ሪፖርት| ፈረሰኞቹ ሲዳማ ላይ የጎል ናዳ አውርደው የሰንጠረዡ አናት ላይ ተቀመጡ

በአዲስ አበባ ስታዲየም በተካሄደው የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ 12ኛ ሳምንት ቅዱስ ጊዮርጊስ ከሲዳማ ቡናን ያገናኘው ጨዋታ ፈረሰኞቹ የዓመቱን ከፍተኛ የጎል መጠን አዝንበው 6-2 በሆነው ውጤት ማሸነፍ ችለዋል።

አሰልጣኝ ሰርዳን ዝቪጅኖቭ በሸገር ደርቢ ኢትዮጵያ ቡና 1-0 ከረታው ስብስባቸው ምንም ዓይነት ለውጥ ሳያደርጉ ወደ ሜዳ ሲገቡ በተመሳሳይ አሰልጣኝ ዘርዓይ ሙሉ ወልዋሎን 5-0 ከረመረመው ስብስባቸው የተጫዋች ለወጥ ሳያደርጉ ነው ለጨዋታው የቀረቡት። 

ኢንተርናሽናል ዳኛ ባምላክ ተሰማ በመራው ጨዋታ ፈጣን ባለ እንቅስቃሴ ወደ ፊት በመሄድ የጀመሩት ጊዮርጊሶች ጎል ማስቆጠር የጀመሩት ገና አምስተኛው ደቂቃ ነበር። የቀኝ መስመር ቦታው ጋር በፈረሰኞቹ ቤት እየተላመደ የሚገኘው ደስታ ደሙ ከቦታው ተነስቶ ከጌታነህ ከበደ ጋር አንድ ቅብብል ብቻ በማድረግ ወደ ፊት በመሄድ ያሻማውን ኳስ ነፃ አቋቋም ላይ የሚገኘው አቤል ያለው ተረጋግቶ በግንባሩ ደገፍ አድርጎ በማስቆጠር ቅዱስ ጊዮርጊስን ቀዳሚ አድርጓል።

ጎል ቢቆጠርባቸውም ሳይረበሹ ተረጋግተው የተጫወቱት ሲዳማ ቡናዎች ምን አልባትም በኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ከተመለከትናቸው ምርጥና አስገራሚ ጎሎች አንዱ መሆን የሚችል ጎል አስቆጥረዋል። ዮሴፍ ዮሐንስ በ12ኛው ደቂቃ ከርቀት በቀጥታ በመምታት ግሩም የሆነ ጎል አስቆጥሮ ሲዳማዎችን አቻ ማድረግ ችሏል።

እረፍት አልባው የጨዋታ እንቅስቃሴ በጎል ታጅቦ ቀጥሎ ያብስራ ተስፋዬ ከሙሉዓለም መስፍን ጋር ተቀባብለው ሙሉዓለም ወደ ሳጥን ውስጥ ገብቶ የሲዳማው ግብጠባቂ ፍቅሩ ወዴሳ ቢያድንባቸውም ብዙም ሳይቆይ የሲዳማን ግራ መስመር ደጋግመው ሲፈትሹት የቆዩት ፈረሰኞቹ  ጥረታቸው ተሳክቶላቸው ሄኖክ አዱኛ ያሻገረውን የሲዳማ ተከላካይ ግሩም አሰፋ በግንባሩ ለግብጠባቂው ፍቅሩ አቀብላለሁ ብሎ በራሱ ላይ ጎል አስቆጥሮ ቅዱስ ጊዮርጊስን መሪነት ወደ ሁለት ከፍ ማድረግ ችሏል። 

ኳሱን ተቆጣጥረው በመጫወት ረገድ ክፍተት የነበረባቸው ሲዳማ ቡናዎች በሚቀራረጥ እንቅስቃሴ እና በተከላካዮች ተደጋጋሚ በሚሰሩ ስህተቶች ዳግመኛ ወደ ጨዋታው ለመመለስ የበራቸው ሂደት ደካማ ነበር። በአንፃሩ ፈረሰኞች ክፍተት የበዛበትን የሲዳማ መስመር ክፍልን ከመስመር አጥቂዎቻቸው በላይ የመስመር ተከላካዮቹ ደስታ ደሙ እና የሄኖክ አዱኛ በሚያደርጉት የማጥቃት እንቅስቃሴ ታግዘው 25ኛው ደቂቃ ደስታ ያሻገረውን አቤል ያለው ሌላ ጎል አስቆጠረ ሲባል ሳይረጋጋ ቀርቶ ሳይጠቀምበት የቀረው ሌላ ጎል መሆን የሚችል ጥሩ ሙከራ ነበር።

የጨዋታው ፈጣን እንቅስቃሴ የሲዳማ ቡናው  ግብ ጠባቂ ፍቅሩ ወዴሳ ባጋጠመው ጉዳት ምክንያት ለደቂቃዎች ያህል መቋረጡ አቀዝቅዞት ቢቀጥልም ብዙም ሳይቆይ በድጋሚ መጫወት አቅቶት በአዱኛ ፀጋዬ ተቀይሮ ወጥቷል። ግብጠባቂው አዱኛ 35ኛው ደቂቃ ላይ ተቀይሮ እንደገባ ወዲያውኑ የጌታነህ ከበደን ጠንካራ የቅጣት ምት ኳስ በጥሩ ሁኔታ በማዳን ፈተናውን ጀምሯል። የመጀመርያው አጋማሽ መጠናቀቂያ ላይ ጌታነህ ከበደ ቀኝ መስመር ላይ የተገኘውን ቅጣት ምት አሻግሮ ግብ ጠባቂው አዱኛ ኳሱን ሳይቆጣጠር የተፋውን ደስታ ደሙ አገባው ሲባል ሳይጠቀምበት ቀረ እንጂ ሌላ ጎል መሆን የሚችል አጋጣሚ ሆኖ አልፏል።

ከእረፍት መልስ ጨዋታው ቀጥሎ ጋዲሳ መብራቴ ከቅጣት ያሻገረውን ጌታነህ ከበደ ብቻውን በግንባሩ በመምታት ለጥቂት ሳይጠቀምበት ቢቀርም በድጋሚ አቤል ያለው ፍጥነቱን ተጠቅሞ ከመስመር ጣጣው ያለቀለት ኳስ አቀብሎት ጌታነህ ከበደ በግንባሩ በመግጨት ለፈረሰኞቹ ሦስተኛ ጎል አስቆጥሯል።

ሦስተኛ ከጎሉ መቆጠር በኃላ በቅዱስ ጊዮርጊስ የሜዳ ክፍል ዋና ዳኛ በዓምላክ ተሰማ በእጅ አልተነካም ረዳቱ ኃይለራጉኤል ወልዳይ ደግሞ በእጅ ተነክቷል በሚል ሳይናበቡ በመቅረታቸው ሲዳማ ቡናዎች ፍፁም ቅጣት ምት ተከለከልን በማለት ቅሬታ ሲያሰሙ የነበረበት ሁኔታ የጨዋታው አስገራሚ ክስተት ነበር።

በዚህ ሁኔታ የቀጠለው ጨዋታ የፈረሰኞቹ ግብጠባቂ ፓትሪክ ማታሲ ንቃት ታክሎበት በቀጥታ የላከውን ኳስ ፈጣኑ አጥቂ አቤል ያለው ተቆጣጥሮ ሳጥን ውስጥ በመግባት ለራሱ ሁለተኛ ለቡድኑ አራተኛ ጎል በማስቆጠር የቅዱስ ጊዮርጊስን የጎል መጠን ከፍ አድርጎታል። 

የፈረሰኞቹን ፈጣን የማጥቃት እንቅስቃሴ መቆጣጠር ያቃታቸው ሲዳማ ቡናዎች በተለይ ዮናታን ፍሰሀ የሚሰራቸው ስህተቶች ተቀይሮ ከመውጣቱ ባሻገር ቡድኑን ዋጋ አስከፍሎታል። ሌላ ጎል መሆን የሚችል ዕድል አቤል ያለው በፍጥነት በመግባት አግኝቶ ግብጠባቂው አዱኛ ያዳነበት ኳስ የሲዳማ ተከላካዮች ቅርፅ አልባ የሆነ እንቅስቃሴ በቂ ማሳያ ነው።

ያገኙትን አጋጣሚ በመጠቀም ረገድ ድንቅ የነበሩት ጊዮርጊሶች አቤል ያለው በድጋሚ ያለቀለት ኳስ በመስጠት ወደ ትክክለኛ ብቃቱ እየተመለሰ መሆኑን እያስመሰከረ የሚገኘው እና በዛሬው ጨዋታ ልዩ የነበረው ጌታነህ ለወትሮው በሚታወቅበት አጨራረስ ብቃት ግብጠባቂውን አዱኛን ጭምር በማለፍ 61ኛው ደቂቃ ላይ አምስተኛውን ጎል አስቆጥሯል።

የቅዱስ ጊዮርጊስን ብልጫን ፈዘው ሲመለከቱ የቆዩት ሲዳማዎች ኤድዊን ፍሪምፖንግ በሰራበት ጥፋት ምክንያት የተሰጠውን ፍፁም ቅጣት ምት ራሱ አዲስ ግደይ የጎል ልዩነቱን ከማጥበብ የዘለለ ፋይዳ ያልነበራት ጎል አስቆጥሯል። የጎሏ መቆጠር ትንሽ ያነቃቃቸው የሚመስሉት ሲዳማዎች ዮሴፍ በድጋሚ ከርቀት አክርሮ የመታውን ግብጠባቂው ማታሲ ያዳነበት ግሩም ሙከራ ነበረች።

በመጨረሻም 89ኛው ደቂቃ ላይ አስራ ስድስት ከሃምሳ ፊት ለፊት መስመሩ ላይ ያገኙትን ቅጣት ምት ዳዊት ተፈራ በአስደናቂ ሁኔታ ቢመታውም የግቡ አግዳሚ ሲመልስበት በመልሶ ማጥቃት የሄዱት ፈረሰኞቹ በቅርብ ጊዜ ወዲህ ከተስፋ ቡድን ዘንድሮ ያደገው እና እየተቀየረ በመግባት መጫወት የጀመረው ወጣቱ ተስፈኛ አብርሃም ጌታቸው በ89ኛው ደቂቃ ተቀይሮ ለገባው አቡበከር ሳኒ አቀብሎት በግንባር በመግጨት ስድስተኛ እና የማሳረጊያውን ጎል አስቆጥሯል። ጨዋታውም በቅዱስ ጊዮርጊስ 6–2 በሆነ ውጤት አሸናፊነት ተጠናቋል።

ውጤቱን ተከትሎ ቅዱስ ጊዮርጊስ ከረጅም ወራት በኃላ የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ መሪ መሆን ጀምሯል።

© ሶከር ኢትዮጵያ