የአሰልጣኞች አስተያየት | ሀድያ ሆሳዕና 0-1 ወላይታ ድቻ

በአስራ ሦስተኛው ሳምንት የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ጨዋታ ብቸኛ በነበረው እና ሜዳው በመቀጣቱ ሀዋሳ ላይ ለማድረግ የተገደደው ሀድያ ሆሳዕና በወላይታ ድቻ 1ለ0 ከተሸነፈበት ጨዋታ መጠናቀቅ በኃላ ሁለቱም አሰልጣኞች ተከታዩን አስተያየት ሰጥተዋል፡፡
“ከእለት እለት ለውጥ አለ፤ ግን የምንፈልግበት ደረጃ ደርሷል ማለት ግን አይቻልም” ደለለኝ ደቻሳ (ጊዜያዊ የወላይታ ድቻ አሰልጣኝ)

ስለጨዋታው እና ከእረፍት መልስ ስለመቀዛቀዛቸው

በጣም ከባድ ጨዋታ ነው፡፡ ሀዲያ ሆሳዕና እንደስብስብ ስናየው በጣም ጥሩ ቡድን ነው። በዛ ልክ ነው እኛም ተዘጋጅተን የመጣነው። አቅደን የመጣነውን አሳክተናል፡፡ በስብስብ ከእኛ የተሻሉ ናቸው ብዬ አስባለሁ። የኛ ወጣቶች ናቸው። እንደ ወላይታ ድቻ ነጥብ ለመያዝም እየሰራን ስለሆነ መጀመሪያ አጋማሽ ጎል እስክናገባ ጎልም ካገባን በኃላ ያለንም ነገር ጥሩ ነበር፡፡ ሁለተኛው አጋማሽ ግን ኃላችንን ደፍነን በህብረት ለመጫወት ነበር የሞከርነው፡፡ ያው እንዳያችሁት ነው፡፡ በዋናነት ቡድኑ ውስጥ ህብረት ለመፍጠር ጥረት አድርገናል፡፡ አንዳንድ ክፍተቶት አሉ። እሱን ለመድፈን ደግሞ እየሰራን ነው፡፡ ከእለት እለት ለውጥ አለ፡፡ ግን የምንፈልግበት ደረጃ ደርሷል ማለት ግን አይቻልም፡፡ መስራት ያለብን ብዙ ነገር እንዳለ ያሳየናል፡፡

አምበሉ ባዬ ገዛኸኝ ከዳኛው ጋር በመጀመሪያው አጋማሽ ስለገባበት ሰጣ ገባ

ከእረፍት መልስ መንገር ባለብን ልክ ነግረነዋል። ያደረገው አግባብነት የለውም። ሜዳ ውስጥ ዳኛ የመሰለውን እና ህጉን ነው ተግባራዊ የሚያደርገው። ሰጣ ገባ ውስጥ መግባቱ አግባብ እንዳልሆነ ነግረነው። ሁለተኛ አጋማሽ ለውጦች አይተናል፡፡ እንሰራበታለን በዲሲፕሊኑ ረገድ፡፡


” ለኔ የመጀመሪያ ጨዋታ ነው፤ ብዙ ስዕል አሳይቶኛል” ፀጋዬ ኪዳነማርያም ሀድያ ሆሳዕና

ስለዛሬው ጨዋታ

በጣም ጥቂት ቀናትን ነው ከቡድኑ ጋር የቆየውት ሶስት አራት ልምምድን ነው ከቡድኑ ጋር የቆየውት እና ዛሬ ደግሞ በውድድር ቡድኑ ምን እንደሚመስል ለማየት ችያለሁ። በነበረው እንቅስቃሴ የመጀመሪያው ሀያ ደቂቃ የድቻ የበላይነት ነበር ማለት ይቻላል፡፡ ከእረፍት በፊት በቀሩት ደቂቃዎች እና በሁለተኛው አርባ አምስት ተጭነን በመጫወት ብዙ የጎል ዕድሎችን ማግኘት ችለናል፡፡ ዕድለኞች አልነበርንም። እንደ እንቅስቃሴ ድቻ በራሱ በጥሩ መነቃቃት ላይ ያለ ቡድን ነው፡፡ የራሱ ጥንካሬ አለው። ሜዳው ላይ አሸንፎ የመጣ ቡድም ነው። ይህን ሁሉ ጫና ችለን እኛ ደግሞ ሜዳችን ውጪ ከመጫወታችን አንፃር ልጆቹ ደግሞ ከፍተኛ ጫና ውስጥ ስላሉ በስነልቦና ተጠናክረን ለመግባት ሞክረናል፡፡

እንደ ቡድን ቡድኑ ይንቀሳቀሳል፡፡ የነጥቡ መራራቅ በልጆቻችን ላይ ጫና እንዳያሳድር ከፍተኛ ጥረት እያደረግን ነው፡፡ ለኔ የመጀመሪያ ጨወታ ነው፡፡ ብዙ ስዕል አሳይቶኛል፡፡ አሁን ሁለት ጨዋታዎች ይቀራሉ፡፡ ከዚህ በመነሳት በክፍተቶቻችን ላይ ሰርተን በአብዛኛው በሁለተኛው ዙር ላይ አጠናክረን የምንቀጥልበት ሁኔታ ነው ምናመቻቸው፡፡ በቀሪ ጨዋታዎች ጥሩ ስራ ሰርተን እንታገላለን ብዬ አስባለሁ፡፡

የቡድኑ ጠንካራ እና ደካማ ጎን

እንግዲህ በድክመት ደረጃ እንዲህ ነው ብዬ መለየት አልቻልኩም። ለምሳሌ በልምምድ ቦታ እንኳን አስራ አንድ ለአስራአንድ ሆነው ጨዋታ ሲያደርጉም አላየዋቸውም። ከስማቸው ጋር ለመላመድም በጣም ጥቂት ቀናቶች ናቸው የነበሩኝ። ለኔ ትንሽ ፈታኞች ናቸው። ግን በሂደት የሚስተካከሉ ናቸው። በየቦታው ጥራት ያላቸው ተጫዋቾች አሉ፡፡ የግል ክህሎታቸው ጥሩ የሆኑ ልጆች አሉ። ከስኳድ አንፃር አሁን ሀያ ተጫዋቾች ናቸው ያሉት። አንድ የተጎዳ አለ፤ ሀያ አንድ በቡድኑ ያለው። ስለዚህ ቡድኑን የማስፋት ስራን በስፋትም በጥራትም ማስካከል የሚገባን ነገር አለ ብዬ አስባለሁ። ምናልባት ይሄ ጥራቱ ላይ ቡድኑን ማስፋት እንዳለብን የሚታየኝ ነገር አለ፡፡

© ሶከር ኢትዮጵያ