አንዳንድ ነጥቦች ስለ ውድድር ዘመን አጋማሽ የዝውውር መስኮት

የ2012 የውድድር ዘመን አጋማሽ የተጫዋቾች የዝውውር መስኮት ከሰኞ የካቲት 16 ጀምሮ ለአንድ ወር ክፍት ሆኖ ዝውውር እየተከናወነ ይገኛል። አንዳንድ ክለቦችም ተጫዋቾችን ማዘዋወር ጀምረዋል። በተከታዩ ፅሁፋችን ዐምና በዚህ ወቅት ከተፈፀሙ ዝውውሮች በመነሳት ያላቸውን አንድምታ እና ተያያዥ ጉዳዮች ለመቃኘት እንሞክራለን።

የተዘዋወሩ ተጫዋቾች ብዛት = 44
ዘንድሮ በክለቦቹ የሚገኙ ተጫዋቾች = 14
በአሁኑ ወቅት በክለቦቹ የማይገኙ ተጫዋቾች = 30

ባሳለፍነው የውድድር ዘመን አጋማሽ የዝውውር መስኮት 44 ተጫዋቾች ከስድስት ወር እስከ አንድ ዓመት የውል ጊዜ የተለያዩ የፕሪምየር ሊግ ተካፋይ የሆኑ ክለቦችን መቀላቀል ችለዋል። ነገር ግን በቁጥር 30 የሚሆኑት (68.18%) በክረምቱ ከተዘዋወሩበት ክለብ የለቀቁ ሲሆን የተቀሩት 14 (31.82%) ተጫዋቾች በአሁኑ ወቅት በክለቦቹ የሚገኙ ናቸው። ከነዚህም ውስጥ 15 የሚሆኑት አጥቂዎች ሲሆኑ አስራ አንዱ የመሐል፣ አራቱ ደግሞ የመስመር አጥቂነት ሚና ነበራቸው። በቦታው ከፈረሙት 11 ተጫዋቾችም መካከል ስምንቱ የውጪ ዜጎች ናቸው። ይህም የአጥቂ ስፍራ የክለቦች አንገብጋቢ ክፍተት መሆኑ እና አማራጭ ለማግኘት ወደ ውጪ እንዲያማትሩ የሚያመላክት ነው። ከዚህ ውጪ ከተቀሩት ፈራሚዎች ውስጥ ሰባቱ የተከላካይ ፣ አምስቱ የአማካይ ስፍራ ተጫዋቾች ሲሆኑ ቀሪዎቹ ሦስት ተጨዋቾች ግብ ጠባቂዎች ነበሩ።

* የአጋማሽ ዝውውሮች የክለቦቻችን ደካማ የተጫዋቾች ምልመላ ሥርዓት ነፀብራቅ ይሆን?

በእግርኳስ ደረጃቸው ከፍ ባሉ ሃገራት የሚገኙ ክለቦች የጥር የዝውውር መስኮትን ለሁለት ዋና ዓላማዎች ሲጠቀሙበት ይስተዋላል። የመጀመሪያው ምክንያት ክለቦቹ ለረጅም ጊዜ ለማስፈረም ሲከታተሏቸው የቆዩ ተጫዋቾች የውል ሒደት ላይ ለውጥ የሚኖር እና ተጫዋቾቹንም በአንፃራዊነት በቀላሉ ማግኘት የሚችሉ ከሆነ ምንም እንኳን አስቸኳይ ምክንያት ባይኖራቸውም የረጅም ጊዜ የቡድን ግንባታን እሳቤ ውስጥ በማስገባት የሚያስፈርሙበት ሂደት ነው። የውድድር ዘመኑ አጋማሽ የዝውውር መስኮት ሁለተኛ እና ዋነኛው ጥቅም ደግሞ ክለቦች በመጀመሪያው ዙር በተለያዩ የሜዳ ክፍሎች ላይ ክፍተት ስለመኖሩ በታመነባቸው ቦታዎች ላይ ተጫዋቾች በማዘዋወር በሁለተኛው ዙር ተወዳዳሪ ቡድንን ይዘው እንዲቀርቡ ማስቻል ስለመሆኑ ይታመናል።

በመሆኑም ክለቦች በመጀመሪያው አጋማሽ መገባደጃ ላይ አስገዳጅ ሁኔታዎች (ጉዳት ወይንም ቅጣት) እስካልተከሰተ ድረስ በሁለተኛው ዙር አዲስ ተጫዋቾች የሚያስፈልጓቸውን ቦታዎች ቀደም ብለው ለይተው ማወቅ ይጠበቅባቸዋል፤ ከዚያም በተለዩት ቦታዎች ላይ አማራጮችን መቃኘት እና ለሚፈልጉት አጨዋወት የተመቹ ተጫዋቾችን ከውል ሁኔታቸው ጋር በማገናዘብ አስቀድመው ስራዎችን መስራት የተለመደ አሰራር ነው።

በክረምቱ የዝውውር መስኮት ክለቦቻችን በሚያደርጓቸው ያልተጠኑ እና ቡድኑን በሚጠቅም ሁኔታ ያልተፈፀሙ ዝውውሮች ምክንያት ተጫዋቾችን በዓመቱ አጋማሽ በማሰናበት ሌሎች ተጫዋቾችን በተመሳሳይ ባልተጠና መንገድ ሲያስፈርሙም ይታያል። ይህ ጉዳይ በተለይም ክለቦቻችንን በሚቀላቀሉ የውጪ ሃገር ዜጋ ተጫዋቾች ላይ በስፋት ይስተዋላል። በመጀመሪያው የውድድር አጋማሽ ክለቦቹ ለተጫዋቾቻቸው ‘በአቋም መውረድ’ ምክንያት የሰጡትን የማስጠንቀቂያ ደብዳቤዎች ስንመለከት ዘንድሮም ተመሳሳይ ነገር እንደሚፈጠር የሚጠቁመን ነው።

ነገር ግን በእኛ ሀገር መሰል አሰራሮች ስለመተግበራቸው በሚያጠራጥር መልኩ የሚፈፀሙት ዝውውሮች በሚፈለገው ደረጃ ቡድኖች ሲጠቅሙ አይስተዋልም፤ ምንም እንኳን በዚህ ወቅት የሚዘዋወሩ ተጫዋቾች በፍጥነት ቡድኑን እንዲጠቅሙና እንዲያሻሽሉት (Immediate Effect) ቢጠበቅም አብዛኞቹ ተጫዋቾች ኮታ ከመሙሏት የዘለለ ቡድኖችን ሲያሻሽሉ አይስተዋልም። ይህ ሁኔታ በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ ከክለቦቹ ደካማ የምልመላ ስርዓት ጋር የሚገናኝ ነው ፤ መስኮቱ ስለተገኘ ብቻ ክለቦች በጥድፊያ ስለሚያዘዋውሯቸው ተጫዋቾች የጨዋታ ባህሪ ፣ ወቅታዊ አቋም እና ሌሎች መረጃዎች ላይ በደንብ ጥናት ሳይደረግባቸው ስለሚመጡ በሂደት ቡድኑን የመጥቀማቸው ነገር እምብዛም አልተመለከትንም።

በሊጋችን እንኳንስ ፈጥኖ ማሰብ እና መንቀሳቀስ በሚጠይቀው የውድድር አጋማሽ ዝውውር ይቅር እና ሙሉ ቡድኑ በሚዋቀርበት የቅድመ ውድድር የዝግጅት ወቅት እንኳን ከበቂ ትንተና የተነሱ ዝውውሮች የማይፈፀሙ መሆናቸውም የአጋማሽ ዝውውሮችን ፈተና ከፍ ያደርገዋል። ቀድሞውንም በአግባቡ ባልተዋቀረ እና ዓመቱ ሳይጀመር አስቀድሞ ከአምናው ስብስቡ ደካማ ጎን በመነሳት ክፍተቱን ያልደፈነ ወይንም ክፍተቱን ለመድፈን የወሰዳቸው እርምጃዎች ያልተሳኩለት ክለብ በውድድር አጋማሽ ላይ ቀዳዳዎቹ በዝተው በጅምላ እና በችኮላ ወደ ገበያ ለመውጣት ሊገደድ ይችላል። በመሆኑም ክለቦች በዝውውር ዙሪያ ሙሉ ትኩረታቸው ክረምቱ ሆኖ ከሁለተኛው ዙር መጀመር አስቀድሞ ያለውን ጊዜ እጅግ ከአቅም በላይ ለሆኑ ምክንያቶች ብቻ ሲሉ መጠቀም ይኖርባቸዋል።

* በወራጅነት ስጋት የሚገኙ ቡድኖች በጅምላ ተጫዋቾች ማዘዋወር እና የተጫዋቾች ጥራት

ዐምና በአጋማሹ የዝውውር መስኮት በርካታ ተጫዋቾችን ያስፈረመው ደደቢት (8) ሊጉ ሲጠናቀቅ የመውረዱ ነገር አልቀረለትም። ደደቢት በመጀመሪያው ዙር ከደመወዝ ጣሪያ እና ከአካሄድ ለውጥ መነሻነት በመጀመሪያ ዙር ይዞ ከቀረበው ቡድን ላይ በሁለተኛው ዙር እጅግ በርካታ ለውጦችን ቢያደርግም መሰል የጅምላ የተጫዋቾች ቅየራ ወደ ክለቡ ከመጡት የተጫዋቾች ጥራት ደረጃ ጋር ተዳምሮ ቡድኑን በሽግግር ውስጥ እንዲገባ ምክንያት ሆኖታል። በሁለተኛው አጋማሽ ከእያንዳንዱ ጨዋታዎች አዎንታዊ ውጤት በሚጠብቅበት ወሳኝ ወቅትም ዳግም በቡድን ግንባታ ውስጥ በመግባቱ በሚፈለገው ደረጃ ለውጥ ማምጣት ሳይችል ቀርቷል።

በአንፃሩ በተመሳሳይ ወቅት በመጀመሪያው ዙር መገባደጃ ላይ የወራጅነት ስጋት ያንዣበበቸው በተለይ ስሁል ሽረ እና ወላይታ ድቻ በተመሳሳይ በርከት ያሉ ተጫዋቾችን ቢያስፈርሙም በትክክልም ቡድኑን ማሻሻል የቻሉ ተጫዋቾችን በማዘዋወራቸው እህል ውሃቸውን ለማስቀጠል የነበራቸውን ውጥን አሳክተዋል። በወቅቱ ስሁል ሽረ(9)፣ ወላይታ ድቻ (5) ተጫዋቾን ቢያስፈርሙም በሽረ ከፈረሙት 7 የሚጠጉ ተጫዋቾች በሁለተኛው ዙር በቀጥታ ወደ መጀመሪያ ተሰላፊነት ሰብረው በመግባት ቡድኑ በሊጉ እንዲቆይ አስችለዋል። በተመሳሳይ ወደ ወላይታ ድቻ ከተዘዋወሩት ተጫዋቾች ውስጥ አራቱ ተጫዋቾች የመጀመሪያ ተመራጭ በመሆን ቡድኑ ላይ ከፍተኛ ለውጥን መፍጠር ችለዋል። እንደ ባህል በርካታ ተጫዋቾች ማዘዋወር በተያዘበት የሀገራችን ሊግ ምንም እንኳን በዚህ ወቅት በቁጥር የበዙ ተጫዋቾችን ማምጣት ባይመከርም እንደ የአምናዎቹ ድቻ እና ሽረ ዝውውሮች የተሻለ ጥራት ያላቸው ተጫዋቾች የሚዘዋወሩ ከሆነ ቡድን የምመጠገን ዕድላቸው ሰፊ ነው።

* የአጋማሽ ዝውውር ክፍተቶችን መሸፈኛ ብቸኛው መንገድ?

ጉዳት፣ ቅጣት፣ የአቋም መውረድ እንዲሁም ሌሎች ምክንያቶች ቡድኖች በስብስባቸው ውስጥ ያላሰቡት ክፍተት እንዲፈጠርባቸው እና ወደ ተጫዋቾች ግዢ እንዲሄዱ ሊያስገድድ ይችላል። ነገር ግን ከቻምፒዮንነት እና ሁለተኝነት እስከ ወራጅ ቀጠናው ድረስ ባለው የሊጉ ሰንጠረዥ መሀል ክፍል ላይ መጨረስ ስኬትም ሆነ ውድቀት ባለሆነበት ሊግ ውስጥ ለተፈጠሩ ክፍተቶች ሁሉ ወደ ገበያ ማማተሩ የሚመከር አይመስልም። በመሆኑም ክለቦች ወደ ውድድር አጋማሽ ዝውውር ከመሄዳቸው አስቀድሞ ያሉበትን ደረጃ ከዓመቱ የውጤት ዕቅዳቸው ጋር ገምግመው የተፈጠሩ ክፈተቶች ካሉ አዲስ ተጫዋቾችን ከማዘዋወር ይልቅ በወጣት ተጫዋቾቻቸው እንዲደፈኑ እምነት መጣል እና መስራት ይጠበቅባቸዋል። ይህም ክፍተትን ከመድፈን ባለፈ የወጣቶቹን በራስ መተማመን በማሳደግ፣ የወደፊቱን ቡድን ከመገንባት እና ወጪን ከማስቀረት በተጨማሪም ያለበቂ ትንተና ከሚደረጉ ድንገተኛ ግዢዎች እና ኪሳራቸው ጭምር ያድናል።

© ሶከር ኢትዮጵያ