የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ የ1ኛ ዙር የክለቦች ዳሰሳ – ባህር ዳር ከተማ

የ2012 የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ የመጀመሪያው ዙር የውድድር ጊዜ መገባደድ ተከትሎ ሶከር ኢትዮጵያ ክለቦችን በተናጥል በመዳሰስ ላይ ተረገኛለች። በዚህ ፅሁፍም የመጀመሪያውን ዙር በ23 ነጥቦች 5ኛ ደረጃ ላይ ሆኖ ያጠናቀቀው ባህር ዳር ከተማን እንመለከታለን።


የመጀመሪያ ዙር ጉዞ

ዐምና በታሪካቸው ለመጀመሪያ ጊዜ በኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ የተሳተፉት ባህር ዳር ከተማዎች ውድድሩን 8ኛ ደረጃን ይዘው ካገባደዱ በኋላ የተለያዩ ለውጦችን በሜዳ እና ከሜዳ ውጪ ባሉ የቡድኑ ክፍሎች ላይ አድርገዋል። በተለይ ክለቡ አሰተዳደራዊ መዋቅሩን እንደ አዲስ ካስተካከለ በኋላ አሰልጣኝ ጻውሎስ ጌታቸውን እና በርከት ያሉ ነባር ተጨዋቾችን በመልቀቅ አዲሱን ዓመት በአዲስ አቀራረብ ለመጀመር ሞክሯል። በዚህም በክረምቱ የዝውውር ጊዜ 9 አዳዲስ ተጨዋቾች እና ክለቡን እንዲያሰለጥኑ በቅዱስ ጊዮርጊስ ቤት ለበርካታ ዓመታት በምክትልነት ያገለገሉትን አሰልጣኝ ፋሲል ተካልኝ ወደ ቡድኑ አምጥቷል።

የመጀመሪያ የሊጉ ጨዋታቸውን ወደ አዳማ አቅንተው ጅማን የገጠሙት ባህር ዳሮች አንድ ነጥብ ከአዳማ አበበ ቢቂላ ስታዲየም በመውሰድ ውድድሩን “ሀ” ብለው ጀምረዋል። በመቀጠልም የዓምናው የሊጉን አሸናፊ ቡድን መቐለ 70 እንድርታን በሜዳቸው በመጋበዝ እና 3-2 በማሸነፍ ተስፋን ሰንቀው አጀማመራቸውን አሳምረዋል። ነገር ግን ቡድኑ ከዚህ በኋላ የተደረጉ ጨዋታዎችን በሜዳው እያሸነፈ ከሜዳው ውጪ ደግሞ እየተረታ እና ነጥብ እየጣለ በመጀመሪያዎቹ ሳምንታት የተሰነቁትን በጎ ተስፋ መና አስቀርቷል።

ወጣ ገባ አቋም ከሚያሳዩ በርካታ የሊጉ ክለቦች (ምናልባት ሁሉም) መካከል አንዱ የሆኑት ባህር ዳሮች የሚተነበይ እንቅስቃሴ እና ውጤት ማሳየት ተስኗቸው የዓመቱን አጋማሽ አገባደዋል። በተለይ ቡድኑ ሊጉ ሲጀምር በነበሩት ጨዋታዎች እና በኋላ በተደረጉት ጨዋታዎች የተለያዩ የጨዋታ መንገዶችን በመተግበር የመጀመሪያውን ዙር አጠናቋል።

የውጤት ንፅፅር ከ2011 ጋር

በ2010 ቡድኑ ወደ ፕሪምየር ሊግ ባደገበት ዓመት በ22 ነጥቦች 7ኛ ደረጃ ይዞ የመጀመርያውን ዙር ያጠናቀቀ ሲሆን በዚህ ዓመት ደረጃውን በ2፤ ነጥቡን በአንድ አሻሽሏል። በጎል ማስቆጠር ደረጃ ዘንድሮ እጅጉን ተሻሽሎ በ10 የበለጠ ጎል ሲያስቆጥር በአንፃራዊነት ጠንካራ ከነበረው የዓምናው የኋላ መስመር ዘንድሮ እጅግ ተዳክሞ በ15 የበለጡ ጎሎች አስተናግዷል።

የቡድኑ አቀራረብ

ለመጀመሪያ ጊዜ በዋና አሰልጣኝነት ሚና እየሰሩ ባሉት ፋሲል ተካልኝ የሚመራው ቡድኑ በእስካሁኑ የሊጉ ጉዞ ወጣ ገባ አቋሞችን ሲያስመለክት ቆይታል። ቡድኑ ሊጉ ሲጀምር በነበሩት ተከታታይ ጨዋታዎች ኳስን ይዞ ለመንቀሳቀስ ቢሞክርም የኋላ ኋላ ግን ቀጥተኝነትን፣ የመልሶ ማጥቃት እንቅስቃሴዎችን እና የቆሙ ኳሶችን አብዝቶ ወደ መጠቀም ተለውጧል። እርግጥ ለዚህ የጨዋታ አቀራረብ መለያየት የተጨዋቾች ጉዳት እና ከሜዳ ውጪ ያሉ አስተዳደራዊ ክፍተቶች እንደ ዋነኛ ምክንያትነት ቢጠቀሱም ቡድኑ በእነዚህ የተለያዩ የጨዋታ መንገዶች ጨዋታዎችን አከናውኗል።

በአብዛኛው (ምናልባት በሁሉም) የሊጉ ጨዋታዎች በ4-3-3 የተጨዋች አደራደር ቅርፅ ወደ ሜዳ ሲገቡ የነበሩት ባህር ዳሮች የተለያዩ የአማካይ መስመር ተጨዋቾችን ጥምረት በየጨዋታዎቹ በመጠቀም ሲጫወቱ ተስተውሏል። በተለይ ቡድኑ ለአጥቂዎች በአንፃራዊነት ቀርበው ሲጫወቱ የነበሩ ተጨዋቾች (የ8 ቁጥር ተጨዋቾች ሚና) በመቀያየር ላለመገመት ጥሯል። በዚህ ተቀያያሪ የአማካይ ክፍል ቁልፍ ሚና የነበረው ፍፁም ዓለሙ ከተለምዶ የአማካይ መስመር ሚና በመለየት የተጋጣሚን የተከላካይ መስመር ሲረብሽ ታይቷል። በተለይ ተጨዋቹ ከዋና የቡድኑ አጥቂዎች ግራ እና ቀኝ እንዲሁም ፊት ላይ በመገኘት የሚያደርጋቸው እንቅስቃሴዎች ቡድኑን እጅግ ጠቅመዋል። ተጨዋቹም ይህ ከአሰልጣኙ የተሰጠውን ልዩ ሚና በአግባቡ በመወጣት ለቡድኑ 8 ጎሎችን በተሰለፈባቸው ጨዋታዎች አስቆጥሯል።

ከአማካይ ክፍሉ በተጨማሪ በሌሎች የቡድኑ ክፍሎች ውስጥም መለዋወጦች ይታያሉ። በተለይ ቡድኑ ተጋጣሚ ላይ ካገባው በርካታ ጎሎች በላይ ያስተናገደው የሚበልጠው የተከላካይ መስመሩ ቡድኑን መሰረት ያጣ አስመስሎታል። በግል ደረጃ ጥሩ ጥሩ ተጨዋቾችን የያዘው ይህ የተከላካይ ክፍል በተለያዩ ምክንያቶች እንደ ቡድን የመከላከሉ ጉዳይ ላይ ክፍተቶችን አሳይቶ 23 ግቦችን በ15 የሊጉ ጨዋታዎች አስተናግዷል። ምንም እንኳን ይህ የላላ የተከላካይ ክፍል በመከላከሉ ክፍተቶች ቢታዩበትን በተቃራኒው ማጥቃቱ ላይ ጉልህ ሚና ይጫወታል። በተለይ የቡድኑ የመስመር ተከላካዮች ከኋላ ሆነው ከሚያስጀምሯቸው ፈጣን የመስመር ላይ እንቅስቃሴዎች በተጨማሪ መስመሩን ይዘው ወደ ተጋጣሚ ሳጥን የሚሮጡበት መንገደኞች ተጋጣሚን ሲፈትን ታይቷል። ከዚህ በተጨማሪም ይህ ክፍል የቆሙ ኳሶችን ወደ ግብነት በመቀየር የተዋጣለት ጊዜን አሳልፏል።

በአንፃራዊነት የተረጋጋ የሚመስለው የቡድኑ የፊት መስመር በሊጉ የአጋማሽ ጉዞ አስፈሪነቱ ታይቷል። በተለይ ቡድኑ ግርማ እና ወሰኑ/ዜናው በሚያደርጉት የመስመር ላይ ፈጣን እንቅስቃሴ እየታገዘ ጥቃቶችን ከመስመር ለመሰንዘር ይጥራል። ከዚህ ውጪ የቡድኑ የመሃል አጥቂ ማማዱ ሲዲቤ ከመስመር የሚነሱ ኳሶችን በአግባቡ በመጠቀም እንዲሁም ከኳስ ውጪ በሚያደርጋቸው እንቅስቃሴዎች ተከላካዮችን እየሳበ ለቡድን አጋሮቹ ምቹ ቦታዎችን በመስጠት ቡድኑን ጠቅሟል።

ከምንም በላይ ቡድኑ ከዚህ ቀደም በነበሩት ዓመታት የነበረበትን የቆሙ ኳሶችን አጠቃቀም ክፍተት በማሻሻል እና ቀጥተኝነትን በማብዛት አጋማሹን በጥሩ ውጤት አገባዷል።

ጠንካራ ጎን

በደረጃ ሰንጠረዡ አስተማማኝ ቦታ ላይ ተቀምጦ ሊጉን ያጋመሰው ባህር ዳር በሜዳው እጅግ ጠንካራ ቡድን ነው። ቡድኑ በሜዳው ካደረጋቸው 7 ጨዋታዎች ሰባቱንም በማሸነፍ እና ተጋጣሚ ላይ 19 ግቦችን በሜዳው በማስቆጠር ሃያልነቱን አሳይቷል። በተለይ ቡድኑ በመጀመሪያዎቹ 4 ተከታታይ የሜዳው ላይ ጨዋታዎች 3 እና ከ3 በላይ ግቦችን በጥሩ የጨዋታ አቀራረብ በማሸነፍ ጠንካራነቱን አስመስክሯል።

ለተለያዩ የጨዋታ አቀራረቦች የሚመቹ ተጨዋቾችን የያዘው ቡድኑ አማራጮችን በተለያዩ አስገዳጅ በሆኑ እና ባልሆኑ አጋጣሚዎች ሲጠቀም ታይቷል። ይህም የተለያየ የጨዋታ አቀራረቡ ቡድኑን እንዳይገመት አድርጎታል። ከዚህ በተጨማሪ ቡድኑ የጨዋታ የመጀመሪያ ደቂቃዎችን በፍጥነት በማከናወን ጨዋታውን ለመወሰን ይጥራል። በተለይ ቡድኑ በሜዳው ሲጫወት የመጀመሪያዎቹን ደቂቃዎች ግብ ለማስቆጠር ይጠቀምባቸዋል።

ከምንም በላይ ቡድኑ በሜዳው ሲጫወት የሚያሳየው ጀብደኝነት ድንቅ ነበር። በተጨማሪም ቡድኑ ተጋጣሚ ላይ ግብ ለማስቆጠርም የግዴታ የፊት መስመር ተሰላፊዎቹን አይጠብቅም። ወይበአማካይ አልያም በተከላካይ ተጨዋቾቹ ቡድኑ ግቦችን እያስቆጠረ አጥቂዎቹ ላይ ብቻ የግብ ማስቆጠር ኃላፊነት እንዳይኖር አድርጓል።

ደካማ ጎን

የቡድኑ ዋነኛ ድክመት የሜዳ ውጪ ጨዋታዎችን የማሸነፍ አይናፋርነት ነው። ቡድኑ እስካሁን ባደረጋቸው 6 የሜዳ ውጪ ጨዋታዎች አንዱንም ሳያሸነፍ በአራቱ እጁን ሰጥቶ በሁለቱ አቻ ወጥቶ ተመልሷል። ከምንም በላይ ቡድኑ ከሜዳው ውጪ ባደረጋቸው በእነዚህ 6 ጨዋታዎች 13 ግቦችን ሲያስተናግድ (በጠቅላላ ጨዋታዎች ካስተናገደው ከ50% በላይ) 3 ግቦችን ብቻ ተጋጣሚዎቹ ላይ አስቆጥሯል። እነዚህን ቁጥሮች ስንመለከት ቡድኑ ምን ያህል ከሜዳው ውጪ እንደሚቸገር ይጠቁማል።

በተለያዩ ምክንያቶች የተለያዩ ተጫዋቾችን በየጨዋታዎቹ የሚጠቀመው ቡድኑ በመጠኑ የቅንጅት ክፍተት ያለበት ይመስላል። በተለይ ቡድኑ እንደ ቡድን የሚጫወትበት መንገድ እና በተጨዋቾች መካከል ያለው የወረደ የእርስ በእርስ መስተጋብር ክፍተቶችን ሲፈጥር ይስተዋላል። ከምንም በላይ ደግሞ ይህ ጉዳይ ከወገብ በታች ባሉት የቡድኑ ተጨዋቾች ላይ ይነበባል።

ከላይ በቁጥሮች ለመጥቀስ እንደተሞከረው የቡድኑ የኋላ መስመር ከፍተኛ ችግሮች ይስተዋሉበታል። በተለይ ቡድኑ ሽግግሮችን (ከማጥቃት ወደ መከላከል) የሚመክትበት መንገድ እጅግ የወረደ እና ለተጋጣሚ ቡድን ተጨዋቾች ምቹ ሁነቶችን የሚፈጥር ሆኖ ታይቷል። ከዚህ በተጨማሪም ይህ የተከላካይ መስመር አልፎ አልፎ የትኩረት ማነሶች እና መዘናጋቶች ይታዩበታል። በተለይ ቡድኑ በሚመራበት ወቅት በሚፈጠር የመዘናጋት ችግሮች በተደጋጋሚ ባለቀ ሰዓት ፈተናዎች ውስጥ ሲጥለው ተስተውሏል።

ከዚህ ውጪ የቡድኑ የአማካይ ተጨዋቾች ለቡድኑ የኋላ መስመር ተገቢ ሽፋን ሲለግሱ አልታይም። በተለይ አጥብበው የሚጫወቱት እነኚህ የአማካይ መስመር ተጨዋቾች በአብዛኛው በማጥቃት ላይ ተስበው በሚያደርጉት እንቅስቃሴ ቡድኑን ከኋላ ተጋላጭ አድርገውታል። በተጨማሪም ቡድኑ የመጀመሪያ የመከላከል መስመር የሚዘረጋበት (first line of defence) መንገድ ያልተደራጀ ነበር። ሦስቱ የቡድኑ የፊት መስመር አጥቂዎች በተናጥል ተጋጣሚ ላይ የሚያደርጉት ጫና (pressing) መድከም ተጨዋቾቹን እንዲባክኑ ብቻ እያደረጋቸው እንደነበር ተስተውሏል።

በሁለቱ የጨዋታ አጋማሾች ሁለት አይነት መልክ የሚያሳየው ቡድኑ በተለይ በሁለተኛ አጋማሽ ደካማ እንቅስቃሴዎችን ሲያሳይ ተስተውሏል። ቡድኑ በ15ቱ ጨዋታዎች ከተቆጠረባቸው 23 ጎሎች አብዛኞቹ በ2ኛ አጋማሽ የተቆጠሩ ግቦች ናቸው።

በሁለተኛ ዙር ምን ይጠበቃል?

በአንደኛው ዙር የሊጉ ጨዋታዎች አስከፊ ውጤት ያላስመዘገበው ቡድኑ በሁለተኛው ዙር ተጠናክሮ ይቀርባል ተብሎ ይገመታል። በተለይ ቡድኑ ካሉበት ችግሮች ያሉት አውንታዊ ጎኖች ስለሚበልጡ ጠንካራ ፉክክር ያደርጋል ተብሎ ይታሰባል።

ከምንም በላይ ቡድኑ ግብ የሚያስተናግድበትን አባዜ የሚተው ከሆነ በጎ ነገሮች ሊያገኝ ይችላል። በተለይ ይህ የተከላካይ መስመር በልምምድ ወይንም በግዢ ጥገናዎችን የሚያገኝ ከሆነ ቡድኑ ከዚህም በላይ ሊጠነክር ይችላል ተብሎ ይጠበቃል።

በተጨማሪም ቡድኑ በተለይ በሁለተኛ አጋማሽ የሚያሳየው የወረደ አቋም መስተካከል አለበት። ቡድኑ ጨዋታዎችን በመጀመሪያው አጋማሽ የመወሰን ጥልቅ ፍላጎት ከማሳየቱ የተነሳ ሁለቱን የጨዋታ አጋማሾች በተመጣጠነ ብቃት አያከናውናቸውም። ከዚህ መነሻነት በሁለተኛው አጋማሽ ተጋጣሚዎች ቡድኑ ላይ ጫናዎችን ሲያሳድሩ ይታያል። ስለዚህ በሁለተኛው ዙር ቡድኑ ጨዋታዎችን በተመጣጣኝ አቀራረብ በሁለቱም አጋማሾች ማከናወን ይጠበቅበታል።

የአንደኛ ዙር የቡድኑ ኮከብ ተጫዋች

ፍፁም ዓለሙ – እርግጥ ቡድኑ ከአንድ በላይ ጥሩ ጊዜን ያሳለፉ ተጨዋቾች በአንደኛ ዙር ቢያስመለክትም በይበልጥ ነጥሮ የወጣው ተጨዋች ፍፁም ዓለሙ ነው። ይህ ተጨዋች ከተሰለፈበት የአማካይ ቦታ እየተነሳ 8 ጎሎችን ከማስቆጠሩ በተጨማሪ 1 ጎል የሆነ ኳስ አመቻችቶ በማቀበል በ9 ጎሎች ላይ ቀጥተኛ ተሳትፎ አድርጓል።

በ15ቱ ጨዋታዎች ተጫዋቹ በእነ ሲዲቤ/ስንታየሁ አማካኝነት የሚፈጠርለትን የመሮጫ ሜዳ (ከተከላካይ ጀርባ) በአግባቡ በመጠቀም የሚያደርጋቸው ጥቃቶች ልዩ ነበር። በተጨማሪም ወደ መስመር በመውጣት ከመስመር ተጨዋቾቹ ጋር የነበረው መስተጋብር ድንቅ ነበር። ከዚህ ውጪ ተጨዋቹ የመልሶ ማጥቃት እንቅስቃሴዎችን የሚያፋጥንበት መንገድ እጅግ ቡድኑን ጠቅሟል።

ተስፋ የሚጣልበት ተጫዋች

ሳሙኤል ተስፋዬ – በክረምቱ የዝውውር መስኮት ቅዱስ ጊዮርጊስን ለቆ ባህር ዳርን የተቀላቀለው ሳሙኤል ተስፋዬ በአንደኛ ዙር የሊጉ ጨዋታዎች በግሉ ተስፋዎችን አሳይቷል። ይህ ወጣት የግራ መስመር ተጨዋች ፋሲል ተካልኝን ተከትሎ ቡድኑ ከተቀላቀለ በኋላ ባደረጋቸው ጨዋታዎች ድንቅ ብቃት አሳይቷል። እርግጥ በመጀመሪያዎቹ ሳምንታት በተደረጉ ጨዋታዎች ተጨዋቹ ድክመቶችን ቢያስመለክትም ወዲያው ከነበረበት ሰመመን በመንቃት ምርጥ ብቃቱን አሳይቷል።

ተጨዋቹ ፍጥነቱን ተጠቅሞ ከሚያደርጋቸው የመስመር ላይ እንቅስቃሴዎች በተጨማሪ ወደ መሃል ሜዳ እየገባ የሚያደርጋቸው የኳስ ንክኪዎች ቡድኑ በመሃል ሜዳ ላይ የተጨዋች ቁጥር ብልጫ እንዲያገኝ አስችሎታል። እነዚህን ተከትሎ ይህ ባለተሰጥኦ ተጨዋች በቀጣይ ብቃቱን ጠብቆ የሚቆይ እና ያሉበትን የውሳኔ ችግሮች የሚያስተካክል ከሆነ ቡድኑን ብሎም የኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድንን የሚጠቅም ይሆናል።

© ሶከር ኢትዮጵያ