ተደጋጋሚው የጅማ አባ ጅፋር ተጫዋቾች ልምምድ ማቋረጥ አሁንም ቀጥሏል

በደሞዝ ክፍያ በጊዜው አለመጠናቀቅ ምክንያት ልምምድ ማቋረጥ እየተለመደ በመጣበት ሊጋችን ጅማ አባ ጅፋሮች በለተለያየ ጊዜ ልምምድ ማቋረጥን ተላምደውታል።

በ14ኛ ሳምንት በሜዳቸው ድሬደዋ ከተማን በጎዶሎ ተጫውተው 2-1 ካሸነፉበት ጨዋታ በኃላ የጅማ አባ ጅፋር ተጫዋቾች ለተከታታይ ሦስት ቀናት ልምምድ መስራትን አቁመዋል። በሀዘን ምክንያት ከቡድኑ ጋር የማይገኙት አሰልጣኝ ጳውሎስ ጌታቸው አለመኖርም የቡድኑን ችግር አባብሶታል። የአምስት ወር ደሞዝ አልተከፈለንም የሚሉት ተጫዋቾቹ መፍትሔ በማጣታቸው ምክንያት አንዳንዶቹ ወደ ትውልድ ከተማቸው እየተጓዙ ይገኛል። የፊታችን ዓርብ በ15ኛ ሳምንት ሀዋሳ ከተማ ላይ ከሀዲያ ሆሳዕና ጋር የሚጫወቱት አባ ጅፋሮች እስካሁን ወደ ስፍራው ለመጓዝ ምንም አይነት እንቅስቃሴ አለማድረጋቸው። የቀጣዩን ጨዋታ የመጫወታቸውን ነገር አጠራጣሪ አድርጎታል።

ያለፉትን ሁለት ዓመት እየተንከባለለ የመጣው የጅማ አባ ጅፋር የፋይናስ ችግር ቡድኑን ከፍተኛ ውድቀት ውስጥ እየከተተው ሲገኝ የክለቡ ጉዳይ ያገባኛል የሚሉ አመራሮች ቸልተኝነት የከተማውን ማኅበረሰብ እና የስፖርት ቤተሰቡን ስም እና ክብር እያጎደፈ ይገኛል።

© ሶከር ኢትዮጵያ