የቅዱስ ጊዮርጊሱ ተከላካይ እስከ አንደኛው ዙር ፍፃሜ ድረስ ክለቡን አያገለግልም

ወሳኙ የቅዱስ ጊዮርጊስ የመሀል ተከላካይ እና አምበል አስቻለው ታመነ በባህር ዳሩ ጨዋታ በገጠመው ጉዳት እስከ አንደኛው ዙር ፍፃሜ ድረስ ለክለቡ ግልጋሎት አይሰጥም፡፡ 

በፕሪምየር ሊጉ ጠንካራ የመከላከል አደረጃጀት ካላቸው ክለቦች መካከል አንዱ የሆነው እና በተከታታይ ባስመዘገበው ውጤታማ ጉዞ መሪነቱን የተቆናጠጠው ቅዱስ ጊዮርጊስ በተደጋጋሚ ጉዳት ተጫዋቾቹን እያጣ ሲሆን አሁን ደግሞ የወሳኙን ተከላካይ አስቻለው ታመነን ግልጋሎት እስከ አንደኛው ዙር ፍፃሜ ድረስ እንደማያገኝ ሶከር ኢትዮጵያ አረጋግጣለች፡፡

ቅዱስ ጊዮርጊስ በአዲስ አበባ ስታዲየም በ10ኛው ሳምንት የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ጨዋታ ባህርዳር ከተማን ጋብዞ ባሸነፈበት ጨዋታ መሐል የማዕዘን ምት ባህርዳሮች ሲያሻሙ ኳሷን ለመግጨት ሲነሳ በክለቡ ግብ ጠባቂ ፓትሪክ ማታሲ የፊት እግሩ በመረገጡ ምክንያት ጉዳት በወቅቱ የገጠመው ሲሆን ከጉዳቱ ለማገገም ባለፉት ሁለት የሊጉ ጨዋታዎች ላይ አልተጫወተም። ጉዳቱ እረፍት የሚያስፈልገው በመሆኑም በቀጣዮቹ ሦስት ቀሪ የአንደኛው ዙር ጨዋታዎች ፈረሰኞቹን አያገለግልም። 

ተጫዋቹ የገጠመው ከአውራ ጣት ፊት ለፊት የሚገኝ Metatarsal Fracture (የሜታታርሳል ስብራት) የሚባል ህመም ሲሆን በበቂ እረፍት ራሱ ቦታውን እየገጠመ መምጣት ስላለበት ሀኪሞቹ ከሶስት እስከ አራት ሳምንት ያህል በቂ እረፍት ካገኘ በኃላ ወደ ልምምድ እንደሚመለስ እንደጠቆሙት ተጫዋቹ ለሶከር ኢትዮጵያ ተናግሯል፡፡ 

ከክለቡ ጋር በተያያዘ በተደጋጋሚ ጉዳት ላይ የሰነበተው ወሳኙ አጥቂ ሳላሀዲን ሰዒድ ዛሬ ወደ ልምምድ የተመለሰ ሲሆን አብዱልከሪም መሐመድም ከመጠነኛ ጉዳቱ አገግሟል፡፡ ረዘም ያለ ጉዳት የገጠመው ለአለም ብርሀኑን ጨምሮ ናትናኤል ዘለቀ፣ ያብስራ ተስፋዬ እና አቤል እንዳለ በጉዳት ከክለቡ ጋር ልምምድ ላይ አይገኙም፡፡

© ሶከር ኢትዮጵያ