ሪፖርት | የደጋፊዎች ግጭት ጥላ ባጠላበት ጨዋታ ኢትዮጵያ ቡና ዙሩን በድል ደምድሟል

15ኛ ሳምንት የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ መርሐግብር ዛሬም ቀጥሎ ሲውል አዲስ አበባ ስታዲየም ላይ ወላይታ ድቻን ያስተናገደው ኢትዮጵያ ቡና 3-1 ሲያሸንፍ ጋብ ብሎ የነበረው የደጋፊዎች ግጭት አሁንም አገርሽቷል።

ኢትዮጵያ ቡና በሳምንቱ መጀመሪያ ከሰበታ ከተማ ጋር አቻ ከተለያየው ቡድን ውስጥ አማካዩ አማኑኤል ዮሐንስና የመስመር አጥቂው አቤል ከበደን አስወጥተው በምትካቸው ዓለምአንተ ካሳ እና ሀብታሙ ታደሰን በማስገባት ወደ ጨዋታው ሲገቡ በአንፃሩ በሜዳቸው ባህር ዳር ከተማን የረቱት ድቻዎች ደግሞ በጉዳት በዛሬው ጨዋታ ባልነበረው ደጉ ደበበ ምትክ ባዬ ገዛኸኝን ወደ መጀመሪያ ተሰላፊነት በመመልስ ወደ ጨዋታው ቀርበዋል።

ከጨዋታው መጀመር አስቀድሞ እና በጨዋታው ወቅት በተለይ በቅርብ ጊዜያት ከውጤት መጥፋት ጋር በተያያዘ በአዲስ አበባ ስታዲየም ቁጥራቸው ቀንሶ ይስተዋል የነበሩት የወላይታ ድቻ ደጋፊዎች ከሌላው ጊዜ በተሻለ በቁጥር በርከት ብለው የተመደበላቸውን ቦታ ጠቧቸው ለማስተዋል ችለናል።

በመጀመሪያው አጋማሽ የጨዋታ ክፍለ ጊዜ ወላይታ ድቻዎች ኢትዮጵያ ቡና ኳስን በነፃነት እንዳይመሰርቱ ለማድረግ በቁጥር በርከት ብለው በተቃራኒ የሜዳ ክፍል በተደጋጋሚ ለመግባት ሲሞክሩ የኃለኛው አራት የተከላካይ ክፍል ደግሞ ተነጥሎ በራሱ ሜዳ ሲቀሩ በተደጋጋሚ የተስተዋለበት እና ኢትዮጵያ ቡናዎች ደግሞ ይህን በመስመሮች መካከል የሚገኝን እጅግ ሰፊ ክፍተትና የተነጠለውን የወላይታ ድቻ የተከላካይ ክፍል ለማጥቃት እጅግ ተቸግረው ተስተውሏል።

በ5ኛው ደቂቃ ወደ ቀኝ ካደላ ቦታ ከተገኘ የቅጣት ምት ኳስ በነፃ አቋቋም የነበረው ተስፋዬ አለባቸው ተቆጣጥሮ ወደ ግብ በላካትና ከግቡ አናት በላይ በወጣችበት ኳስ የመጀመሪያ ሙከራውን ያገኘው ጨዋታ በ12ኛውና በ13ኛው ደቂቃ ዓለምአንተ ካሳ ከሳጥን ውጭ እንዲሁም ታፈሰ በተከላካዮች መካከል ያሸለከለትን ኳስ ሀብታሙ አጥብቦ ገብቶ ሞክራት ወደ ውጭ በወጡባቸው ኳሶች ባለሜዳዎቹ የመጀመሪያ ሙከራዎችን አስመልከተውናል።

በ21ኛው ደቂቃ ኢትዮጵያ ቡናዎች ኳስን ለመመስረት ባደረጉት ጥረት ተክለማርያም ሻንቆ የማቀበያ አማራጮቹ በሙሉ በተቃራኒ ተጫዋቾች በተዘገቡበት ሂደት ወደ ፊት በተሻለ አቋቋም ይገኝ ለነበረው አስራት ቱንጆ ለማቀበል ያሰበው ኳስ በባዬ ገዛኸኝ ቢቆረጥም በረኛው መልሶ ኳሱን ለማግኘት የሞከረበት እንዲሁም በመቀጠል ኳሱን ያገኘው አለምአንተ ካሳ በአደገኛ ቀጠና ውስጥ በቁጥር ተበልጠው ኳሱን ከማራቅ ይልቅ በአጭር ተቀባብለው ለመውጣት የሞከሩበት መንገድ እጅግ ድንቅ የሚባል ነበር።

ምንም እንኳን ፈጠን ባለ አጨዋወት በድቻ የሜዳ አጋማሽ ይገኝ የነበረውን የተከፋፈተውን የሜዳ ክፍል በመጠቀም ረገድ ደካማ የነበሩት ኢትዮጵያ ቡናዎች ከተጋጣሚያቸው በተሻለ ተደጋጋሚ የግብ እድሎችን ለመፍጠር ሞክረዋል። በ26ኛው ደቂቃ አስራት ቱንጆ ወደ ግራ ከጠበበ አንግል በቀጥታ የመታውን የቅጣት ምት ኳስ መክብብ ደገፉ እንደምንም ያዳነበት እንዲሁም በ27ኛው ደቂቃ ታፈሰ ሰለሞን በተመሳሳይ ያሾለከለትን ኳስ ሀብታሙ አግኝቶ ከድቻ ተከላካዮች ጋር ታግሎ የሞከረውን በረኛ ሲመልስበት ደግም ኳሷን በእጅ ነክቶ ለማስቆጠሮ ያደረገው ጥረት የቢጫ ካርድ ሰለባ ለመሆን ተገዷል።

ወላይታ ድቻዎች በመልሶ ማጥቃት እንቅስቃሴ ወደ መሀል ተጠግቶ ለመከላከል ይሞክር የነበረውን ኢትዮጵያ ቡና በተደጋጋሚ ሲፈተኑ ተስተውሏል። ይህ ጥረታቸው ግን በስተመጨረሻም ሰምሮላቸው በ32ኛው ደቂቃ ተስፋዬ አለባቸው ከራሳቸው የሜዳ አጋማሽ ወደ መሀል ሜዳ እጅጉን የተጠጋ የቡና ተከላካዮች ጀርባ ያሳለፈለትን ኳስ ተቆጣጥሮ ባዬ ገዛኸኝ እየነዳ በመግባት በተረጋጋ አጨራረስ ቡድኑን መሪ ያደረገች ግብ ማስቆጠር ችሏል።

ከግቧ መቆጠር መልስ በነበሩት ቀሪ የመጀመሪያ 45 ደቂቃ የጨዋታ ክፍለ ጊዜ ኢትዮጵያ ቡና ይበልጥ በጨዋታውን በበላይነት ተቆጣጥረው ተደጋጋሚ እድሎችን ለመፍጠር ጥረት አድርገዋል። በርካታ እድሎችን መፍጠር የቻሉት ቡናዎች በሀብታሙ ታደሰ በሁለት አጋጣሚዎች እንዲሁም እንዲሁም በፍቅረየሱስ ተ/ብርሃን ለግብ የቀረቡ ሲሆን በተጨማሪም በ39ኛው ደቂቃ በረጅሙ የተላከለትን ኳስ አቡበከር ናስር የአንተነህ ጉግሳን ስህተት ተጠቅሞ ያገውን ኳስ ከድቻው በረኛ ጋር 1ለ1 ተገናኝቶ እጅግ የሚያስቆጭ አጋጣሚ ሊያመክን ችሏል።

በድቻዎች 1-0 የበላይነት ከተጠናቀቀው የመጀመሪያ አጋማሽ መልስ በሁለተኛው አጋማሽ ኢትዮጵያ ቡናዎች ውጤቱን ለመቀልበስ እጅግ ከፍተኛ ጥረት አድርገዋል። ከመጀመሪያው አጋማሽ ከነበራቸው የመልሶ ማጥቃት ፍላጎት ረገድ በሁለተኛው አጋማሽ ተዳክመው የተስተዋሉት ወላይታ ድቻዎች በ57ኛው ደቂቃ የቡናው ግብጠባቂ ተክለማርያም ከግብ ክልሉ ወጥቶ ለማቀበል ሲል የተሳሳተውን ኳስ ተስፋዬ አለባቸው ከረጅም ርቀት አግኝቶ ወደ ግብ የላከውና ወደ ውጭ ከወጣበት ኳስ ውጭ ይህ ነው የሚባል የግብ እድል ለመፍጠር ተቸግረው ተስተውሏል።

ከመጀመሪያው አጋማሽ በተሻለ ፈጥነው ወደ ተጋጣሚ የግብ ክልል ለመድረስ ፍላጎት የነበራቸው ኢትዮጵያ ቡናዎች ረጃጅም ኳሶችን በተደጋጋሚ ለመጠቀም ከፍተኛ ጥረት ሲያደርጉ ተስተውሏል። ኢትዮጵያ ቡና ፍፁም የበላይ በነበሩበት የጨዋታ አጋማሽ በ50ኛው ደቂቃ ከቅጣት ምት አለምአንተ ያሻማውን ኳስ ፈቱዲን የመጀመሪያ ኳስ በማሸነፍ ከግቡ ቅርብ ርቀት ለነበረው አቡበከር አቀብሎት ያመከናት እንዲሁም በ60ኛው ደቂቃ እንደመጀመሪያው አጋማሽ ሁሉ አስራት ቱንጆ ወደ ግራ ከጠበበ አንግል ከቅጣት ምት ሞክሮ መክብብ በግሩም ሁኔታ ያዳነበት ኳስ ተጠቃሽ ሙከራ ነበር።

ጫናቸውን አጠናክረው የቀጠሉት ኢትዮጵያ ቡናዎች በግሩም አንድ ሁለት የገቡትን ኳስ አህመድ ከቀኝ ሳጥን ጠርዝ አፈትልኮ ገብቶ ከሞከራትና ለጥቂት ቋሚው ታካ ከወጣችበት ሞክራ ጥቂት አፍታ በኃላ በ66ኛው ደቂቃ ሚኪያስ መኮንን ከመሀል እየነዳ የድቻ ተጫዋቾች ቀንሶ ወደ ግራ በተለጠጠ አቋቋም ላይ ለነበረው ሀብታሙ ሰጥቶ ተጫዋቹ በግል ጥረት አጥብቦ በመግባት የአቻነቷን ግብ ማስቆጠር ችሏል።

ከግቧ መቆጠር በኋላ ይበልጥ የተነቃቁት ቡናዎች በአንድ ደቂቃ ልዮነት በታፈሰ ሰለሞንና አቡበከር ናስር በተከታታይ አስደናቂ አጋጣሚዎችን ፈጥረው መጠቀም ሳይችሉ ቀርተዋል። አሁንም ተጨማሪ ጎል ለማግኘት እየታተሩ የነበሩት ቡናዎች በ73ኛው ሀብታሙ ታደሰ ከግራ መስመር አጥብቦ ገብቶ ወደ ግብ የላከውና እንዲሁም በ74ኛው አቡበከር ድቻ ሳጥን ውስጥ ለሚኪያስ አቀብሎት ወደ ግብ የላካቸውን ሁለት አደገኛ አጋጣሚዎች በድቻው ግብጠባቂ መክብብ ጥረት ግብ ከመሆን ድነዋል።

በ79ኛው ደቂቃ ኢትዮጵያ ቡናዎች በሜዳው የላይኛው ክፍል ሲደርሱ የቡድኑ ሁነኛ የጥቃት አማራጭ የሆነው አህመድ ድንገተኛ ከኳስ ውጭ ሩጫውን ተጠቅሞ የደረሰውን ኳስ ከቀኝ የድቻ ሳጥን ሰብሮ በመግባት ወደ መሀል ያሻማውን ኳስ ውብሸት ዓለማየሁ በቅርቡ የነበረው አቡበከር እንዳይጠቀምበት ለማድረግ ባደረገው ጥረት ወደ ራሱ ግብ ገጭቶ የቡናን ሁለተኛ ግብ ማስቆጠር ችሏል።

በተመሳሳይ በግሩም ሁኔታ የተሰጠውን ኳስ ተጠቅሞ አቡበከር ናስር በ82ኛው ደቂቃ ከቀኝ ሳጥን ጠርዝ ሰብሮ በመግባት የቡናን መሪነት ወደ ሶስት ያሳደገች ግብ ማስቆጠር ችሏል። በተከታታይ ከተቆጠሩት ሁለት ግቦች በኋላ የኢትዮጵያ ቡና ተጫዋቾች ወደ አሰልጣቸው ካሳዬ አራጌ በማምራት አሰልጣኙ በተጫዋች ዘመኑ ይለብሰው የነበረውን 15 ቁጥር መለያ በመያዝ ደስታቸውን የገለፁበት መንገድ የተለየ ነበር።

ከግቦቹ በኃላ ሜዳ ላይ ከነበረው እንቅስቃሴ ይልቅ ትኩረቶች ሁሉ በፀጥታ አጠባበቅ ቸልተኝነት የተነሳ እጅግ ተቀራርበው ተቀምጠው በነበሩት የሁለቱ ክለብ ደጋፊዎች መካከል በቃላት መለዋወጥ ተጀምሮ በተፈጠረ ግጭት ጨዋታው ላይ ጥላ ማጥላት ችሏል። በርካታ ደጋፊዎችን ለጉዳት በዳረገው ሁነት በተለይ የፀጥታ አስከባሪዎች የኢትዮጵያ ቡና ደጋፊዎችን ከነበሩበት ቦታ ለማስለቀቅ በተከተሉት ያልተገባ አካሄድ በርካታ ቁጥር ያላቸው የኢትዮጵያ ቡና ሴት ደጋፊዎች ጉዳት አስተናግደው አስተውለናል።


ጨዋታው በኢትዮጵያ ቡናዎች 3-1 የበላይነት መጠናቀቁን ተከትሎ የክለቡ የልብ ደጋፊ የሆኑት አቶ ወርቀሸት በቀለ ከሰሞኑ በኢንተርኮንቲኔንታል ሆቴል በደጋፊዎች ማኅበር በተዘጋጀው የእራት ግብዣና የውይይት መርሐግብር ላይ የዛሬውን ጨዋታ ካሸነፉ ለመስጠት ቃል የገቡትን የማበረታቻ ገንዘብ ከጨዋታው መጠናቀቅ በኃላ ለኢትዮጵያ ቡና ተጫዋቾች አስረክበዋል።

© ሶከር ኢትዮጵያ