ሪፖርት| ባለ ሐት-ትሪኩ ኦኪኪ ደምቆ በዋለበት ጨዋታ ምዓም አናብስት ሀዋሳን ረምርመዋል

በኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ 14ኛ ሳምንት የመክፈቻ ጨዋታ መቐለ 70 እንደርታ በሜዳው ሀዋሳ ከተማን አስተናደዶ 5-1 በመርታት ነገ ጨዋታቸውን ከሚያደርጉት ተፎካካሪዎቹ ጋር ያለውን ልዩነት አጥብቧል። ኦኪኪ አፎላቢም በመቐለ መለያ የመጀመርያ ሐት-ትሪኩን ሰርቷል።

መቐለዎች ከባለፈው ሳምንት ቋሚ ተሰላፊዎቻቸው ዳንኤል ደምሴ (ቀይ ካርድ) ፣ ሄኖክ ኢሳይያስ እና ሳሙኤል ሳሊሶን በማሳረፍ በሙሉጌታ ወልደጊዮርጊስ፣ ያሬድ ከበደ እና ኤፍሬም አሻሞ ተክተዋል። ሀይቆቹም ባለፈው ሳምንት ጅማን ካሸነፈው ስብስብ ዳንኤል ደርቤ፣ ዘላለም ኢሳይያስ፣ ሄኖክ ድልቢ እና ሄኖክ አየለን በማሳረፍ በወንድማገኝ ማዕረግ፣ ፀጋአብ ዮሐንስ፣ ብርሀኑ በቀለ እና የተሻ ግዛው ተክተው ገብተዋል።

የባለሜዳዎቹ ሙሉ ብልጫ የታየበት የመጀመርያው አጋማሽ በሁለቱም ቡድኖች በኩል በርካታ ሙከራዎች የታዩበት ሲሆን ባለሜዳዎቹም ከበርካታ ጊዜያት በኃላ የአቀራረብ ለውጥ አድርገው የኳስ ቁጥጥር ብልጫ የወሰዱበት ነበር። በጥሩ መነቃቃት የጀመረው ጨዋታው ገና በአራተኛው ደቁቃ ነበር ግብ የተስተናገደበት። ኦኪኪ ኦፎላቢ ከሥዩም ተስፋዬ በጥሩ መንገድ የተሻገረለትን ኳስ አክርሮ በመምታት አስቆጥሮ ቡድኑን መሪ ማድረግ ችሏል።

ከግቡ በኋላም ወደ ተጋጣሚ ግብ ክልል ተጠግተው የግብ ዕድሎች መፍጠር ያላቆሙት መቐለዎች ኤፍሬም አሻሞ በተሰለፈበት የግራ መስመር በርካታ ዕድሎች ፈጥረዋል። ከነዚህም ኤፍሬም አሻሞ ከመስመር በጥሩ መንገድ አሻግሯት ተከላካዮች እንደምንም ያወጧት እና ኦኪኪ ኦፎላቢ ከሁለት ተከላካዮች መሐል አልፎ መቷት ቤሊንጋ የመለሳት ይጠቀሳሉ። ከተደጋጋሚ ሙከራ በኋላም በ12ኛው ደቂቃ ሥዩም ተስፋዬ ያሻማትን ኳስ ሙሉጌታ ወልደጊዮርጊስ ወደግብነት ቀይሮ የቡድኑን መሪነት ወደ ሁለት ከፍ አድርጓል።

ጨዋታው ገና በጊዜ በተቆጠሩ ጎሎች የከበደባቸው ሀዋሳዎች በሀያ ሦስተኛው ደቂቃ ይበልጥ ጨዋታው እንደሐከብድ ያደረገ ክስተት ተፈጥሯል። አለልኝ አዘነ ጥፋት ከሰራ በኃላ ዋና ዳኛው ብሩክ የማነብርሀን የቢጫ ካርድ ሲሰጡት ዳኛውን በግንባሩ ለመምታት በመሞከሩ በቀይ ካርድ ከሜዳ ተሰናብቶ ቀሪዎቹን ረጅም ደቂቃዎች እንግዶቹ በጎዶሎ ቁጥር ለመጫወት ተገደዋል።

ዘግይተው ወደ ጨዋታው እንቅስቃሴ የገቡት ሀይቆቹ የተሻለ ጫና በፈጠሩባቸው የመጀመርያ አጋማሽ የመጨረሻ ደቂቃዎች በርካታ ዕድሎች ፈጥረው በፍሊፕ ኦቮኖ ድንቅ ብቃት ጎል ሳይሆኑ ቀርተዋል። አለልኝ አዘነ በሁለት አጋጣሚዎች እና የተሻ ግዛው ያደረገው እጅግ ለግብ የቀረበ ሙከራም ይጠቀሳሉ። በተለይም አለልኝ አዘነ ከርቀት አክርሮ መቶ ፍሊፕ ኦቮኖ እንደ ምንም ያወጣው ኳስ እና የተሻ ግዛው አለልኝ አዘነ በግሩም ሁኔታ ያሻገረለትን ኳስ ተጠቅሞ በመምታት ፍሊፕ ኦቮኖ ያዳነው ሙከራ ሀይቆቹ ካደረጓቸው ሙከራዎች የተሻሉ ለግብ የቀረቡ ነበሩ።

እንደ መጀመርያ አጋማሽ ሁሉ የባለሜዳዎቹ ሙሉ ብልጫ የታየበት ሁለተኛው አጋማሽ መቐለዎች ምንም እንኳ እንደ መጀመርያው አጋማሽ በርካታ ንፁህ ዕድሎች ባይፈጥሩም በኳስ ቁጥጥር ረገድ ግን ከእንግዶቹ በብዙ መመዘኛ ተሽለው ታይተዋል። በስልሳኛው ደቂቃም ኦኪኪ ኦፎላቢ ከርቀት ግሩም ግብ አስቆጥሮ የግብ ልዩነቱን ወደ ሦስት ከፍ ማድረግ ችሏል። አጥቂው ራሱ አክርሮ መቶት ተከላካዮች ተደርበውት የመለሱት ኳስ በድጋሚ አክርሮ በመምታት ነው ግሩም ግብ ያስቆጠረው።

ናይጄርያዊው አጥቂ ኦኪኪ ከሦስት ደቂቃዎች በኋላ ሐት-ትሪክ የሰራበትን ጎል አስቆጥሯል። አጥቂው በሳጥን ውስጥ ከአማኑኤል ገብረሚካኤል ያገኛትን ኳስ አክርሮ በመምታት ነበር ግቡን ያስቆጠረው።

ባለሜዳዎቹ ከግቡ በኋላም በአማኑኤል ገብረሚካኤል አማካኝነት በሦስት አጋጣሚዎች እና በአስናቀ ሞገስ እጅግ ለግብ የቀረቡ ሙከርዎች አድርገው የግብ መጠኑን ከፍ የማድርግ አጋጣሚዎች አምክነዋል። በተለይም አስናቀ ሞገስ ያሬድ ብርሀኑ በጥሩ ሁኔታ ያቀበለውን ኳስ ተጠቅሞ መትቶ የግቡን ቋሚ ታካ የወጣችበት እና አማኑኤል ገብረሚካኤል ከሳጥኑ ጠርዝ መትቶ የግቡ ቋሚ የመለሰበት በባለሜዳዎቹ በኩል አስቆጪ ሙከራዎች ነበሩ።

በሁለተኛው አጋማሽ ተቀዛቅዘው የታዩት ሀዋሳ ከተማዎች ብሩክ በየነ ካደረጋት ብቸኛ ሙከራ ውጭ ይህ ነው የሚባል ሙከራ ማድረግ አልቻሉም። ያም ሆኖ በሥልሳ ዘጠነኛው ደቂቃ በመቐለ ሳጥን ውስጥ ኳስ በእጅ በመነካቷ የተሰጠውን ፍፁም ቅጣት ምት ብሩክ በየነ አስቆጥሮ ቡድኑን ከባዶ መሸነፍ አድኗል።

መደበኛ የጨዋታ ክፍለ ግዜ ተጠናቆ በተሰጠው ተጨማሪ ደቂቃ መቐለ የማሳረጊያ ጎል በቢያድግልኝ ኤልያስ አማካኝነት አስቆጥሯል። ተከላካዩ ከመሀል ሜዳ አርቆ የመታትን ኳስ የቤሊንጌ ኢኖህ ስህተት ታክሎባት ነበር ከመረብ ላይ ያረፈችው። ጨዋታውም በመቐለ 5-1 አሸናፊነት ሊጠናቀቅ ችሏል።

ጨዋታው በዚህ ውጤት መጠናቀቁን ተከትሎ መቐለዎች ከሁለት ጨዋታዎች ሽንፈት አገግማው ወደ ድል ሲመለሱ ሀዋሳ ከተማዎች ደረጃቸውን ለማሻሻል የነበራቸው እድል አባክነዋል።

©ሶከር ኢትዮጵያ