ሪፖርት | ይገዙ ቦጋለ በድጋሚ ሲዳማ ቡናን ታድጓል

በኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ 15ኛው ሳምንት ሀዋሳ ላይ ሲዳማ ቡና በሰበታ ከተማ ተፈትኖም ቢሆን 1ለ0 ድል አድርጓል፡፡

ሲዳማ ቡናዎች ባሳለፍነው ሳምንት ከወልቂጤ ጣፋጭ ሦስት ነጥብ ይዘው ሲመለሱ ከተጠቀሙበት ተሰላፊዎች ውስጥ በአንድም ተጫዋች ላይ ለውጥ ሳያደርጉ ወደ ሜዳ ሲገቡ ሰበታ ከተማ በአዲስ አበባ ስታዲየም ከኢትዮጵያ ቡና ጋር ያለ ግብ ካጠናቀቀው ቡድን በአራቱ ላይ ቅያሪን አድርጓል፡፡ ሲይላ ዓሊ፣ አቤል ታሪኩ፣ መስዑድ መሐመድ እና ኃይለሚካኤል አደፍርስን በማስወጣት ጌቱ ኃይለማርያም፣ ደሳለኝ ደባሽ፣ ናትናኤል ጋንቹላ እና ሳሙኤል ታዬን ቀዳሚ ተሰላፊ በማድረግ ገብቷል፡፡

ሲዳማ ቡናዎች በቅርቡ ህይወቱ ላለፈው የቀድሞው ተጫዋቻቸው ሞገስ ታደሰ ምስል ያለበት ቲሸርት በማሰራት ሀዘናቸውን የገለፁ ሲሆን ጨዋታውም በህሊና ፀሎት ተጀምሯል፡፡

በመጀመሪያዎቹ አስራ አምስት ደቂቃዎች ሲዳማ ቡና ኳስ ቁጥጥር እና ተሻጋሪ ኳሶች ተሽሎ የታየ ሲሆን በቶሎ ወደ ግብ በመድረስ ጥሩ ቢንቀሳቀሱም አጠቃቀም ላይ ክፍተት ተስተውሎባቸዋል። 6ኛው ደቂቃ ላይ ግሩም አሰፋ ከሰበታው ተከላካይ ጌቱ እግር ነጥቆ ለይገዙ ቦጋለ ሰጥቶት ተጫዋቹ ባለመረጋጋቱ መጠቀም ሳይችል ቀርቷል፡፡ በመልሶ ማጥቃት የተገኘችን ኳስ ሀብታሙ ገዛኸኝ በቀኝ በኩል በረጅሙ ሲያሻግር ሲቻኮል የነበረው ይገዙ ቦጋለ አግኝቷት እንደምንም ወደ ግብ መትቶ ከግቡ መስመር ላይ ግብ ጠባቂው ዳንኤል አጃይ በግሩም ሁኔታ ያወጣበት እንዲሁም በ13ኛው ደቂቃ ሀብታሙ ገዛኸኝ የፈጠራት መልካም አጋጣሚ አዲስ ግደይ ጋር ደርሳ ተጫዋቹ ሁለት ጊዜ ገፋ አድርጎ ወደ ግብ ሲመታ እንደምንም ብሎ ዳንኤል አጃይ የመለሰበት እንደ ማሳያ የሚነሱ ነበሩ፡፡

ለአስራ አምስት ደቂቃዎች ያህል አስፈሪ የነበሩት ሲዳማ ቡናዎች ወደ መቀዛቀዙ ሲገቡ በአንፃሩ የአሰልጣኝ ውበቱ አባተው ቡድን እየተነቃቃ ወደ ጨዋታ ገብቷል፡፡ በተለይ ታደለ መንገሻ የግል ጥረቱን በመጠቀም ወደ ፊት እየተሳበ በመጫወት የፈጠራቸው አጋጣሚዎች ቀላል የሚባሉ አልነበሩም። ታደለ በተለይ ሁለት ተጫዋቾች አልፎ ወደ ሳጥን ተጠግቶ ያሻገራትን ደሳለኝ ደባሽ በግንባር ገጭቶ ለጥቂት የወጣችበት ተጠቃሽ ዕድል ነበረች። በዚህ ሒደት ብርሀኑ አሻሞ ከሰበታ ቅብብል አቋርጦ ያገኛትን ኳስ ከሳጥን ውጪ ወደ ግብ አሻምቶ ይገዙ ቦጋለ ማቀበል እየቻለ ሳይጠቀምባት የቀረው በሲዳማ በኩል አስቆጪ አጋጣሚ ሆናለች፡፡

ወደ መልበሻ ክፍል ለማምራት አስር ደቂቃዎች ሲቀሩ ሁለት ክስተቶች ተመልክተናል። የሲዳማ ቡናው አማካይ ዮሴፍ ዮሐንስ ቅጣት ምት ለመምታት ከሌሎች ተጫዋቾች ጋር የፈጠረው እሰጣ ገባ እና አሰልጣኝ ውበቱ አባተ ተጫዋቾቻቸው ወደ ግብ ሲደርሱ መረጋጋት ሲሳናቸው በተደጋጋሚ በመመልከታቸው እግራቸው ስር የነበረውን የፕላስቲክ ውሀ በመወርወር ስሜታዊ ሲሆኑ ያየንበት ሌላኛው የጨዋታው አካል ነበር፡፡ በጭማሪ የእረፍት መውጫ ሰዓት ላይ ናትናኤል ጋንቹላ ሰበታን መሪ የምታደርግ ኳስን ቢያገኝም ተከላካዮች ተረባርበው ወደ ውጪ አውጥተውበታል፡፡

በእረፍት ሰዓት ባለፈው ሳምንት ሲዳማ ቡና ከወልቂጤ ከተማ ሲጫወቱ በተፈጠረ ረብሻ ጉዳት ገጥሟቸው በሆስፒታል ለሚገኙ የሲዳማ ቡና ደጋፊዎች የገንዘብ ማሰባሰብ ስራ ከተከናወነ በኋላ ሁለተኛው አጋማሽ ተጀምሯል፡፡ ሰበታ ከተማዎች ፍፁም ተሻሽለው በቀረቡበት እና ሲዳማ ቡና ከርቀት በሚያገኙት አጋጣሚ ዕድሎች ለማግኘት የሞከሩበት፤ የተጫዋቾች ስርአት አልበኝነት የታየበት እንዲሁም የእለቱ ዋና ዳኛ ተፈሪ አለባቸው እግሩ ላይ ጉዳት ገጥሞት ለመቋረጥ የተገደደበት የሁለተኛው አጋማሽ ዋነኛ ተጠቃሽ ሁነቶች ነበሩ፡፡

ሰበታ ከተማ አስቻለው ግርማን ለውጦ ካስገባ በኋላ ይበልጡኑ ወደ ሲዳማ ግብ ክልል ሰብሮ ለመግባት የሚያደርገው ጥረትን ያሳመረ ሲሆን ተጫዋቹም ከሳሙኤል ታዬ ጋር የፈጠረው ጥምረትም ጥሩ ነበር፡፡ ሲዳማ ቡናዎችም በእንቅስቃሴ ይበለጡ እንጂ አልፎ አልፎ በሚያገኙት ቀዳዳ አልያም ደግሞ ከርቀት የሚመቱት ኢላማውን የጠበቀ ሙከራ ቀላል የሚባሉ ዕድሎች አልነበሩም፡፡ ብርሀኑ አሻሞ ከርቀት አክርሮ መቶ ዳንኤል አጄ በያዘበት ሙከራ ወደ ግብ ለመጠጋት የሞከሩት ሲዳማ ቡናዎች አበባየው ዮሐንስ መሀል ለመሀል አሾልኮ ሰቶት አዲስ ግደይ ሳይደርስባት የቀረችው አስቆጪ ዕድል አሁንም ተጠቃሿ ነበረች፡፡

ቀዳዳዎችን እየፈለጉ ወደ ግብ ሲጠጉ የነበሩ ሲዳማዎች 56ኛው ደቂቃ ላይ ግብ አስቆጥረዋል፡፡ በጨዋታው ጥሩ የነበረው አበባየው ዮሀንስ ከሳጥን ውጪ አክርሮ የመታውን ኳስ ዳንኤል አጄ ለመያዝ ተቸግሮ ሲተፋው ከፊት ለፊት የነበረው ይገዙ ቦጋለ ደርሶ ወደ ግብነት ለውጧት ቡድኑን መሪ አድርጓል፡፡

ከግቧ በኃላ ለማስጠበቅ ካልሆነ በስተቀር ወደ ፊት ከመሄድ ከቆጥበው የታዩት ሲዳማ ቡናዎች በሰበታ ከተማ ብልጫ ተወስዶባቸዋል፡፡ በተለይ አስቻለው ግርማን ማዕከል አድርገው ማጥቃቱ ላይ ያልቦዘኑት ሰበታዎች አንተነህ ተስፋዬ ባደረጋት የርቀት ሙከራ የሲዳማን ግብ ለመፈተሽ ተጠግተዋል፡፡ ሳሙኤል ታዬ በግል ጥረቱ ሁለት የሲዳማ ተጫዋቾችን አልፎ ከርቀት አክርሮ ወደ ግብ መትቶ ብረት የመለሰችበት ምናልባት ሰበታን አቻ ለማድረግ በጣም የቀረበች አስቆጭ ዕድል ነበረች፡፡

ሲዳማ ቡናዎች 78ኛው ደቂቃ ይገዙ ቦጋለ አግኝቶ መጠቀም ካልቻላት አንድ ኳስ ውጪ ሌላ እድል መፍጠር ያልቻሉ ሲሆን የመጨረሻዎቹን አስር ደቂቃዎች ተጨማሪ ተጫዋቾች በማስገባት ጫና ማሳደራቸውን የቀጠሉት ሰበታዎች ተጨማሪ ሙከራዎች አድርገዋል። ሆኖም 87ኛው ደቂቃ ቀይረው ያስገቡትን አጥቂው ባኑ ዲያዋራን በቀይ ካርድ አጥተዋል፡፡ ቀድሞ ቢጫ ካርድ አይቶ የነበረው ባኑ ከግርማ በቀለ ጋር ኳስን ለመሻማት በሚዘልበት ወቅት በክርኑ መቶታል በማለት በቀይ ካርድ ከሜዳ ተወግዷል፡፡ ተጫዋቹ እኔም ተመትቻለሁ አልወጣም በማለት ያንገራገረ ሲሆን የእለቱን ዳኛ ለመማታት ሲጋበዝም ታይቷል። ተጫዋቹን ለማስወጣት በተደረገ ጥረት የተነሳ ጨዋታው ለአራት ደቂቃ ለመቋረጥ ሲገደድ በሒደቱ ለአሰልጣኝ ውበቱ አባተም ቢጫ ካርድ ተሰጥቷቸዋል፡፡

ጨዋታው ሊጠናቀቅ በተሰጠው ጭማሪ ላይ የዕለቱ ዋና ዳኛ ተፈሪ አለባቸው እግሩ ላይ ሕመም አጋጥሞት ለአምስት ያህል ደቂቃዎች በሲዳማ ቡና የህክምና ባለሙያዎች እርዳታ ካገኘ በኋላ በድጋሚ መምራት የቻለ ሲሆን ተጨማሪ ግብ ሳይቆጠርበት ጨዋታው 1ለ0 ተጠናቋል፡፡

ጨዋታው ተጠናቆ ወደ መልበሻ ክፍል በሚያመሩበት ወቅት የሰበታ ከተማ ደጋፊዎች የቀድሞ አሰልጣኝ ክፍሌ ቦልተናን ስም በመጥራት አሰልጣኝ ውበቱ አባተን ሲቃወሙ ተመልክተናል። ጨዋታው ተጠናቆ የሰበታ ከተማ የቡድን አባላት ወደ ሆቴል በመኪና በሚያመሩበት ወቅትም በርካታ የሰበታ ከተማ ደጋፊዎች ተጫዋቾቹ ላይ ተቃውሞን ያሰሙ ሲሆን አሰልጣኝ ውበቱ አባተ ላይ ጥቃት ለመሰንዘር ሙከራንም ሲያደርጉ አይተናል። በተፈጠረው ግርግርም አሰልጣኙ በፀጥታ አካላት እና በአንዳንድ ሰዎች ታጅበው ወደ ሆቴላቸው ሄደዋል፡፡

© ሶከር ኢትዮጵያ