የአሰልጣኞች አስተያየት | ፋሲል ከነማ 2-2 ቅዱስ ጊዮርጊስ

በኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ 14ኛ ሳምንት ጎንደር ላይ ፋሲል ከነማ ከቅዱስ ጊዮርጊስ 2-2 ከተለያዩ በኋላ የሁለቱ ቡድን አሰልጣኞች አስተያየታቸውን እንደሚከተለው ሰጥተዋል።


“በራሳችን ያልተደራጀ እንቅስቃሴ ተቀጥተናል” ሥዩም ከበደ (ፋሲል ከነማ)

ስለ ጨዋታው

ጨዋታውን ስንመለከተው በጣም ጥሩ ነው። እስከዛሬ ካደረግናቸው ጨዋታዎች የዛሬው የተሻለ ነው። የመጀመሪያው ሰላሳ ደቂቃ በጣም ጥሩ ነበር። ተጫዋቾቹ የነበራቸው ጥረት በጣም ጥሩ ነበር። ከዚህ በፊት ስድስት ጨዋታ አሸንፈናል፤ ስባተኛውን ለማሸነፍ ያለንን ነገር ሁሉ አድርገናል። ያው እግር ኳስ በስህተት የታጀበ ነው፤ እረፍት ለመውጣት የተወሰነ ደቂቃ በቀረው ሰዓት በራሳችን ያልተደራጀ እንቅስቃሴ ተቀጥተናል። እና የመጀመሪያውን አጋማሽ 1-0 እየመራን ቢጠናቀቅ ኖሮ የተሻለ እድል ይኖረን ነበር ብዬ አስባለሁ። ሁለተኛው አጋማሽ ላይም ጥሩ በነበርንበት ሰዓትም እንደዛ አይነት ግብ ሲገባ አስደንጋጭ ነገር አለው። ከዛም ተነስተን ግብ ማስቆጠራችን ጥሩ ነው። ሶስታችንም በመሪነት ቦታው ተጣብቀናል። መቐለ፣ እኛም ጊዮርጊስም… አሁን አንድ ጨዋታ ይቀረናል፤ ያለንን መነሳሳት ይዘን የተሻለ ነገር እናደርጋለን ።

ስለ ቀይ ካርዱ

ጨዋታ ላይ ውስጥ ሆነህ እና ውጭ ሆነን የምናየው ይለያያል። የተጫዋቾቹ ስሜት ነው፤  በሁለቱም በኩል ሲታይ ትዕግስት የማጣት ጉዳይ ነው። ውጤት ከመፈለግ አኳያ ነው፤ ሆኖም እየደገፍኩት አይደለም እና ከዚህ ልንማር ይገባናል። እንደ ሀገር ያለው ውድድር ላይ ስፖርታዊ ጨዋነቱ ጥሩ ነው። በዚህ መቀጠል አለበት።

“እኔ የማስበው ስታዲየም የመጡ ደጋፊዎች በሙሉ ተዝናንተው እንደሄዱ ነው” ሰርዳን ዝቪጅኖቭ (ቅዱስ ጊዮርጊስ)

ስለ ጨዋታው

ዛሬ እኔ የማስበው ስታዲየም የመጡ ደጋፊዎች በሙሉ ተዝናንተው እንደሄዱ ነው። ምክንያቱም በዚህ ሰዓት ያሉ ጥሩ ተፎካካሪ ቡድኖች ናቸው ጨዋታ ያደረጉት። ጨዋታው በጣም አሪፍ ነበር፤ ሁለቱም ቡድን አጥቅቶ ነው የተጫወተው፤ አራት ግብ ተቆጥሯል። በመጀመሪያው አጋማሽ እኛ ጥሩ ነበርን፤ በሁለተኛው አጋማሽ ደግሞ ፋሲል ጥሩ ነበር ። ቢሆንም ግን አሁን ስለ ወደፊት ነው የምናስበው። ነጥብ ተጋርተን መሄዳችንም ጥሩ ነው ።

ስለ ውጤቱ

እንደ አጠቃላይ ካየኸው ከጨዋታው አንፃር ውጤቱ ጥሩ ነው። ነገር ግን ሁለት ለአንድ ከመራን በኋላ ስለሆነ አቻ የወጣነው ሁለት ነጥብ እንዳጣን ነው የማስበው።

ስለ ዳኝነት

ስለዳኝነት አስተያየት መስጠት አልፈልግም። ዳኛዋ ሥራዋን ነው የሰራችው። በውሳኔያቸው ጣልቃ መግባት ስለማልፈልግ አስተያየት አልሰጥም።

© ሶከር ኢትዮጵያ