የአሰልጣኞች አስተያየት | ድሬዳዋ ከተማ 1-0 መቐለ 70 እንደርታ

በአስራ አምስተኛ ሳምንት የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ድሬዳዋ ከተማ በሜዳው መቐለ 70 እንደርታን 1-0 በሆነ ጠባብ ውጤት ካሸነፈበት ጨዋታ በኋላ የሁለቱ ቡድኖች አስተያየታቸውን እንደሚከተለው ሰጥተዋል።

”አሁንም ያለብን ችግር ግብ ማስቆጠር ነው” ፍስሐ ጥዑመልሳን (ድሬዳዋ ከተማ )

ስለ ጨዋታው

እንግዲህ ዛሬ በሰንጠረዡ አናት ላይ ካለ ቡድን ጋር ነው የተጫወትነው። እኛ ደግሞ ታች ነው ያለነው። ቡድናቸው ጥራት ባላቸው ተጫዋቾች የተሞላ እና ውጤታቸውም ለተጨማሪ ውጤት የሚያበረታታ ነው። እኛ ደግሞ ከሽንፈት መልስ ነው ከጅማ የመጣነው። አሁንም ያለብን ችግር ግብ ማስቆጠር ነው። ብዙ ግብ ላይ ደርሰናል። እነሱ የኛን ያህል ግብ ላይ አልደረሱም። ያው ባለቀ ሰዓት ግብ በማስቆጠራችን ማሸነፍ ችለናል።

በሁለተኛው ዙር ምን አይነት ለውጦች እንጠብቅ?

እንግዲህ መጀመሪያ እንዳያችሁት የተከላካዩ መስመር በአንድ ወይም በሁለት ደቂቃ ግብ የሚቆጠርበት ነበር። አብዛኛውን ስራ የሰራነው እዛ ላይ ነው። ማጥቃቱም ላይ እየሰራን ነው መጀመሪያ ላይ ግብ ላይ ብዙ አንደርስም ነበር። ዋናው መድረሱ ነው፤ ግቡ ደግሞ እየተሰራ ይመጣል። በቀጣይ ደግሞ የምንጨምራቸው ተጫዋቾች ስላሉን እነሱን አቀናጅተን የተሻለ ነገር ለማድረግ እንሞክራለን ።

በርከት ያለ ደጋፊ ስለመገኘቱ?

እኔም ተጫዋች ነበርኩ። ደጋፊው ጥሩ ነገር ካላገኘ ይሸሽሃል፤ ጥሩ ካልሆንክ አይደግፍህም። ስለዚህ ያ ነው የታየው። አሁን እኛ ሁለተኛ ዙር ጥሩ ነገር ከሰራን የግድ እናመጣዋለን። ስለዚህ እኛ ስራ ይጠበቅብናል። አሁንም ይሄ ውጤት አያኩራራንም። ያለንበት ነገር የማያኩራራ ስለሆነ አሁንም ትኩረት አድርገን ስራ ነው መስራት ያለብን።



”በመከላከል ላይ የምንፈጥራቸው ስህተቶች ዋጋ እያስከፈሉን ነው ”ገብረመድህን ኃይሌ (መቐለ 70 እንደርታ)

ስለ ጨዋታው

የዛሬው ጨዋታ እንግዲህ በኳስ ጨዋታ ሊያጋጥም የሚችል ነገር ያጋጠመን። ማለትም አጋጣሚዎችን ስታገኝ አለመጠቀም አንድ ትልቅ ችግር ነው። ሁለተኛው ደግሞ እድለኛ አልነበርንም፤ በጣም ብዙ ኳሶች ናቸው ግብ ሊሆኑ የሚችሉ አጋጣሚዎች ናቸው። ግን እነዛን ኳሶች መጠቀም ባለመቻል ከዛ በኋላ በተፈጠረው የግብ ጠባቂ እና የተከላካይ አለመናበብ በተፈጠረ ስህተት ግብ ተቆጠረብን። በመከላከል ላይ የምንፈጥራቸው ስህተቶች ዋጋ እያስከፈሉን ነው። በርግጥ ብልጭ ድርግም ሚል ጨዋታ ነበር መሐል ላይም አሁንም ችግር እንዳለብን ያሳየ ጨዋታ ነው። ነገር ግን አጠቃላይ ስታየው ተሸንፈን መውጣት አልነበረብንም።

ስለ ተጋጣሚ?

ጥሩ ነው፤ እንግዲህ የሚችሉትን ያህል ተንቀሳቅሰዋል። ያው ታችም ስለሆኑ መፍጨርጨር የግድ ነው። አጋጣሚውን መጠቀም በራሱ አንድ ትልቅ ነገር ነው።

© ሶከር ኢትዮጵያ