ቅድመ ዳሰሳ | ወልቂጤ ከተማ ከ ሲዳማ ቡና

በሌላኛው የ14ኛ ሳምንት የመጨረሻ የጨዋታ ቀን ከፍተኛ መነቃቃት ላይ የሚገኙት ወልቂጤ ከተማዎች ሲዳማ ቡናን የሚያስተናግዱበት ጨዋታ ቀጣዩ የዳሰሳችን ትኩረት ነው።

ባለፉት ተከታታይ አራት ጨዋታዎች ያልተሸነፈው ወልቂጤ ውኬታማነቱን በማስቀጠል ደረጃውን ለማሻሻል የነገው ጨዋታ ወሳኝ ነው።

የወልቂጤ ከተማ ያለፉት 5 ጨዋታዎች አቋም (ከቅርብ ወደ ሩቅ)
አቻ አሸነፈ አሸነፈ አሸነፈ ተሸነፈ

እንደተጋጣሚ ቡድኖች ሁኔታ አጨዋወታቸውን የሚቃኙት ወልቂጤ ከተማዎች ባለፉት አምስት የጨዋታ ሳምንታት ተከታታይ ነጥቦችን በማስመዝገብ መልካም የሚባል ወቅታዊ አቋም ላይ ይገኛሉ። በነገው ጨዋታም በደጋፊያቸው ታግዘው ሰሞነኛ ያለመሸነፍ ጉዟቸውን ለማስቀጠል ከፍተኛ ጥረት ያደርጋሉ ተብሎ ይጠበቃል ፤ በጨዋታው ከፍተኛ መሻሻልን ያሳየው የማጥቃት ጨዋታቸው ዋነኛ ተዋናይ ከሆኑት ሦስቱ አጥቂዎች አንዳች ነገር የሚጠበቁ ይሆናል።

በመስመሮች መካከል ያለውን ክፍተት በማጥበብ በጥንቃቄ የሚከላከሉት ወልቂጤዎች የአጥቂዎቻቸውን አስደናቂ ፍጥነት በመጠቀም ፈጠን ያሉ መልሶ ማጥቃቶችን ለመሰንዘር የሚያደርጉት ጥረት ለተጋጣሚዎች ለመቋቋም አስቸጋሪ ስለመሆኑ የኢትዮጵያ ቡና ጨዋታ በቂ ማሳያ ነው።

የነገው ተጋጣሚያቸው ሲዳማ ቡና በወራጅ ቀጠና ከሚገኙት ድሬዳዋ ከተማና ሆሳዕና እኩል በሊጉ በርካታ ግቦችን (23) ያስተናገደ ከመሆኑና ካለበት የመከላከል ችግሮ አንፃር በነገው ጨዋታ ለወልቂጢዎች ግብ ለማስቆጠር ሊመች ይችላል ብሎ መገመት ይቻላል።

ባለሜዳዎቹ ወልቂጤዎች በነገው ጨዋታ ላይ ይበልጣል ሽባባውና ፍፁም ተፈሪን ግልጋሎት የማያገኙ ይሆናል።

የሲዳማ ቡና ያለፉት 5 ጨዋታዎች አቋም (ከቅርብ ወደ ሩቅ)
አሸነፈ ተሸነፈ አሸነፈ ተሸነፈ ተሸነፈ

ሲዳማ ቡና በሜዳው የሚያስመዘግበውን ውጤት ከሜዳ ውጪም በመድገም ደረጃውን ለማሻሻል አልሞ የነገውን ጨዋታ ይጠባበቃል።

ዝብርቅርቅ ያለ የውድድር ዘመን እያሳለፉ የሚገኙት ሲዳማዎች አሁንም ቢሆን በቀላሉ የሚያስቆጥሩ ነገር በተመሳሳይ በቀላሉ ግብ የሚያስተናግድ ቡድን እንደሆነ ቀጥሏል። እንደ ወልቂጤ ሁሉ በፈጣን አጥቂዎቹ ፈጣን እንቅስቃሴ መነሾ ግቦችን የሚያስቆጥሩት ሲዳማዎች አሁንም እስካልተፈታው ደካማ የመከላከል አደረጃጀታቸው የነገውን ጨዋታ የሚያደርጉ ይሆናል።

ለማጥቃት ካላቸው ከፍ ያለ ትኩረት የተነሳ በርከት ያሉ ተጫዋቾች በተጋጣሚ የሜዳ አጋማሽ የሚልኩት ሲዳማዎች ለተጋጣሚ ፈጣን የማጥቃት ሽግግር በተጋጣሚ ከሚወሰድባቸው የቁጥር ብልጫ አንፃር በቀላሉ ግብ እያስተናገዱ ይገኛል። ነገም ይህ የሚሆን ከሆነ በቀላሉ ግብ ማስተናገዳቸው አይቀሬ ነው።

ባሳለፍነው ሳምንት ያለ አዲስ ግደይም ግቦችን ለማስቆጠር እንደማይቸገር ያሳየው ቡድኑ በነገው ጨዋታ ላይ ለጠንካራዎቹ የወልቂጤ ከተማ ተከላካዮች ከባድ የቤት ስራ ይሆናሉ ተብሎ ይጠበቃል።

ሲዳማ ቡናዎች የተከላካዮቻቸውን ጊት ጋትኮችና ዮናታን ፍሰሃን ጨምሮ ወሳኙን የጨዋታ አቀጣጣይ ዳዊት ተፈራን አገልግሎት አያገኙም።

እርስበርስ ግንኙነት

– ሁለቱ ቡድኖች በሊጉ ለመጀመርያ ጊዜ ይገናኛሉ።

ግምታዊ አሰላለፍ

ወልቂጤ ከተማ (4-3-3)

ይድነቃቸው ኪዳኔ

ዳግም ንጉሴ – ቶማስ ስምረቱ – ዐወል መሐመድ – አዳነ በላይነህ

አልሳሪ አልማህዲ – በረከት ጥጋቡ – ኤፍሬም ዘካርያስ

ጫላ ተሺታ – አህመድ ሁሴን – ሳዲቅ ሴቾ

ሲዳማ ቡና (4-3-3)

ፍቅሩ ወዴሳ

አማኑኤል እንዳለ – ሰንደይ ሙቱኩ – ግርማ በቀለ- ተስፉ ኤልያስ

ትርታዬ ደመቀ – ዮሴፍ ዮሐንስ – አበባየሁ ዮሐንስ

አዲስ ግደይ – ይገዙ ቦጋለ – ሀብታሙ ገዛኸኝ

© ሶከር ኢትዮጵያ