ቅድመ ዳሰሳ | ኢትዮጵያ ቡና ከ ወላይታ ድቻ

አዲስ አበባ ላይ የሚደረገው የኢትዮጵያ ቡና እና የወላይታ ድቻን ጨዋታ እንደሚከተለው ተመልክተነዋል።

በተከታታይ አምስት የሊጉ ጨዋታዎች ድል ማድረግ ያልቻሉት ኢትዮጵያ ቡናዎች ከተደቀነባቸው የወራጅ ቀጠና ስጋት ለመውጣት እና የዓመቱን አጋማሽ በውጤት ለመቋጨት ድልን አልመው ወደ ሜዳ ይገባሉ።

የኢትዮጵያ ቡና ያለፉት 5 ጨዋታዎች አቋም (ከቅርብ ወደ ሩቅ)
አቻ አቻ ተሸነፈ ተሸነፈ አቻ

በቡድን ለውጥ (transition) ላይ ያሉት ኢትዮጵያ ቡናዎች አዲሱን የአሰልጣኝ ካሳዬ አራጌ ሃሳብ ሙሉ ለሙሉ ለመተግበር እየተቸገሩ ይመስላል። በተለይ ቡድኑ የተጋጣሚ የመከላከል ወረዳ ላይ ሲደርስ የሚያደርገው እንቅስቃሴ እጅግ ስልነት የጎደለው ሆኖ ይታያል።
ከኳስ ጋር ምቾት ያላቸው ተጨዋቾችን የያዘው ቡድኑ ነገም እንደ ከዚህ ቀደሞቹ ጨዋታዎች ኳስን በትዕግስት ይቆጣጠራል ተብሎ ይጠበቃል። በተለይ ብቃት፣ ቅልጥፍና እና ፍጥነት በተሞላቸው የአማካይ መስመር ተጨዋቾቹ ታታሪነት ታግዞ ቡድኑ ኳስን ያንሸራሽራል ተብሎ ይታሰባል። ነገር ግን ቡድኑ ባሳለፍነው ሳምንት ያሳየውን አማራጭ የጨዋታ አቀራረብ በተወሰኑ ቅፅበቶች ሊያስመለክት እንደሚችል ይገመታል። ምናልባት ወላይታ ድቻዎች መሐል ሜዳ ላይ የቁጥር ብልጫ የሚወስዱ ከሆነ እና የተከላካይ ክፍላቸውን ወደ መሐል ሜዳ በመግፋት የሚጫወት ከሆነ ቡናማዎቹ ረጃጅም ኳሶችን ከተከላካይ ጀርባ በመጣል በጎ ነገሮችን ለማምጣት ይጥራሉ። ለዚህ አማራጭ አጨዋወት ደግሞ ቡድኑ ፈጣን የመስመር አጥቂዎችን በመያዙ ሊጠቀም ይችላል።

ካለፉት 5 የሊጉ ጨዋታዎች ሁለት ጎል ብቻ ተጋጣሚ ላይ ያስቆጠሩት ባለሜዳዎቹ የፊት መስመራቸውን በአግባቡ ካላስተካከሉ እየተነቃቁ ባሉት ድቻዎች ሊፈተኑ ይችላሉ። ከዚህ ውጪ ድቻዎች የቡናን የተከላካይ መስመር እና የአማካይ መስመር የኳስ ቅብብል መንገድ የሚዘጉ ከሆነ ባለሜዳዎቹ ሊቸገር ይችላል።

በቡና በኩል የቡድን ዜና ለማግኘት ያደረግነው ጥረት አልተሳካም።

የወላይታ ድቻ ያለፉት 5 ጨዋታዎች አቋም (ከቅርብ ወደ ሩቅ)
አሸነፈ አሸነፈ አሸነፈ ተሸነፈ አሸነፈ

አሰልጣኝ ገብረክርስቶስ ቢራራን ካሰናበቱ በኋላ እጅግ የተነቃቁት ወላይታ ድቻዎች የዓመቱን ሦስተኛ የሜዳ ውጪ ድል በመዲናዋ ለማሳካት እና ከመሪዎቹ ጋር ያላቸውን የነጥብ ልዩነት ለማጥበብ ወደ ሜዳ ይገባሉ።

በወጣቱ አሰልጣኝ ደለለኝ ደቻሳ የሚመራው ቡድኑ ከነበረበት የወራጅ ቀጠና በአንድ ጊዜ በመስፈንጠር አምስተኛ ደረጃ ላይ ተቀምጧል። በተለይ ደግሞ እኚህ አሰልጣኝ ቡድኑን በዋና አሰልጣኝነት መምራት ከጀመሩ በኋላ ከተደረጉ 6 ጨዋታዎች 15 ነጥቦችን ቡድኑ በመሰብሰብ ጥሩ ቦታ ላይ ተቀምጧል።

ከወገብ በላይ ባሉት የቡድኑ ተጨዋቾች ታግዞ ጨዋታዎችን ለማሸነፍ የሚጥረው ቡድኑ ነገም የእነዚሁ አጥቂዎቹን ፍጥነት እጅግ የሚሻ ይመስላል።በተለይ ኢትዮጵያ ቡናዎች ኳስ ከኋላ እንዳይጀምሩ በማድረግ የተጋጣሚውን የኳስ ምስረታ ገና በእንጭጩ ለመቅጨት እንደሚጥር ይገመታል። ከዚህ ውጪ ባዬን ጨምሮ ያሉት የቡድኑ የማጥቃት ባህሪ ያላቸው ተጨዋቾች የመልሶ ማጥቃት እንቅስቃሴዎችን በመጠበቅ ቡናዎች ላይ ጥቃት ለመፍጠር እንደሚንቀሳቀሱ ይገመታል። በተጨማሪም ቡድኑ የአማካይ መስመር ተጨዋቾቹን ቁጥር በርከት አድርጎ ወደ ሜዳ በመግባት በባለሜዳዎቹ በኩል የጨዋታው የበላይነት እንዳይወሰድበት እንደሚሞክር ይታሰባል።

ፍጥነት አልባው የቡድኑ የኋላ መስመር በነገው ጨዋታ በቀላሉ ለፈጣኖቹ የቡና አጥቂዎች እጁን እንዳይሰጥ አስግቷል። በተለይ ቡድኑ የኋላ መስመሩን ወደ መሐል ሜዳው የሚገፋ ከሆነ በሽግግሮች ሊፍረከረክ ይችላል። ከምንም በላይ ደግሞ አንጋፋው የተከላካይ መስመር ተጨዋች ደጉ ደበበ በነገው ጨዋታ አለመኖሩ ቡድኑን ያጋልጠዋል ተብሎ ይታሰባል።

ወላይታ ድቻዎች በነገው ጨዋታ አንጋፋው ተከላካይ ደጉ ደበበን ብቻ በጉዳት ምክንያት የማያገኙ ይሆናል።

እርስ በርስ ግንኙነት

በሊጉ ለ12 ጊዜያት ተገናኝተው ሦስት ሦስት ጊዜ ሲሸናነፉ በስድስቱ ግንኙነት አቻ ተለያይተዋል። ቡና 10፣ ድቻ 8 አስቆጥረዋል።

ግምታዊ አሰላለፍ

ኢትዮጵያ ቡና (4-3-3)

ተክለማርያም ሻንቆ

አህመድ ረሺድ – ፈቱዲን ጀማል – ወንድሜነህ ደረጀ – አስራት ቱንጆ

ፍቅረየሱስ ተ/ብርሃን – አማኑኤል ዮሐንስ – ታፈሰ ሰለሞን

ሚኪያስ መኮንን – አቡበከር ናስር – አቤል ከበደ

ወላይታ ድቻ (4-3-3)

መክብብ ደገፉ

ያሬድ ዳዊት – ውብሸት ዓለማየሁ – አንተነህ ጉግሳ – ፀጋዬ አበራ

በረከት ወልዴ – ተስፋዬ አለባቸው – እድሪስ ሰዒድ

እዮብ ዓለማየሁ – ባዬ ገዛኸኝ – ቸርነት ጉግሳ

© ሶከር ኢትዮጵያ

error: