተለይ በቡድኑ የመልሶ ማጥቃት አጨዋወት ላይ ጉልህ ድርሻ ነበረው። በሰማንያ አንደኛው ደቂቃም በጨዋታው በርካታ ዕድሎች ያባከነው ሳሊፍ ፎፋና መድሀኔ ብርኃኔ ከመስመር ያሻገረለትን ኳስ በግንባሩ በማስቆጠር የቡድኑ መሪነት ወደ ሁለት ከፍ ማድረግ ችሏል።

ስሑል ሽረዎች ከሁለተኛው ግብ በኃላ ብዙም ሳይቆዩ በሰማንያ ስምንተኛው ደቂቃ ሶስተኛውን ግብ አስቆጥረዋል። ሳሊፍ ፎፋና በሳጥን ውስጥ ያገኘውን ኳስ ለአብዱለጢፍ መሐመድ አቀብሎት የመስመር አማካዩ አስቆጥሮታል። ጨዋታውም በሽረ 3-0 አሸናፊነት ተጠናቋል።

ውጤቱን ተከትሎ ስሑል ሽረዎች ከሽንፈት አገግመው ነጥባቸው ወደ አስራ ዘጠኝ ከፍ ሲያደርጉ ሀይቆቹ በነበሩበት አስራ ስድስት ነጥብ ረግተዋል።

© ሶከር ኢትዮጵያ