ከፍተኛ ሊግ | መከላከያ ነጥብ ሲጥል ሀላባ አሸንፏል

የኢትዮጵያ ከፍተኛ ሊግ 9ኛ ሳምንት ምድብ ለ የመጨረሻ ጨዋታዎች ዛሬ ተከናውነው ሀላባ ከተማ አሸንፏል። መከላከያ ከወላይታ ሶዶ ደግሞ አቻ ተለያይተዋል።

10:00 በተካሄደው የከፍተኛ ሊግ የምድብ ለ መከላከያ ከወላይታ ሶዶ ሲገናኙ በጨዋታው መጠናቀቂያ ላይ በተቆጠሩ ጎሎች ጨዋታው በአንድ አቻ ውጤት ተጠናቋል። በተከታታይ አራት ጨዋታ በአቻ ውጤት ያጠናቀቁት መከላከያዎች ከጨዋታው ሦስት ነጥብ ፈልገው እንደገቡ በሚያሳይ ሁኔታ በከፍተኛ ተነሳሽነት ነበር በፍጥነት ወደ ወላይታ ሶዶ የግብ ክልል በተደጋጋሚ መድረስ ችለው የነበረው። በ10ኛው ደቂቃም ዳዊት ማሞ በግራ እግሩ ከርቀት የመታውን የወላይታ ሶዶ ግብጠባቂ እንዳሻው እሸቴ ሚዛኑን ሳይጠብቅ በመቅረቱ ያልተቆጣጠረውን ኳስ መሐመድ አበራ በግንባሩ ገጭቶ ወደ ውጭ ለጥቂት የወጣበት በመከላከያ በኩል የጨዋታው የመጀመርያ ሙከራ ነበር።

በራሳቸው ሜዳ ክፍል በዝተው ሲከላከሉ የቆዩት ወላይታ ሶዶዎች በተለይ ቁመቱ ረጅሙ ሮበርት ሳሊሎን ትኩረት ያደረገው የማዕዘን ምት አጠቃቀማቸው ለመከላከያ ተከላካዮች አደጋ ሲሆን ቆይቷል።

የዕለቱ ዳኛ በሚወስናቸው ውሳኔዎች ደስተኛ ባለመሆን በተደጋጋሚ ቅሬታ ያሰሙ የነበሩት መከላከያዎች ትኩረታቸውን ከጨዋታው እንቅስቃሴ በመውጣታቸው የጎል ዕድል ለመፍጠር ቢቸገሩም 34ኛው ደቂቃ ዘነበ ከበደ ከመስመር ያሻገረውን ኳስ ፍሬው ሰለሞን ደገፍ አድርጎ ለጥቂት የወጣበት ኳስ የሚያስቆጭ ነበር።

ሙሉ ለሙሉ በሚያስብል ሁኔታ በራሳቸው ሜዳ በመከላከል ሲጫወቱ የቆዩት ወላይታ ሶዶዎች በሁለተኛው አጋማሽ ለመከላከያው ግብጠባቂ አቤል ማሞ ስራ አቅለውለት ውለዋል። አሰልጣኝ ዘላለም ሽፈራው ወላይታ ሶዶዎች መከላከልን ምርጫቸው በማድረጋቸው ምክንያት የተከላካይ ቁጥርን በመቀነስ የአጥቂ ቁጥራቸውን በማብዛት በጨዋታው ሦስት ነጥብ ለማግኘት ይጥራሉ ቢባልም አንድ አይነት የሆነ የማጥቃት መንገድ መከተላቸው ዋጋ አስከፍሏቸዋል።

በዚህ ሂደት ውስጥ 60ኛው ደቂቃ የመከላከያው ዳዊት ማሞ ፍፁም ቅጣት ምት ክልል ውስጥ ሆን ብለህ ልታሳስተኝ ወድቅሀል በሚል የዕለቱ ዋና ዳኛ በሁለት ቢጫ በቀይ ካርድ ከሜዳ አስወግደውታል። በዚህ ውሳኔ ክፉኛ የተበሳጩት የቡድኑ ተጫዋቾች እና አባላት ቅሬታቸውን ሲያሰሙ ተመልክተናል። ከዚህ በኃላ የነበረው የጨዋታው መንፈሱ ተቀይሮ ወደ ሁከት አምርቶ የተለያዮ ውዝግቦችን አስተናግዶ ጨዋታው መካሄዱን ቀጥሏል።

ምንይሉ ወንድሙ በመከላከያ በኩል በጥሩ መንገድ ወደ ጎል የመታውን የግብ ክልላቸውን ከተከላካዮቹ በተጨማሪ በንቃት ይጠብቅ የነበረው ግብጠባቂው እንደሻው እሸቴ ይዞበታል።

በመጨረሻም በመልሶ ማጥቃት ጫና ይፈጥሩ የነበሩት ወላይታ ሶዶዎች በኃይሉ ግርማ እና ቴዎድሮስ ታፈሰ በሚያደርጉት ቅብብል የተቋረጠውን ኳስ ወደ ፊት ይዘው የገቡት ወላይታ ሶዶዎች ተረጋግቶ ሰለሞን ደጀኔ አመቻችቶ ያቀበለውን ክብሩ በለጠ በ89ኛው ደቂቃ ባስቆጠረው ጎል ቀዳሚ መሆን ችለዋል።

ሙሉ ዘጠና ደቂቃ እንደነበራቸው ጠንካራ መከላከል ውጤቱን አስጠብቀው ይወጣሉ ሲባል በተጨማሪ ደቂቃ ፍፁም ቅጣት ምት ያገኙት መከላከያዎች ምንተስኖት ከበደ ኳሱን ወደ ጎልነት በመቀየር መከላከያን ከሽንፈት ታድጓቸዋል። ጨዋታውም በአንድ አቻ ውጤት ተጠናቋል።

ሌላው ዛሬ የተካሄደው የ9ኛ ሳምንት መርሐ ግብር ሀላባ ላይ ተከናውኖ ሀላባ ከተማ ካፋ ቡናን 2-0 ማሸነፍ ችሏል። ለሀላባ ጎሎቹን አቡሽ ደርቤ እና ተመስገን ተመስገን ይልማ አስቆጥረዋል።

© ሶከር ኢትዮጵያ