የአሰልጣኞች አስተያየት | ወላይታ ድቻ 3-0 ድሬዳዋ ከተማ 

በ12ኛው ሳምንት የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ በሶዶ ስታዲየም ወላይታ ድቻ በታሪኩ ለመጀመሪያ ጊዜ ድሬዳዋ ከተማን 3-0 ካሸነፈበት ጨዋታ መጠናቀቅ በኃላ የቡድኖቹ አሰልጣኞች ተከታዮቹን አስተያየቶች ሰጥተውናል፡፡ 

“ውጤቱ አስፈላጊ ስለሆነ ሁለተኛውን አጋማሽ በጥንቃቄ ነው የተጫወትነው” ደለለኝ ደቻሳ ጊዜያዊ የወላይታ ድቻ አሰልጣኝ

ስለጨዋታው

እንዳያችሁት በፕሮፋይል ደረጃ ድሬዳዋን ስናሸንፍ የመጀመሪያችን ነው፡፡ እኛም በዛ ልክ ነበር ተዘጋጅተን የመጣነው፡፡ ባለፈው ሀዋሳ ላይ ራሳችን በፈጠርነው ስህተት ውጤት አጥተን ነው የመጣነው። እነዛን ስህተቶች ለቅመን በደጋፊያችን ፊት ጥሩ ነገር ይዘን ለመውጣት ነው የገባነው፡፡ እንዳያችሁት ከመጀመሪያ ሰከንድ ጀምሮ በማጥቃት ተጫውተን ውጤታማ ሆነናል፡፡

በሁለተኛው አጋማሽ ስላልተደገመው የቡድኑ እንቅስቃሴ

የመጀመሪያው አጋማሽ ላይ ሦስት ጎል አግብተናል፡፡ ሁለተኛ አጋማሽ ላይ ጥንቃቄ ላይ አተኩረን ነው የገባነው። ሜዳችንን ዘግተን ማጥቃት ባለብን ዕድል ልክ ለማጥቃት ነው ሁለተኛ አጋማሽ ላይ የገባነው ፤ ቢሆንም ተሳክቶልናል ብዬ አስባለሁ፡፡ ከዚህ በፊት በተለይ ደግሞ ሀዋሳ ላይ ግብ አግብተን ድጋሚ ለማግባት ስንል በከፈትነው ስህተት ነው ግብ የተቆጠረብን ፤ ያውም ባለቀ ሰዓት። ነገር ግን ያንን ላለመድገም ውጤቱ ከምንም በላይ አስፈላጊ ነው፡፡ ካለንበት ደረጃ ፈቅ ለማለት ውጤት ስለሚያስፈልገን ትኩረት እና ጥንቃቄ በተሞላበት ሁኔታ ሁለተኛውን አርባ አምሰት የኛን ሜዳ ደፍነን እነርሱ መሀል ላይ ኳሱን ቢይዙም የምናገኘውን ኳሶች ከነሱ የተሻሉ ነበሩ፡፡ ያው አላገባንም እንጂ ያንን መርጠን ነው የገባነው፡፡ ውጤቱ አስፈላጊም ስለሆነ ሁለተኛውን አጋማሽ በጥንቃቄ ነው የተጫወትነው፡፡ 

“ከዕረፍት በፊት እንደነበራቸው ብልጫ እና እንቅስቃሴ ሦስት ጎል ማስቆጠራቸው የሚያንስ ነው” ስምኦን አባይ ድሬዳዋ ከተማ

ከሜዳው ውጪ ስለማሸነፍ ችግር እና ስለዛሬው ሽንፈት 

ልክ ነው እንግዲህ እግር ኳስ ይሄ ነው፡፡ በ45 ደቂቃው ነው ተሸንፌ የወጣውት፡፡ ፈፅሞ የኛ ቡድን በመጀመሪያ  45 እንዳያችሁት ምንም ዝግጁ አልነበረም። በተለይ ከወገብ በታች ዲፌንሱም በጣም የተበታተነ እና ያልተቀናጀ ቡድን ነበር፡፡ ያንን ነገር በመጠቀም ደግሞ እነሱ ሦስት ጎል በተከታታይ ሊያገቡብን ችለዋል፡፡ ስለዚህ ከዕረፍት በፊት እንደነበራቸው ብልጫ እና እንቅስቃሴ ሦስት ጎል ማስቆጠራቸው የሚያንስ ነው፡፡ በመጀመሪያው አጋማሽ በነበረው ነገር ሙሉ ለሙሉ ብልጫ ተወስዶብኝ መሸነፍ ችያለሁ። ከፍተኛ የሆነ ድካምም ይታያል ልጆቹ ላይ። ባሉን ልጆች ነው የምንጫወተው ፤ የምንቀይረው እንኳን ብዙም የለም ፤ አድካሚ ጉዞ እያደረግን ነው፡፡ ማስተካከል ያለብንን ለማስተካከል ጥረት ማድረግ ነው ለሚቀጥለው፡፡ 

ስለተከላካይ መስመሩ ድክመት እና ስለበረከት ቅያሪ

ዛሬ የኋላው ተደራጅቷል ማለት አንችልም። ሦስት ጎል ገብቶብን ተደራጅቷል ማለት አንችልም። በረከትን በመጀመሪያው አጋማሽ የተሻለ መከላከል ኖሮን ቢሆን አልጠቀምበትም ነበር። ሙሉ ለሙሉ ጤነኛም አይደለም ውስጡ። ስለዚህ ግድ ሲሆንብኝ ነው ያስገባሁት። ቢሆንም ግን ለምሳሌ ወጣቶቹ ሲያደርጉ በነበሩት እንቅስቃሴ በነሙኸዲን እና ያሲን ላይ ያየሁት ነገር ብሸነፍም ተስፋ ሰጪ ነው፡፡ ቢሆንም ግን አሁንም ማስተካከል ያለብን ሚመስለን ኋለ ያለውን ነው፡፡ ጎል ጋር መድረስ ከቻልክ ኋላውን ማስተካከል ካልቻልክ ዋጋ ያስከፍልሀል። ስለዚህ ተከላካይ ላይ ያለውን ነገር አሁንም መስራት ካልቻልን አስቸጋሪ ነው፡፡ ግን ባሉ ተጫዋቾች ነው መስራት የምትችለው። ያለው ተጫዋች ደግሞ መተግበር ካልቻሉ ዋጋ ሊያስከፍል ይችላል። በቀጣይ ሂደት ለማስተካከል ጥረቶች እናደርጋለን፡፡

©ሶከር ኢትዮጵያ