ቅድመ ዳሰሳ | ፋሲል ከነማ ከ ቅዱስ ጊዮርጊስ

በጎንደር ዐፄ ፋሲለደስ ስታዲየም የሚደረገውን የሳምንቱን ተጠባቂ ጨዋታ እንደሚከተለው ዳሰነዋል።

ባሳለፍነው ሳምንት በተደረገ የሊጉ መርሐ ግብር የመጀመሪያ የሜዳቸው ውጪ ድል መቐለ ላይ ያስመዘገቡት ፋሲል ከነማዎች የዋንጫ ተፎካካሪያቸውን በመርታት ደረጃ ሰንጠረዡ አናት ላይ ለመቀመጥ እና የሜዳ ላይ አልሸነፍ ባይነታቸውን ለማስቀጠል የነገውን ጨዋታ ይጠባበቃሉ።

የፋሲል ከነማ ያለፉት 5 ጨዋታዎች አቋም (ከቅርብ ወደ ሩቅ)
አሸነፈ አሸነፈ አቻ አሸነፈ ተሸነፈ

በሜዳቸው ሲጫወቱ እጅግ ጠንካራ የሆኑት ፋሲል ከነማዎች ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በሙጂብ ቃሲም ላይ ብቻ ጥገኛ በመሆን ነጥቦችን እየሰበሰቡ ይገኛሉ። ይህ ሁለገብ ተጨዋች ቡድኑ ከ6ኛ ሳምንት በኋላ ያስቆጠራቸው 7 ጎሎች ሁሉንም ከመረብ አገናኝቶ ቡድኑን ከፍተኛ ነጥብ አስገኝቷል። (በ6ኛ ሳምንት ከተደረገው የፋሲል እና የባህር ዳር ጨዋታ በኋላ ሙጂብ ብቻ ነው የክለቡ ግብ አስቆጣሪ) ይህ የተጨዋቹ ምርጥ ብቃት በገሃድ ክለቡን እየጠቀመ ቢገኝም ቡድኑን ወደ ፊት ተጎጂ ሊያደርግ እንደሚችል ይታሰባል። በተለይ ተጨዋቹ በሌለባቸው እና በተጋጣሚ ቡድን ተጨዋቾች በሚያዝበት (ማርክ በሚደረግበት) ወቅት ቡድኑ መፍትሄዎችን ከሌሎች ተጨዋቾቹ ማምጣት ይቸገራል። ነገም ከተጨዋቹ ወሳኝነት አንፃር ጠንካራ የተከላካይ መስመር ያላቸው ቅዱስ ጊዮርጊሶች ለሙጂብ ከፍተኛ ትኩረት አድርገው ወደ ሜዳ ሊገቡ ይችላሉ።

በተቃራኒው በተጋጣሚ ቡድን ተጨዋቾች ሙጂብ ከፍተኛ ትኩረት ማግኘቱ ሌሎች የቡድኑን የወገብ በላይ ተጨዋቾች ነፃነት ሊሰጥ እንደሚችል ይታሰባል። በተለይ ፈጣኖቹ እና ታታሪዎቹ ሽመክት እና ሱራፌል በመስመሮች መካከል በመገኘት የቅዱስ ጊዮርጊስን ጊዜ ከባድ ለማድረግ ይጥራሉ ተብሎ ይጠበቃል።

በሊጉ ዝቅተኛ ግብ ያስተናገደው (8) ፋሲል በነገው ጨዋታ ተከላካይ መስመሩ ሊፈተን ይችላል። በተለይ ከጨዋታ ጨዋታ እየበረታ የመጣውን የቅዱስ ጊዮርጊስ አስፈሪ የፊት መስመር ቡድኑ ለማቆም በከፍተኛ ደረጃ መታተር አለበት።

በባለሜዳዎቹ በኩል አብዱራህማን ሙባረክ በነገው ጨዋታ የማይሰለፍ ሲሆን ጋብሬል አሕመድ እና እንየው ካሣሁን ሙሉ ለሙሉ ከጉዳታቸው በማገገማቸው ለጨዋታው ዝግጁ ናቸው ተብሏል።

የቅዱስ ጊዮርጊስ ያለፉት 5 ጨዋታዎች አቋም (ከቅርብ ወደ ሩቅ)
አሸነፈ አሸነፈ አሸነፈ አሸነፈ አቻ

ከአስከፊ የሊጉ ጅማሮ በኋላ ወደ ትክክለኛው የአሸናፊነት መንገድ የገቡት ቅዱስ ጊዮርጊሶች ባሳለፍነው ሳምንት ያስመዘገቡትን የመጀመሪያ የሜዳ ውጪ ድል (ወልዋሎን 4-1 በማሸነፍ) በተከታታይ ለመድገም እና በደረጃ ሰንጠረዡ አናት ያላተውን ልዩነት አስፍተው ለመዝለቅ ጎንደር ከትመዋል።

ቀስ በቀስ እየተዋሀደ የመጣው ቡድኑ አሁን ላይ ከፍተኛ የተጋጣሚ ቡድን ስጋት ሆኗል። በተለይ ከወገብ በላይ የሚገኙት የቡድኑ ተጨዋቾች ለቡድናቸው በጎ ነገሮችን ለማምጣት የሚጥሩበት መንገድ የተጋጣሚን የተከላካይ መስመር ይረብሻል። ነገም ቡድኑ በሊጉ 6 ጎሎችን ለየብቻቸው ባስቆጠሩት ጌታነህ እና አቤል ታግዞ የፋሲልን የተከላካይ መስመር ሊፈታተን ይችላል። ከሁለቱ በተጨማሪ ምርጥ ብቃቱ ላይ የሚገኘው ጋዲሳ መብራቴ የሚያደርጋቸው የመስመር ላይ እንቅስቃሴዎች ነገ ይጠበቃሉ። በተለይ ተጨዋቹ ከመስመር እየተነሳ የሚያደርጋቸው ጥቃቶች እና ለቡድን አጋሮቹ የሚያመቻቻቸው እድሎች ተጋባዦቹን ተጠቃሚ ሊያደርጉ ይችላሉ።

በሊጉ አንድ ጊዜ ብቻ ሽንፈት ያስተናገደው ቅዱስ ጊዮርጊስ በነገው ጨዋታ ቀጥተኝነተን እንደሚመርጥ ይገመታል። ምናልባት ባለሜዳዎቹ ፋሲል ከነማዎች እንደ ከዚህ ቀደሞቹ የሜዳቸው ላይ ጨዋታዎች ኳስን ለመቆጣጠር ስለሚሞክሩ ቡድኑ ረጃጅም ኳሶችን ከመልሶ ማጥቃት እንቅስቃሴዎች ጋር አዳቅሎ ለጨዋታው ሊቀርብ ይችላሉ።

በፈረሰኞቹ በኩል ናትናኤል ዘለቀ፣ አስቻለው ታመነ እና ለዓለም ብርሃኑ በጉዳት ምክንያት ለነገው ጨዋታ ሙሉ ለሙሉ እንደማያደርሱ ሲገለፅ የሳልሀዲን ሰዒድ መሰለፍ አጠራጥሯል ተብሏል።

ይህንን ተጠባቂ ጨዋታ የአማራ መገናኛ ብዙሃን ኤጀንሲ በቴሌቪዥን እና በሬዲዮ አማራጮቹ በቀጥታ ለስፖርት ቤተሰቡ እንደሚያስተላልፍ ታውቋል።

እርስ በእርስ ግንኙነት

– ሁለቱ ቡድኖች በሊጉ እስካሁን ሰባት ጊዜ (ሁለት ፎርፌዎችን ጨምሮ) ተገናኝተው ቅዱስ ጊዮርጊስ 3 ጊዜ ሲያሸንፍ ፋሲል ከነማ 2 አሸንፏል። ሁለት ጊዜ ደግሞ አቻ ተለያይተዋል። የፎርፌ ጎሎችን ጨምሮ ቅዱስ ጊዮርጊስ 11 ሲያስቆጥር ፋሲል 9 አስቆጥሯል።

ግምታዊ አሰላለፍ

ፋሲል ከነማ (4-3-3)

ሚካኤል ሳማኬ

ሰዒድ ሀሰን – ከድር ኩሊባሊ – ያሬድ ባየ – አምሳሉ ጥላሁን

በዛብህ መለዮ – ሀብታሙ ተከስተ – ሱራፌል ዳኛቸው

ሽመክት ጉግሳ – ሙጅብ ቃሲም – ኦሲ ማውሊ

ቅዱስ ጊዮርጊስ (4-3-3)

ፓትሪክ ማታሲ

ደስታ ደሙ – ኤድዊን ፍሪምፖንግ – ምንተስኖት አዳነ – ሄኖክ አዱኛ

የአብስራ ተስፋዬ – ሙሉዓለም መስፍን – ሀይደር ሸረፋ

ጋዲሳ መብራቴ – ጌታነህ ከበደ – አቤል ያለው

© ሶከር ኢትዮጵያ