“ወደ ክለቡ ተመልሶ የመስራት ወኔ የለኝም፤ ፍላጎቴ ሞቷል” አሰልጣኝ ግርማ ታደሰ

ከክለቡ የእግድ ደብዳቤ የደረሳቸው አሰልጣኝ ግርማ ታደሰ ከሀዲያ ሆሳዕና ጋር መለየታቸውን ከሶከር ኢትዮጵያ ጋር ባደረጉት ቆይታ ገልፀዋል፡፡ ክለቡ ከትናንት በስቲያ ለአሰልጣኝ ግርማ እና ረዳቶቻቸው የእግድ ደብዳቤ መስጠቱ የሚታወቅ ሲሆን ክለቡ እስካሁን በቀጣይ ስላለው ሁኔታ ባይገልፅም አሰልጣኞቹ ከቡድኑ ጋር ስለመለያየታቸው እየተነገረ ይገኛል። ከሆሳዕና መልቀቃቸውን የገለፁት አሰልጣኝ ግርማ ታደሰም ከሶከር ኢትዮጵያ ጋር ባደረጉት ቆይታ ስለ ወቅታዊው ሁኔታ አስተያየታቸውን አጋርተውናል።


ስለወቅታዊው ሁኔታ

መሠረታዊው ነገሩ ውጤት ከሌለ አሰልጣኝ ይነሳል፤ ምንም ጥያቄ የለውም። ውጤት የጠፋበት ግን የራሱ ምክንያት አለው። ውጤት በመጥፋቱ የምጠየቀው እኔ ነኝ። ሁለተኛ ክለቡም መፍትሔ ብሎ የወሰደው አሰልጣኝ ማንሳት ነው፤ ይችላል። መፍትሔው ትክክል ነው የሚባለው ግን ነገ የተሻለ ውጤት ሲመጣ ነው። ያ ከሆነ ትክክለኛ እርምጃ ነው የተወሰደው ብለህ ትቀበላለህ። ነገር ግን ቀጣይ የሚመጣው አሰልጣኝም እንደኔ የሚቸገር ከሆነ ነኔ ላይ የተወሰደው መፍትሔ ትክክል አይደለም። ከዛ ውጪ ከሥራ አስኪያጁ እስከ ቦርዱ ጥሩ ነገር ነበረኝ። ከእኔ ጋር በመግባባት ነው የሰራነው። የምጠይቀው ነገር ተግባራዊ ለማድረግ ከጅምሩ ጀምሮ በተቻላቸው መጠን ጥረዋል። የተሳካ ባይሆን ኖሮ የተሳካ ነበር ብዬ አልልም፤ ባላቸው ዕውቀት የሚችሉት አድርገዋል፡፡ ስለዚህ ላመሰግናቸው እፈልጋለሁ። ነፃነት ሰጥተውኛል።

እንደ ክለብ የተበላሹ ነገሮች አሉ። እነዛ የተበላሹ ነገሮች ተደምረው እኔ ላይ መጡ። ከተጫዋቾች ጋር በተያያዘ የዐምና ሽልማት እና ጥቅማጥቅማቸው ያለመሰጠት በጣም ችግር ፈጠሩብኝ። ዐምና ሽልማት መሬት ተብሎ አልተሰጣቸውም ዘንድሮ የመጡት ደግሞ የጠየቁት አልተሟላም፡፡ የዚህ ድምር ውጤት እኔ ላይ መጣና ተጠያቂ ሆንኩኝ፡፡ ተጫዋቾቹ የተባሉትን ነገር በወቅቱ ባለማግኘታቸው የመጫወት ፍላጎታቸውን አውርዶታል። ሁሌ የገንዘብ ጥያቄ ነው የሚያቀርቡት። ያን ደግሞ እኔ ማድረግ አልችልም፤ ቢሮው ነው እንጂ የሚፈታው። ይህ የኔን ሥራ አበላሸብኝ እንጂ ከማንም የሚያንስ ቡድን አይደለም።

አንዳንዴ ከአቅም በላይ የማትፈታው ችግር ሲገጥምህ ከባድ ነው። የተጫዋቾቹ ጥያቄ ገንዘብ ነው፡፡ ክለቡ ይህን በቀጣይም ካልፈታ እጅግ ከባድ ነው፡፡ የእኔ ግን እዚህ ጋር ማቆም ጥቅም አለው። አንደኛ የአመራሩን ቅር የተሰኘ ክለቡ ወደታች እንዲወድቅ ይመኛል፡፡ አመራሩን ነው ወይንስ ክለቡን መጥላት ያለብኝ የሚለውን መለየት አስፈላጊ ነው፡፡ 2008 የነበረው ችግር አሁን ላይ የለም ብዬ ነበር የመጣሁት። ነገር ግን አሁንም በ2012 በክለቡ እያየሁት ያለሁት የዛን ጊዜ የነበሩ ክፍተቶችን ነው፡፡ የገረመኝ ደግሞ 2008 ሳቆም በተመሳሳይ በ13ኛው ሳምንት ላይ ነበር። ዘንድሮም ከክለቡ ስለያይ በ13ኛው ሳምንት ላይ አቆምኩ። አሁንም መስራት እየተቻለ አይደለም፤ ሰዎች ካላገዙ አስቸጋሪ ነው። በአንድ ሰው ብቻ የሚሆን ነገር አይደለም፡፡ ይሄ ቡድን ቢያድግ ለኔም ለተጫዋቾቼ ጥሩ ነው፡፡ ቢያንስ ፕሮፋይላችን ያድጋል። ክለቡ ግን በዚህ አሰራር ከቀጠለ ምንም አይጠቀምም።

ስለ መልቀቃቸው

አሁን በጣም ሰላም ነው ያገኘሁት። በጣም ጤነኛ እና በጣም ደስተኛ ነኝ። ግን አንድ ቅር የሚለኝ ነገር አለ። ድሮ ሆሳዕና ከተማ ሲባል በነበረበት ወቅት ክለቡን የሚወዱ አሁንም ያሉ ንፁህ ደጋፊዎች አሉ። እነሱን እኔ በከፍተኛ ሊግ የሰጠኋቸውን ጥሩ ነገር በፕሪምየር ሊጉ ሳላስቀጥል እነሱንም ሳላስደስት ይሄ መፈጠሩ እጅግ ቅር ብሎኛል፡፡ ሌላ ምንም ቅር ያለኝ ነገር የለም። እኔ የትም መስራት እንደምችል በራስ መተማመኑ አለኝ። ግን እዚህ ያለው ደጋፊ ለኔ ጥሩ አክብሮት አለው። ጊዜያቸውን፣ ገንዘባቸውን እና ጉልበታቸውን ዋጋ ከፍለው ከጎኔ የቆሙ አሉ። እነዛን አለማስደሰቴ ቅር ብሎኛል። ከዛ ውጪ ምንም ቅር ያለኝ ነገር የለም።

ወደ ክለቡ ስለመመለስ

በምን ሞራልህ ነው የምትሰራው? ቤት ቁጭ ብዬ የክለቡን ችግር ሳስብ ይከብደኛል። እኔ እኮ ስጋት ነው ያለብኝ። ይሄን ስጋት ይዞ የሚቀጥል ከሆነ ቁልቁለት ነው። ችግሩ ቢፈታ እኔ ከውጪ እንኳን ሆኜ ቡድኑን እደግፋለሁ። ቡድኑ የእኔ አሻራ አለበት የሚባለው በሊጉ መቆየት ሲችል ነው፡፡ ዳግም ወደ ታች ከተመለሰ ምንም አሻራ የለም ማለት ነው፡፡ ስለዚህ ቡድኑ እንዲቆይ የራሴን አሻራ አበረክታለሁ፤ ውጪ ሆኜ ማለት ነው። ተመልሶ መስራት ላይ ግን ወኔ የለኝም፤ ፍላጎቴ ሞቷል፡፡ ትናንት የሰራኸው ሁሉ ስህተት ነው ተብለህ ከአንተ ጋር ሲደሰት የነበረው ዞሮ ሲሰድብህ ስታይ ትበሳጫለህ። በዚህ መንገድ እንኳን አሁን ተመልሶ መስራት ወደፊትም አላስበውም። ከባድ ነው ለኔ፤ ተመልሼ አላሰለጥንም፡፡

© ሶከር ኢትዮጵያ