ሪፖርት | የደጉ ደበበ ግብ ወላይታ ድቻን ለድል አብቅታለች

በኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ የአስራ ሦስተኛው ሳምንት የዛሬ ብቸኛ ጨዋታ ሜዳው በመቀጣቱ ሀዋሳ ላይ ለማድረግ የተገደደው ሀድያ ሆሳዕና በወላይታ ድቻ 1ለ0 ተሸንፏል፡፡

ሆሳዕና ባለፈው ሳምንት በአዲስ አበባ ስታዲየም በሰበታ ሲሸነፍ ከተጠቀመው ስብስብ ሱራፌል ጌታቸውን በይሁን እንዳሻው ብቻ በመለወጥ ወደ ሜዳ ሲገባ ድቻዎች በበኩላቸው በሜዳቸው ድሬዳዋን ድል ሲያደርጉ ከተጠቀሙት ሙሉ ስብስብ ምንም ለውጥ ሳያደርጉ ገብተዋል፡፡

አሰልጣኝ ፀጋዬ ኪዳነማርያምን ከሰሞኑ የሾመው ሀዲያ ሆሳዕና በህክምና ባለሙያው እየተመራ ወደ ሜዳ ይገባል ተብሎ ቢጠበቅም አዲሱ አሰልጣኝ ቡድኑን ለመጀመሪያ ጊዜ እየመሩ ወደ ሜዳ ሊገቡ ችለዋል፡፡ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ረዳት አሰልጣኝ ሙሉጌታ ምህረት እና የግብ ጠባቂው አሰልጣኝ ውብሸት ደሳለኝ በስታዲየሙ ተገኝተው በተከታተሉት እና ከተለመደው በተቃራኒ እጅግ በርካታ ደጋፊዎች በአስገራሚ ድባብ ከአፍ እስከ ጉድፉ የሀዋሳን ስታዲየም ሞልተው በታዩበት በዛሬው ጨዋታ የመጀመሪያው አጋማሽ ወላይታ ድቻዎች በመስመር በኩል በሚያደርጉት አስፈሪ እንቅስቃሴ ታጅበው ሜዳውን በመለጠጥ በተጋጣሚው ላይ ጫና ሲያሳድሩ ሆሳዕናዎች በአንፃሩ በመልሶ ማጥቃት ከአፈወርቅ ኃይሉ እግር ከሚነሱ ኳሷች አብዛኛዎቹን ደቂቃዎች ለመጠቀም የሞከሩበት ቢሆንም ስኬታማ የሆኑት ግን በጥቂት አጋጣሚዎች ብቻ ነበሩ።

2ኛው ደቂቃ በቀኝ የሀድያዎች የግብ ክልል አንተነሀ ጉግሳ መሀል ለመሀል አሾልኮ የሰጠውን ኳስ ወጣቱ እዮብ አለማየሁ እየነዳ ወደ ሳጥን ተጠግቶ ግብ ጠባቂው አቤር ኦቮኖ እንደምንም ወጥቶ ከግብ ከመሆን የታደጋት ክስተት ድቻዎችን በሙከራ ረገድ ቀዳሚ እንዲሆኑ ያደረገች ዕድል ነበረች፡፡ ድቻዎች በእዮብ እና ቸርነት በቀኝ እና ግራ በኩል ፈጣን የሆኑ ተሰንጣቂ ኳሶችን ከመፍጠር ባለፈ ሰብሮ ወደ ግብ ክልል ለመግባት ተደጋጋሚ ጥረትን አድርገዋል፡፡ 11ኛው ደቂቃ ሆሳዕናዎች ቢስማርክ አፒያ በግራ በኩል በረጅሙ ያሻገረውን ኳስ ከተለመደው የመስመር አጥቂነቱ ወደ ተከላካይ ስፍራ ተለውጦ ለወላይታ ድቻ ሚጫወተው ፀጋዬ አበራ ኳስ ለማቀዝቀዝ ባሰበበት ወቅት ሱራፌል ዳንኤል በፍጥነት አግኝቷት ለበሀይሉ ተሻገር አቀብሎት አማካዩ ፊት ለፊት ከግብ ጠባቂው መክብብ ጋር ተፋጦ ወደ ግብነት ለወጠው ሲባል መክብብ እንደምንም ይዞበታል፡፡

26ኛው ደቂቃ ላይ በግራ የሆሳዕና ግብ ክልል በተሰራ ጥፋት የተገኘውን የቅጣት ምት ባዬ ገዛኸኝ በረጅሙ ወደ ግብ ሲያሻማ አንጋፋው ተከላካይ ደጉ ደበበ በግንባር ገጭቶ ወደ ግብነት ለውጧት የጦና ንቦቹን መሪ ማድረግ ችሏል፡፡ ግብ ካስቆጠሩ በኃላ ወደ መቀዝቀዝ የገቡት ድቻዎች መልሶ ማጥቃትን አማራጭ በማድረጋቸው በሆሳዕናዎች ቶሎ ቶሎ ከሚነሱ ተሻጋሪ ኳሶች ጫና ውስጥ ተገደዋል፡፡ በተለይ ሁለቱ ጋናዊያን አጥቂዎች ቢስማርክ ኦፖንግ እና ቢስማርክ አፒያ ተደጋጋሚ ጊዜ ግልፅ ዕድሎችን እያገኙ አምክነዋል፡፡ ሄኖክ አርፊጮ ከቅጣት ምት በረጅሙ ሲያሻማ አዩብ በቀታ በግንባር ገጭቶ መክብብ ደገፉ ያወጣት እና አሁንም ከቅጣት ምት ሄኖክ አርፊጮ ያደረጋት አስቆጪ ሙከራ ተጠቃሽ ነች፡፡ ድቻዎች ባዬ ገዛኸኝ ከእለቱ ዳኛ አሸብር ሰቦቃ ጋር በሜዳ ላይ ሲያደርግ ከሚታየው ሰጣ ገባ ባሻገር በእዮብ እና ቸርነት ጥምረት ተጨማሪ ግብ ለማከል ቢያልሙም ሳይሳካ ቀርቷል፡፡

ከእረፍት መልስ በይበልጥ ፍፁም ብልጫን ይዞ የገባው ሀድያ ሆሳዕና ረጃጅም ኳሶች ላይ በደንብ ትኩረት ከማድረግ በዘለለ የአጥቂውን ክፍል ከሁለት ወደ ሦስት ከፍ በማድረግ አቻ ለመሆን እጅግ ብርቱ ትግል አድርገዋል፡፡ ገና ከእረፍት እንደገቡ ሱራፌል ሲያሻማ ፀጋሰው ግልፅ ዕድል አግኝቶ መጠቀም ሳይችል የቀረበት ክስተት ምናልባትም የአሰልጣኝ ፀጋዬን ቡድን ምታነቃቃ አሪፍ ዕድል ነበረች፡፡ 52ኛው ደቂቃ ሀድያዎች በደስታ ጊታሞ አማካኝነት ግብ ቢያስቆጥሩም ኳሷ ቀድማ በእጅ ተነክታለች በሚል ተሽራለች፡፡

ከመጀመሪያው አጋማሽ የማጥቃት አቀራረባቸውን ለወጥ አድርገው በመከላከል አደረጃጀት ወደ ሜዳ የገቡት ድቻዎች ጥብቅ መከላከልን በመከተላቸው ከግብ ጠባቂያቸው መክብብ ጋር ተጣምረው መረባቸውን ላለማስደፈር ብርቱ ትግል አድርገዋል፡፡ በተለይ የመሐል ክፍላቸውን ወደ ፊት አስጠግተው በአፈወርቅ እና ይሁን በሚጣሉ ኳሶች ግብ ፍለጋ ውስጥ የገቡት ነብሮቹ በርካታ ያለቀላቸውን ዕድሎች ቢያገኙም ለማስቆጠር በሚያደርጉት ጥረት ከፍተኛ ጉጉት በመኖሩ ከግብ ጋር እየተገናኙ መጠቀም ሳይችሉ ቀርተዋል፡፡

ቡድኑ በሁለቱ ቢስማርኮች እየታገዘ ጥረት ቢያደርግም መክብብ ደገፉ በተደጋጋሚ አክሽፎቸዋል፡፡ በመልሶ ማጥቃት 68ኛው ደቂቃ ላይ ያገኙትን ተሻጋሪ ኳስ ቢስማርክ ኦፖንግ ነፃ አቋቋም ላይ ሆኖ አግኝቷት ወደ ግብ ሲመታ ተከላካዩ ውብሸት አለማየሁ ከግቡ ጠርዝ ላይ በሚገርም ብቃት ተንሸራቶ አውጥቷታል፡፡

ጨዋታው እየተደረገ ባለበት ሰዓት ስታዲየሙ ሙሉ በሙሉ ሞልቶ ተመልካቾች በቂ ቦታ ለማግኘት በመቸገራቸው በየዛፉ እና በየሰው ቤት ላይ በርካቶች ቆመው ለማየት የተገደዱ ሲሆን በዚህም ሂደት በስታዲየሙ የግራ ክፍል ባለው ዛፍ ላይ ሆነው ሲከታተሉ የነበሩ ደጋፊዎች ከዛፉ ላይ ሲወድቁ ታይተዋል። በተለይ አንድ ህፃን ጉዳት ገጥሞት በአፋጣኝ ቀይ መስቀሎች ህክምና ሲያደርጉለት አስተውለናል፡፡

ጨዋታው ሊጠናቀቅ 16 ደቂቃዎች ሲቀሩት ድቻዎች የዕለቱ ዳኛ አሸብር ሰቦቃ ሆን ብሎ ጫና እያሳደረብን ነው፡ በተደጋጋሚም እኛ እየበደለ ነው በማለት በአምበሉ ባዬ ገዛኸኝ አማካኝነት ክስ አስይዘዋል፡፡ ሆሳዕናዎች በቢስማርክ አፒያ ሁለት ጊዜ በመጨረሻዎቹ ደቂቃዎች መልካም አጋጣሚን አግኝተው ዕድለኛ ባለመሆናቸው ማስቆጠር ሳይችሉ በመቅረታቸው ጨዋታው በወላይታ ድቻ 1ለ0 አሸናፊነት ተጠናቋል፡፡

✿በጨዋታው መሀል በቅርቡ ጉልበቷ ላይ ጉዳት የገጠማት የዲላ ከተማዋ አጥቂ ቤዛ ታደሰ ለህክምና ወጪዋ የሚውል በሀድያ ሆሳዕና ደጋፊዎች እንዲሁም በሌሎች በተገኙ ክለቦች ትብብር በስታዲየሙ ውስጥ ከአስራአምስት ሺህ ብር በላይ ተሰብስቧል፡፡

✿ክለቦቹ እየተጫወቱ ባለበት ወቅት የኳስ አቀባዮች ከተጣለባቸው የስራ ድርሻ ውጪ ሜዳ ላይ ተኝተው ጊዜያቸውን ሲያሳልፉ ያየን ሲሆን ይሄም ቅሬታን ከደጋፊው ዘንድ ያስነሳና መለመድ የሌለበት ድርጊት ነው፡፡

© ሶከር ኢትዮጵያ