ወላይታ ድቻ ጊዜያዊ አሰልጣኙን ቋሚ ሊያደርግ ነው

ከአሰልጣኝ ገብረክርስቶስ ቢራራ ስንብት በኃላ ያለፉትን ስድስት የፕሪምየር ሊግ ጨዋታዎች በመምራት ለወላይታ ድቻ ውጤት መሻሻል ቁልፍ አስተዋጽኦ የነበረው አሰልጣኝ ደለለኝ ደቻሳ ወላይታ ድቻን በዋና አሰልጣኝነት ለመረከብ ተቃርቧል፡፡

ወላይታ ድቻ በአዲሱ አሰልጣኝ ገብረክርስቶስ ቢራራ እየተመራ ነበር ዓመቱን የጀመረው። ክለቡ የ2012 የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ በሜዳው ሲዳማ ቡናን 2ለ0 በመርታት አጀማመሩን ቢያሳምርም ከዚያ በኋላ እስከ ስምንተኛ ሳምንት ከድል በመራቁ ምክንያት ዋና አሰልጣኙን ለማንሳት መገደዱ ይታወሳል፡፡ ካለፈው ዓመት ጀምሮ በረዳትነት ሲያገለግል የነበረው ወጣቱ አሰልጣኝ ደለለኝ ደቻሳን የዋና አሰልጣኝ ቅጥር እስኪፈፀም ድረስ በጊዜያዊነት ከሾመ በኋላም ካለፉት ስድስት ተከታታይ ጨዋታዎች በሀዋሳ ከተማ ከገጠማቸው ውጪ ሁሉንም በድል በመወጣት ከሊጉ ግርጌ ወደ አምስተኛ ከፍ ማለት ችሏል፡፡

ለዚህ ውጤት ክለቡ እንዲበቃ ደግሞ ጉልህ ድርሻን እየተወጡ የሚገኙት አሰልጣኝ ደለለኝ ደቻሳ ክለቡን ለቀጣዩ አንድ ዓመት በዋና አሰልጣኝነት እንዲመሩ የክለቡ ቦርድ ከመግባባት በመድረሱ በቀጣይ ወደ ቋሚ አሰልጣኝነት እንደሚሸጋገሩ ለማወቅ ተችሏል።

በወላይታ ድቻ ከታዳጊ ቡድን ጀምሮ የአሰልጣኝ ዘነበ ፍሰሀ እና አሸናፊ በቀለ ረዳት በመሆን የሰራው አሰልጣኝ ደለለኝ ከወቅታዊ የክለቡ ጉዞ ጋር በተገናኘም ከሶከር ኢትዮጵያ ጋር ባደረገው አጭር ቆይታ ስለውጤቱ መሻሻል የሚከተለውን ብሏል፡፡

“የመጣው ውጤት ልጆቹን አንድ በማድረግ ነው። እኔ ከታዳጊ ቡድን ጀምሮ ቡድኑን ስለማውቀው መጠቀም ያለብን ተጫዋቾች እነማን እንደሆኑም ስለማውቅ እነሱን በአግባቡ በመጠቀም የቡድኑን መንፈስ በማይረብሽ መልኩ ቡድኑን ሳይጠቅሙ የተቀመጡት ላይ ደግሞ እርምጃ በመውሰድ እንዲሁም ከደጋፊው እና ከቦርድ ሰዎች ጋር በግልፅ በመነጋገር፤ እነዚህም ተደምረው ውጤታማ አድርጎናል።

“እኔ የቡድኑን ህብረት ማጠናከሩ ላይ ነው ትኩረት ያደረኩት። ከዛ ባለፈ ተጫዋቾች ከራሳቸው ጥቅም ቡድኑን እንዲያስቀድሙ ጥሬያለሁ። እነሱም ማስቀደም የጀመሩበት ሁኔታ አለ። ለምሳሌ ተከላካዮቹን ደጉ በደንብ ያስተባብራል፤ አማካዮቹን ደግሞ ተስፋዬ፤ ከዛ ባለፈ ደግሞ እንደ የቦታቸው ልምድ ያላቸው ተጫዋቾች ህብረት እንዲፈጥሩ አድርገናል። ይህን ማድረግ ደግሞ የጀመርነው ከጅማ ጋር ለመጫወት ስንሄድ ነበር። አጥቂው፣ ተከላካዩ ምን መስራት አለበት የሚለውን ከኛ አልፎ ለተጫዋቾቹ ኃላፊነት ሰጥተን ስለነበር፤ እንነጋገርም ስለነበር በዛኑ ልክ መስተካከል ያለባቸውን ለክለቡ ገልፀናል። ዋናው ሚስጥሩ ስራውን በጋራ እየሰራን ስለሆነ ነው። የአሰልጣኝ ቡድን አባላትን ከተመለከትክ ወጣቶች ነን። ምንም የምንወሻሸውም የምንደባበቀውም ነገር የለም። በጋራ እያወራን እየሰራንም ስለሆነ ያ ነው ለስኬታችን ትልቅ ነገር ብዬ የማስበው።”

የፕሪምየር ሊጉ አንደኛው ዙር ሊጠናቀቅ የሚቀረው አንድ ጨዋታ ብቻ የሚቀረው ሲሆን የዝውውር መስኮቱ ሲከፈት ወላይታ ድቻ በሚያሰናብታቸው ተጫዋቾች ምትክ አዳዲስ ተጫዋቾች እንደሚያስፈርም ከክለቡ ያገኘነው መረጃ ይጠቁማል፡፡

© ሶከር ኢትዮጵያ