ጅማ አባ ጅፋር ከብሩክ ገብረአብ ጋር ተለያየ

የጅማ አባጅፋሩ የመስመር እና የአማካይ ስፍራ ተጫዋች ብሩክ ገብረአብ ከክለቡ ጋር ተለያይቷል፡፡

በከፍተኛ ሊጉ ለስሑል ሽረ ሲጫወት ክለቡ ወደ ፕሪምየር ሊጉ ለመግባቱ ጉልህ ሚና ከነበራቸው ተጫዋቾች መካከል አንዱ የሆነውና በመስመር እንዲሁም በአማካይ ስፍራ ላይ የሚጫወተው ብሩክ ገብረአብ 2010 ክረምት ላይ ስሑል ሽረን ከለቀቀ በኃላ ጅማ አባጅፋርን መቀላቀሉ ይታወሳል፡፡ ተጫዋቹ ዐምና በክለቡ የመጀመሪያ ዓመት ቆይታው በተወሰነ መልኩ ክለቡን ያገለገለ ሲሆን ዘንድሮ ግን ከገጠመው መጠነኛ ጉዳት ጋር በተያያዘ በቋሚነት ለመሰለፍ ቢቸገርም ባለፉት ሶስት የሊጉ ጨዋታዎች ላይ ግን ከጉዳት አገግሞ በክለቡ ተጫውቷል፡፡ ሆንም ቀሪ የውል ጊዜ የሚቀረው ተጫዋቹ ለክለቡ ባስገባው የልቀቁኝ ጥያቄ መሠረት ሊለያይ ችሏል፡፡

ከክለቡ ጋር በተያያዘ ለሁለተኛው ዙር የፕሪምየር ሊጉ ጉዞ ከተወሰኑ ተጫዋቾች ጋር ሊለያይ እንደሚችል እና ከከፍተኛ ሊጉ ደግሞ ሌሎች አዳዲስ ተጫዋቾች ለማካተት ማሰቡን ሶከር ኢትዮጵያ ያገኘችው መረጃ ይጠቁማል፡፡

©ሶከር ኢትዮጵያ