“በእርግጠኝነት ነው የምነግርህ፤ ድሬደዋ ከተማን በሁለተኛው ዙር የሚያቆመው አይኖርም” በረከት ሳሙኤል ድሬደዋ ከተማ

በረከት ሳሙኤል ስለ ድሬዳዋ ቀጣይ ዕጣ ፈንታ ይናገራል

ድሬዳዋ ከተማ በ2008 ዳግመኛ ወደ ኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ከተቀላቀለ ጀምሮ ከዓመት ዓመት አሰልጣኝ በመቀያየርና የተሻለ ቡድን በመስራት ውጤታማ ይሆናል ቢባልም በየዓመቱ ደካማ የሜዳ ላይ እንቅስቃሴ እያሳየ እና ወደ ታችኛው ሊግ ለመውረድ አፋፍ እየቆመ መትረፉን ተያይዞታል።

ዘንድሮም ከለመደው የውጤት ቀውስ ውስጥ የሚገኘው ድሬደዋ ገና በጊዜ ነው አሰልጣኙን ማሰናበት የጀመረው። በሊጉ እስካሁን ባደረጋቸው 14 ጨዋታዎች አራት ጨዋታ በማሸነፍ፣ በሁለት ጨዋታ አቻ በመውጣት፣ በሰባት ጨዋታዎች ሽንፈት አስተናግዶ አስራ አራተኛ ደረጃ ላይ ይገኛል። አሳሳቢው የድሬደዋ ከተማ ወቅታዊ አቋም አስመልክቶ ያለፉትን አራት ዓመታት ቡድኑ ውስጥ በታታሪነት እያገለገለ የሚገኘው ተከላካዩ በረከት ሳሙኤል የቡድኑ መሠረታዊ ችግር እና በቀጣይ መስተካከል አለባቸው በሚባሉ ጉዳዮች ዙርያ ከሶከር ኢትዮጵያ ጋር አጭር ቆይታ አድርጓል።

እንደሚታወቀው ድሬደዋ ከተማ ከዓመት ዓመት ከስህተቱ ሳይማር ላለመውረድ እየተጫወተ ይፈኛል። አንተ በቡድኑ ውስጥ አራት አመት እንደቆየ ተጫዋች የድሬደዋ ከተማ መሠረታዊ ችግር ምንድነው ትላለህ?

በቡድኑ ውስጥ እንደመቆየቴ የተረዳሁት ነገር ቢኖር ቡድኑ በየዓመቱ አዳዲስ ተጫዋች የሚቀያየር መሆኑ ነው። አንድ ክለብ አዲስ ቡድን እየሰራ በሄደ ቁጥር ተጫዋቾቹ እስኪላመዱ ድረስ በሚኖረው ሒደት ውስጥ የምትፈልገውን ውጤት ለማግኘት የውጤት መገራገጭ ይኖራል። ብዙ ጊዜ ድሬዳዋን አይተህ እንደሆነ ሁለተኛው ዙር ላይ በጣም ጠንካራ ቡድን ነው የሚሆነው። ምክንያቱም አዲስ የመጡ ተጫዋቾች ከቡድኑ ጋር እየተላመዱ የሚመጡበት ጊዜ ስለሆነ በሙሉ አቅማቸው ስለሚጫወቱ ቡድኑን ውጤታማ ሲያደርጉት ትመለከታለህ። ቅዱስ ጊዮርጊስ ብዙ ዋንጫ ያነሳውን ጊዜ ስታይ እና ያለፉትን ሁለት ዓመታት ዋንጫ ያጣበትን ምክንያት ስትመለከት በአንዴ ከቡድኑ ጋር ረጅም ዓመት የቆዩ ተጫዋቾችን አሰናብቶ አዲስ ቡድን እየሰራ በመምጣቱ ምክንያት ነው። ዘንድሮ ግን ውድድሩ ገና ያላለቀ ቢሆንም ተጫዋቾቹ ከቡድኑ ጋር እየተላመዱ በመምጣታቸው ለዋንጫ እየተፎካከሩ ይገኛሉ። ድሬዳዋም የዚህ አይነት ችግር ውስጥ ነው የገባው፤ በየአመቱ አዳዲስ ተጫዋች በመጡ ቁጥር ቡድኑን እስክታደራጅ ድረስ አንደኛውን ዙር ትቸገራለህ። ሁለተኛው ዙር ሁሌም ድሬደዋ ጠንካራ ስለሚሆን በሊጉ ሊቆይ ችሏል። ዘንድሮም በእርግጠኝነት ነው የምነግርህ ድሬዳዋ ከተማን በሁለተኛው ዙር የሚያቆመው አይኖርም ።

በአንተ አገላለፅ የቡድኑ ቁልፍ ችግር ሁሌም አዲስ ቡድን መስራት ነው ካልክ ይህ በቀጣይ እንዲስተካከል ምን መደረግ አለበት ትላለህ?

አንድ ቡድን የረጅም ጊዜ እቅድ ሊኖረው ይገባል። ተጫዋችን ለአጭር ጊዜ ማስፈረም ተገቢ አይደለም። ቢያንስ ለሁለት ዓመት እንዲፈርሙ ቢደረግ ተጫዋቹ ቡድኑን ተላምዶ ጥሩ አገልግሎት መስጠት ይችላል። አሁን ለምሳሌ ከእኔ ጋር አንተነህ ተስፋዬ ጥሩ የመከላከል ጥምረት ነበረው። እንዲሁም ሌሎችም የተከላካይ ስፍራ ተጫዋቾች አብዛኛዎቹ የሉም። አሁን በተከላካይ ስፍራ ከሚጫወቱ ተጫዋቾች ውስጥ እኔ ብቻ ነው የቀረሁት፤ ቦታው ተበትኗል ማለት ነው። በግሌ ስታየኝ እኔ አሁን ጥሩ ደረጃ ላይ ነኝ ማለት እችላለው። ሆኖም እንደ ቡድን አብረውኝ ከሚጫወቱ ተጫዋቾች ጋር ለመላመድ ለጊዜው ተቸግሬያለው። ምክንያቱ ደግሞ የእነርሱ ችግር ሳይሆን መቀናጀት ስለሚቀረን ነው። ይህ ነገር ደግሞ ድሬዳዋን ጎድቶታል። በሚቀጥለው ዓመትም በተመሳሳይ አዲስ ልጅ የሚመጣ ከሆነ ችግሩም ይቀጥላል። ስለዚህ የረጅም ዓመት እቅድ ሊኖረው ውጤታማ የሚያደርገው ሰው ያስፈልገዋል።

በዘላቂነት ችግሮች የሚፈቱበትን መፍትሔ አስቀምጠህልኛል። ይሄ እንዳለ ሆኖ የሊጉ የአንደኛው ዙር ሊጠናቀቀድ የአንድ ጨዋታ ዕድሜ ይቀረዋል። ድሬዳዋ በሊጉ እንዲቆይ በግልህ እና እንደ ቡድን ምን ለመስራት አቅደሀል ?

አሁን በግሌ በጣም በራስ መተማመኔ የጨመረበት ጥሩ ብቃት ላይ እገኛለው። ቡድኔንም ለመጥቀም ከመቼውም ጊዜ በተሻለ ተዘጋጅቼ እገኛለው። ቅድም እንዳልኩህ በሁለተኛው ዙር ጠንክረን እንቀርባለን። ሁላችንም ከመቐለ ጨዋታ አንስቶ ቡድኑን ለመታደግ ጠንክረን እንሰራለን።

ድሬዳዋ ከመጣህ ጀምሮ ቡድኑ ምንም እንኳን በውጤት ቢቸገርም አንተ በግልህ ጥሩ የውድድር ዓመታትን እያሳለፍው ነው። ስለ ወቅታዊ አቋምህ አጫውተኝ ?

እኔ አሁን ትክክለኛ አቋሜ ላይ እገኛለሁ። ከድሬዳዋ በተጨማሪ ለኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን መጫወት ያለብኝ ደረጃ ላይ ነው የምገኘው። ይህን በሙሉ ልብ የምናገረው አሁን ካለኝ ነገር ተነስቼ እና አሁን ካሉት ተከላካዮች የሚያንስ አቅም ስሌለኝ ነው። አሰልጣኝ አብርሀም መብራቱ በእኔ መጠቀም ካለበት ጊዜው አሁን ነው ባይ ነኝ።

© ሶከር ኢትዮጵያ